abune gm 003

በዝቋላ ገዳም የተቀሰቀሰው እሳት ለማዳፈን ጥረት እየተደረገ ነው

የካቲት 26 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

abune gm 003ከማክሰኞ የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የተቀሰቀሰው እሳት በትናንትናው እለት ተባብሶ የነበረ ቢሆንም ወደ ሌላ ቦታ ሳይዛመት ከሸለቆው ውስጥ ለማዳፈን ጥረት የተደረገ መሆኑን የገዳሙ አበምኔት አባ ገብረ ማርያም ዛሬ ጠዋት በስልክ ገልጸዋል፡፡

በሸለቆው ውስጥ የተዛመተው እሳት ማኅበረ መነኮሳቱ፤ ምእመናንና የፖሊስ ኃይል ባደረጉት ርብርብ ከሸለቆው ሳይወጣ ለማቆም ተችሏል፡፡ ነገር ግን ከተዳፈነው እሳት ከፍተኛ ጭስ እየወጣ በመሆኑ እሳቱ እንዳይቀጣጠል ጥረት በማደረግ ላይ እንደሚገኙም አበምኔቱ ገልጸዋል፡፡

በገዳሙ ደን ላይ ለተከሰተው እሳት ቃጠሎ መንስኤ ከሰል በማክሰል ላይ በነበረ አንድ ግለሰብ እንደሆነ ከገዳሙ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡

ግለሰቡ በድብቅ ከሰል በማክሰል ላይ ሳለ እሳቱ ከቁጥጥሩ ውጪ በመሆኑ ሲገለገልበት የነበረውን አካፋና ሹራብ ጥሎ እንደተሰወረ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የካቲት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. የእሳቱን መንስኤ ለመጣራት በወንበር ቀበሌ ጽ/ቤት ከወረዳና ከዞን ከመጡ የፖሊስ ባለሥልጣናት ጋር በተደረገ ውይይት የግለሰቡ ማንነት ታውቋል ሲሉ በስብሰባው የተሳተፉ መነኮሳት ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ግለሰቡን ለመያዝ ክትትል እያደረገ ሲሆን፤ እሳቱ ዳግም እንዳይነሳም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፤፤