እንኳን ለዘመነ ዮሐንስ አደረሰን!

‹‹ምድርን ጎበኘኻት›› (መዝ.፷፬፥፱)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ጳጉሜን ፮፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

የዘመናት አስገኝ፣ የፍጥረታት ባለቤት፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ዓመታትን በቸርነቱ የሚያፈራርቅ፣ ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ  በቸርነቱ አሻግሮናልና ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን!

ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በዝማሬው የእግዚአብሔር ቸርነቱን፣ ምሕረቱን እንዲሁም ገበሬው ፈጣሪን አምኖ የዘራባትን ዘር ምድር በኪነ ጥበቡ እንዴት አድርጋ እንደምትመልስ፣ የዓመቱን ሰብል እግዚአብሔር እንደሚባርክ እንዲህ ሲል ገልጾታል፤ ‹‹…ምድርን ጎበኘኻት፤ አጠጣሃትም፤ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተሞላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ፤ እንዲሁ ታሰናዳለህና ትልሟንም ታረካለህ፤ ቦይዋን ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፤ ቡቃያዋንም ትባርካለህ፤ በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ፤ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል፤ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፤ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ፤ ማሰማሪያዎች መንጎችን ለበሱ፤ ሸለቆዎችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮሃሉ፤ ይዘምራሉም››  በማለት ያዘክረዋል፡፡ (መዝ.፷፬፥፱-፲፫)

እግዚአብሔር ኃጥአንንም ሆነ ጻድቃንን ሳይለይ በቸርነቱ ለሁሉ ወቅታትን እያፈራረቀ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ይሰጠናል፤ በክረምቱ ወራት ጠለ በረከቱን፣ ዝናመ ምሕረቱን አውርዶልን፣ ምድርን አለስልሶ፣ ችሮታውን ሳያጎድልብን ገበሬው ታምኖት የጣላትን ቅንጣት ፍሬ ከቅጠልነት ወደ አበባነት ቀይሮ፣ ፍሬ ለማፍራታቸው፣ ተስፋን መፈንጠቃቸውን አሳይቶናል፤ ስጦታው የማያልቅ ቸርነቱ የበዛ ጌታ ፍሬያቸውን እንመገብ ዘንድ ይፍቀድልን፡፡

አዲሱ ዓመት በክረምት ደፍርሶ፣ ይፈስ የነበረው ጅረት ጠርቶ ንጹሕ ሆኖ የሚንፎለፎልበት፣ በደመና ተሸፍኖ የነበረው ሰማይ ጠርቶ ፀሐይ የምትፈነጥቅበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፅዋት በጽጌያት ውበት የምታጌጥበት ወቅት (ወር) ነው፡፡ ተፈጥሮ በራሱ ልዩ የሆነ ለውጥ ይንጸባረቅበታል፤ ሕፃናት በዝማሬያቸው ‹‹አበባ አየሽ ወይ›› በማለት የተዘራው እህል ከቅጠልነት ፍሬ ለማፍራት  መቃረቡን፣ ወደ አበባነት መቀየሩን ያበሥራሉ፤ የፈጣሪን ድንቅ ስጦታ ቸርነት ይገልጣሉ፡፡ ይህን ሁሉ እንመለከት ዘንድ በዝናብ አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ፣  በነፋስ አሳድጎ ፍጥረቱን የሚመግብ እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሓ ለግሦ ከዘመን ዘመን አሻገረን! ካለፈው ዓመት ይህቺን ዓመት ጨምሮ ሰጠን! ምድር የተባልን እኛን ሰዎች በቸርነቱ ጎበኘን፤ ታዲያ ምን ያህሎቻችን የተዘራብንን ቃሉን ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ ለማፍራት ጣርን (ተጋን)! በልባችን እርሻ የፈሰሰብን ቃሉ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ በጎነት፣ ትሩፋት ፍሬን ያፈራ ዘንድ ለሠለሰ! (ምቹ ሆነ)! ምድር ጠለ በረከቱን ከፈጣሪ ተቀብላ፣ ድርቀቷን በልስላሴ፣ ባዶነቷን በጽጌያት ውበት፣ በአረንጓዴው ሰብል ለውጣ፣ አፍላጋት ጠርተው ሲፈሱባት፣ እንስሳቱ ለምለም ሣር ሲነጩባት፣ የሰው ልጆች ፍሬን ሲለቅሙባት፣ ተራራው ሸለቆው ችሮታ ፍቅሩን ሲመሰክሩ ይስተዋላል፤ የሰው ልጆችም የተዘራብንን ቃሉን በመንገድ ዳር ወድቆ ወፎች እንደለቀሙት፣ በእሾህ ተጥሎ እሾህ እንዳነቀው፣ በጭንጫ ወድቆ ፀሐይ እንዳጠወለገው ሳይሆን በለምለም የልባችን ሰብል ተዘርተው፣ አፍረተው ይገኙ ዘንድ ለቃሉ ምን ያህል ምቹ ሆንን!?

ዕድሜ ለንስሓ ዘመን ለፍስሓ የሰጠን መልካም እንድንሠራበት ነውና በመጪው ዘመን የትናንት ስሕተታችንን አርመን፣ የተጣላን ታርቀን፣ የበደልን ክሰን፣ ያልባሰበት የባሰበትን እየደገፈ፣ ያለው ለሌለው እያካፈለ ለመኖር ልናቅድ ይገባናል፤ ለምድራዊ ኑሯችን የምንተገብራቸውን እንደምናቅድ ለመንፈሳዊ ሕይወታችንም ማሰብ ተገቢ ነው፤ የዘመናት ጌታ፣ ብርሃንና ጨለማን ፣በጋና ክረምትን የሚያፈራርቅ፣ ዘመንን በዘመን የሚተካ፣ የሠራዊት ጌታ፣ የእስራኤል ቅዱስ ልዑል እግዚአብሔር ዘመነ ሉቃስን ፳፻፲፭ ዓ.ምን አሳልፎ ለዘመነ ዮሐንስ ፳፻፲፮ ዓ.ም አድርሶናልና ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን! እክለ በረከቱን ለእኛ የሚያድል ፈጣሪ ዘመኑን የፍቅር፣ የሰላም፣ የምሕረት ዘመን ያድርግልን!  የተሰጠንን ዘመን መልካም ልንሠራበት እንነሣ! በስንፍና ያሳለፍነው ጊዜ ይብቃን! በአዲስ ዘመን በአዲስ ዕቅድ፣ በአዲስ መንፈስ ለሥራ እንነሣ! ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ እንዲህ ይለናልና፤ ‹‹…የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለ ልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና፡፡›› (፩ጴጥ.፬፥፫)

የዕድሜያችን ቀመር (አቆጣጠር) እየተደመረ የሚቀነስ መሆኑን ሳንዘነጋ በምድር የእንግድነት ኑሮአችን ከሞት በኋላ ላለው ሕይወት እንሚበጅን መልካም ምግባራትን እንሥራበት፤ ትናንት በክረምቱ ወራት ቀኑ ጨልሞ፣ ጨፍግጎ እንደ ልብ ከቦታ ቦታ እንንቀሳቀስ ዘንድ፣ ባቀድነው ሰዓት ወጥተን በፈለግነው ጊዜ ለመግባት ስንቸገር ነበር፤ አሁን ግን አለፈ፤ ጎርፉ ቀረ፤ ደመናው ተገፈፈ፤ ቅዝቃዜው ቀነሰ፤ የማያልፍ የለምና አዲስ ወቅት ብሩህ ወር ተተካ፤ ይህ እንደሚሆን በልባችን ሙሉ ተስፋ ሰንቀን ነበር፤ ምኞት ብቻ ሳይሆን ይዘን የነበረው መተማመኛ የሚገኝበት ተስፋ ነው! በሕይወታችንም እንዲሁ የገጠመን ነገር ሁሉ ያልፋል፤ የጨለመው ይነጋል፤ የራቀው ይቀርባል፤ የደፈረሰው ይጠራል፤ የችግሩን አቀበት ወጥተን እንደጨረስን ከበስተጀርባው ያለውን ለምለም መስክ እናገኛለንና በፈጣሪ ተስፋን እናድርግ፡፡

በአዲስ ዓመት፣ በአዲስ ዕቅድ፣ በአዲስ ሰብእና፣ በአዲስ መንፈስ ለመኖር እናቅድ፤ ተስፋችን እግዚአብሔር ነውና! ግን ይህ ሁሉ ይከወን ዘንድ መንገዳችን ከመንገዱ፣ ጉዟችን እንደ ፍቃዱ ይሆን ዘንድ ከእርሱ እንድንማር ነግሮናልና ትሕትናን፣ ፍቅርንና ይቅር ባይነትን ከእርሱ እንማር! መልካም ዘመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!