“ተማሪ በሞተ በሰባት ዓመቱ ተምሮ ይመጣል ትላለች እናቱ”

ይህ ሥነ ቃል ከሞቀ ከደመቀ ቤቱ የላመ የጣመን ትቶ የነገው ካህን፣ መምህር፣ ሊቅ የመሆን ህልሙን ለማሳካት ቃለ እግዚአብሔር ፍለጋ የተሰደደው ተማሪ በረሃብ፣ በእርዛት፣ በሽታን መቋቋም ተስኖት ወደ ቤቱ አለመመለሱን ፤ወጥቶ መቅረቱን የተማሪውን መከራ ለማዘከር በሰፊው በማኅበረሰቡ ዘንድ የተነገረ ቃል ነው።



ተማሪው በተማሪ ቤት ምንም ዓይነት የምግብ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳት የመሳሰለውን ድጋፍ አያገኝም።

ጥሬ ቆርጥሞ፣ ኮቸሮ አኮችሮ በአንድ እራፊ ጨርቅ ተጠቅልሎ፤ ማደሪያ ሳያምረው በሳር ጎጆ ተጠግቶ የመማርያ አዳራሽ ሳይኖረው በዛፍ ጥላ ሥር ትምህርቱን በትጋት በንቃት ይከታተላል።

ተማሪው ከምግብ እጥረት የተነሳ ሰውነቱ ቀጥኖና አጥሮ በዳፍንት በሽታ በማታ ማየት እየተሳነው የትምህርት ቤቱን ኑሮ በመከራ ይገፋል።

ተማሪው በቂ ንፁሕ የመጠጥ ውኃ ፣ የመጸዳጃ ቤት ካለማግኘቱ የተነሣ ለልዩ ልዩ ተላላፊ በሽታዎች ይጋለጣል። በዚህም ሰውነቱ በምግብ እጥረት የተጎዳ በመሆኑ በሽታን መቋቋም ስለማይችል ለሞት በቀላሉ ይጋለጣል። 

ብዙዎችም ከትምህርት ቤት ያተረፉት በሽታ በዕድሜአቸው ሙሉ በአገልግሎታቸው ሲያውካቸው ይገኛል። 

ዛሬ በዓለም ብሎም በኢትዮጵያ በግልና በአካባቢ ንጽሕና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችን ለመቀነስና የተሻለ ዓለምን ለመፍጠር የሚረባረቡ አካላት ቢኖሩም የአብነት ተማሪዎች ግን ዛሬም የችግሩ ተጠቂዎች እንደሆኑ ይገኛሉ።

በተማሪ ቤት ጎልቶ የሚታየውን ችግር በተለየም ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የበሽታ ዓይነት ከግልና ከአካባቢ ንጽሕና ጉድለት፤ ከንጹሕ ውኃ መጠጥ አለማግኘት፤ ከምግብ እጥረት ጋር ተደምሮ የሚመጣ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን የጤና እክል ለመታደግ 12 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ሚያደርግ መርሐ ግብር ነድፎ የሁሉንም ተሳትፎ እየጋበዘ ይገኛል። የመርሐግብሩ ሥያሜ ተማሪ በሞተ……..የሚል መሪ ቃል እዲኖረው ተደርጓል። ምክንያቱም እውቀትን ለመሻት መራራውን ሞት የተጎነጩ ሊቃውንትን ለማዘከርና አሁን ያሉትን ተማሪዎች ሕይወት ለመታድግ ገላጭ ቃል ሆኖ በመገኘቱ ነው።

• የመርሐ ግብሩ አስፈላጊነት

  • የግልና የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ አምላካዊ ትዕዛዝ መሆኑን ለማስገንዘብና ተፈጻሚ ለማድረግ (ኦሪት ዘዳግም 23፣13) 
  • በአብነት ትምህርት ቤት በግልና በጋራ የንጽሕና አጠባበቅ ችግር የሚፈጠረውን የሕመምና የሞት አደጋ ለመቀነስ 
  • ተማሪዎቹ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ምቹ የሆነ የመማርና የማስተማር ሁኔታ መፍጠር
  • በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ያለውን ዝቅተኛ የጤናና የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ 
  • የአብነት ተማሪው ስለጤና አጠባበቅ ምንነት ተረድቶ እርሱም ለኅበረተሰቡ እውቀቱን እንዲያስፋፋ ለማገዝ 

• ከእርሶ ምን ይጠበቃል

  • ፕሮግራሙ እውን እንዲሆን የሙያ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል።
  • ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ 
  • 200 ግራም የሆነ 12,000 የልብስ ሳሙና 
  • 10 ባለ 3,000 ሊትር የውኃ ማጠራቀሚያ የፕላስቲክ ታንከር 
  • የውኃ ማከሚያ ኬሚካሎች
  • ለውኃ መጠጫ፣ ለማብሰያ፣ ለመመገቢያ የሚሆኑ የተለያዩ መጠን ያላቸው ቁሳቁስ
  • ለገላና ለልብስ ማጠቢያ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን 
  • የግል ንጽሕና መጠበቂያ የሚያገለግሉ (መርፌ፣ ምላጭ)
  • በ10 ትምህርት ቤቶች የጋራ መጸዳጃ ቤት ሥራ እንዲሁም 
  • የጤና አጠባበቅ ሥልጠና 

የድጋፍ ማሰባሰቢያ 
ጊዜ፦ ከመጋቢት 21 እስከ ሚያዝያ 11 ቀን 2005 ዓም 
ቦታ፦ በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ
ለበለጠ መረጃ ስልክ፦ 0911 751529 / 0913 102621