ቤተ ጣዖቱ ተዘጋ! የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ኅዳር 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

“በአርሲ ሀገረ ስብከት  በመርቲ ወረዳ ልዩ ስሙ ፈረቀሳ በተባለ ሥፍራ ከ120 አመታት በላይ የአርሲዋ እመቤት” በሚል የባዕድ አምልኮ ሥርዓት ሲፈጸምበት በነበረ ሥፍራ ላይ የባዕድ አምልኮ ሥርዓቱን በማጥፋት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን  ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ኅዳር 1 ቀን 2005 ዓ.ም. አኖሩ፡፡

 

ብፁዕነታቸው በሥፍራው ለተገኙት ምእመናን በሰጡት ቃለ ምዕዳን “ከዚህ በፊት ይህ ቦታ የአርሲዋ እመቤት በሚል የዲያቢሎስ መፈንጫ፡ የሕሙማን መዋያ የነበረ ሲሆን ከአሁን በኋላ ግን የምሕረትና የፈውስ አደባባይ እንዲሁም የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ የሚፈጸምበት ሆኗል” ብለዋል፡፡ ለአካባቢው ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክትም  የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ይወጡ ዘንድ አሳስበዋል፡፡

 

ይህ የባዕድ አምልኮ ሥርዓት ከ1885 ዓ.ም. ጀምሮ ወ/ሮ ሻበሻ ወርቅ ይመር በምትባል ሴት በሥፍራው እንደተመሠረተና ምዕመናንን በማሳሳት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንዲያፈነግጡ በማድረግ እስካረፈችበት እሰከ ጥቅምት 19 ቀን 1912 ዓ.ም ድረስ ቆይታለች፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ሲከተሏትና የመሠረተችውን የባዕድ አምልኮ ሥርዓት ሲያከናውኑ የነበሩ ተከታዮቿ  “የአርሲዋ እመቤት”፤ የአካባቢው ሙስሊሞች ደግሞ “ሞሚናት” በሚል አጠራር ሥርዓቱን በማጠናከር በዚሁ ቦታ ላይ በቅዱስ ገብርኤል ስም በየዓመቱ ጥቅምት 19 እና  ግንቦት 19 ቀን በከፍተኛ ሁኔታ የባዕድ አምልኮ ሥርዓቱን ለብዙ ዘመናት ሲያከናውኑት እንደቆዩ ይነገራል፡፡

 

የብዙ ዘመናት ጸሎት ሰምሮ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል መመሪያ ሰጪነትና ድጋፍ ሀገረ ስብከቱና የወረዳው ቤተ ክህነት እንዲሁም ምእመናን ባደረጉት ጥረት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነትና ሥርዓት መሠረት ባዕድ አምልኮ መፈጸም የተወገዘ መሆኑን በማስተማርና በማሳመን የመሠረት ድንጋዩ እንዲቀመጥና የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ ስምምነት ላይ ተደሷርል፡፡

 

በአካባቢው የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮችም የእርሻ ማሳቸውን ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ በመፍቀድ ከ1200,00 ብር በላይ በማዋጣት መለገሳቸውን የደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡