library

ቤተ መጻሕፍቱ የመጻሕፍትና ቁሳቁስ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጀ፡፡

ሰኔ 04 ቀን 2004 ዓ.ም

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖአምላክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን ቤተ መጻሕፍት እየሰጠ ያለውን አገልግሎት አጠናክሮ ለመቀጠል ይረዳው ዘንድ የመጻሐፍትና ቁሳቁስ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አዘጋጀ፡፡

library

በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ሥር የሚገኘው ቤተመጻሕፍት ፡-“ስትመጣ …በርኖሱንና መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን አምጣልኝ” (2ኛ ጢሞ.4÷13) በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው በዚሁ የመጻሐፍትና ቁሳቁስ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር፡-

 

•    ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ምክርና ትምህርት የሚሰጡ መጻሕፍት፣ መዛግብት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦችን፣ የአስኳላ (አካዳሚካል) መጻሕፍት፣
•    ጥናታዊ ጹሑፎችን እንዲሁም
•    ቤተመጻሕፍቱን ለማደራጀት የሚያግዙ ቁሳቁሶችን በመስጠት ምእመናን የበኩላቸውን እገዛ እንዲያበረክቱ ጠይቋል፡፡

 

‹‹ቤተመጽሐፍቱ ቅዳሜን ጨምሮ በሌሎቹም መደበኛ የሥራ ቀናት ለአንባቢያን አገልግሎት እየሰጠ ነው፤›› ያሉት  የቤተ መጻሕፍት አገልጋይ  አቶ ደጀኔ ፈጠነ፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ አንባቢያን በቤተ መጻሕፍቱ እየተጠቀሙ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ስለመርሐ ግብሩ ዓላማ የተጠየቁት አቶ ደጀኔ “ ቤተ መጻሕፍቱን በመጻሕፍት ዓይነትና ብዛት ክምችቱን ማሳደግ÷ አገልግሎቱን በኮምፒውተር የታገዘ÷ አስፈላጊ በሆኑ የመገልገያ መሣሪያዎች የተሟላ፤ ለተገልጋዮችም ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት የመርሐ ግብሩ ዓላማ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ለለጋሾች በቀላሉ መጻሕፍትን ገዝተው ማበርከት ይችሉ ዘንድ በማኅበሩ ሕንፃ ከተዘጋጀው ጊዜያዊ ሽያጭ በተጨማሪ አዲስ አበባ በሚገኙ የማኅበሩ ሱቁች የሽያጭና የመረከብ አገልግሎት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 17 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ በሚቆየዉ መርሐ ግብር በርካታ መጻሕፍት፣መጽሔቶችና ለቤተመጻሐፍት አገልግሎት የሚረዱ ኮምፒውተሮች፣ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ መደርደሪያዎችና ሌሎች አስፈላጊ መገልገያዎችን  ለማሰባሰብ ታቅዷል፡፡