በአዲስ ዓመት አዲስ ሕይወት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹እነሆሉን አዲስ አደርጋለሁአዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፡፡ ባሕርም ወደ ፊት የለም›› በማለት እንደ ተናገረው (ራእ. ፳፩፥፩-፭) ዘመን እያለፈ አዲስ ዘመን ይተካል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በዕድሜ ላይ ዕድሜን እየጨመረ፣ ዘመናትን እያፈራረቀ በየጊዜያቱ አዲስ ዓመትን ያመጣልናል፡፡ አሁንም በእርሱ ቸርነት ለ፳፻፲ ዓመተ ምሕረት ደርሰናል፡፡ እኛም ዘመን በመጣ ቊጥር ‹‹እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!›› እንባባላለን፡፡ ስለ ትናንትና እንጂ ስለ ነገ ባናውቅም እስከ ዛሬ ድረስ በመቆየታችንም እንደሰታለን፡፡ ነገን በተስፋ ለሚጠባበቅ ሰው በእውነትም ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ በጣም ያስደስታል፡፡ ነገር ግን ያለፈውን ዓመት ስንዋሽ፣ ስንሰርቅ፣ ስንዘሙት፣ ስንጣላ፣ ስንተማማ፣ ስንደባደብ፣ ስንሰክር አሳልፈን ከኾነ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!›› የሚለው ቃል ርግማን ይኾንብናል፡፡

ስለ ተለወጠው ዘመን ሳይኾን ስላልተቀየረው ሰብእናችን፤ ስላልተለወጠው ማንነታችን፤ ስላልታደሰው ሥጋችን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በኀጢአት እየኖሩ ዐውደ ዓመትን ማክበር ራስን ያለ ለውጥ እንዲቀጥል ማበረታታት ነውና ከምንቀበለው ዘመን ይልቅ መጪውን ዘመን ለንስሐ ለማድረግ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ያሳለፍነውን የኀጢአት ጊዜ እያሰብን እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀንን እግዚአብሔርን እያመሰገንን ሕይወታችንን በጽድቅ ልናድስ ይገባናል፡፡ በንስሐ ባልታደሰ ሕይወታችን በዕድሜ ላይ ዕድሜ ቢጨመርልን ለእኛም ለዘመኑም አይበጅምና፡፡ ‹‹ባረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፡፡ መቀደዱም የባሰ ይኾናል›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል (ማቴ. ፱፥፲፯)፡፡

ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር እየኖርን ዘመንን ብቻ የምንቈጥር ከኾነ ሕይወታችንን ከሰብአዊነት ክብር ብሎም ከክርስቲያናዊ ሕይወት በታች እናደርገዋለን፡፡ ራስን ከጊዜ ጋር ማወዳደር መቻል ክርስቲያናዊ ሓላፊነት ነው፡፡ ይኸውም ጊዜ ሳይቀድመኝ ልቅደመው ብሎ ማሰብ መቻል ነው፡፡ በአሮጌ ሕይወት ውስጥ ኾነን ዓመቱን አዲስ ከማለት ይልቅ ከኀጢአት ወደ ጽድቅ በመሸጋገር ራሳችንን በጽድቅ ሥራ ማደስ ይበልጣል፡፡ ስለዚህም ያለፈውን ዓመት በምን ኹኔታ አሳለፍሁት? በመጭው ዓመትስ ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል? በሚል ጥያቄ መነሻነት በአዲሱ ዓመት መንፈሳዊ ዕቅድ ሊኖረን ይገባል፡፡

በመሠረቱ ዘመን ራሱን እየደገመ ይሔዳል እንጂ አዲስ ዓመት የለም፡፡ ሰዓታትም ዕለታትም እየተመላለሱ በድግግሞሽ ይመጣሉ እንጂ ከዚህ በፊት ያልነበረ ሰዓት ወይም ቀን ወይም ደግሞ ወር አለዚያም ዓመት የለም፡፡ ወርኀ መስከረምም ለብዙ ሺሕ ዓመታት ራሱን እየደገመ በየዓመቱ አዲስ ሲባል ይኖራል እንጂ ሌላ መስከረም የለም፡፡ ‹‹የኾነው ነገር እርሱ የሚኾን ነው፤ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፡፡ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ ማንምእነሆ ይህ ነገር አዲስ ነውይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል›› እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን (መክ. ፩፥፱-፲)፡፡ ዘመን አዲስ የሚባለው እኛ ሰዎች (ክርስቲያኖች) ሕይወታችንን በጽድቅ ስናድስ ነው፡፡ ያለ መልካም ሥራ የሚመጣ ዓመት፤ ከክፉ ግብር ጋር የምንቀበለው ዘመን አዲስ ሊባልም፣ ሊኾንም አይችልም፡፡ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት በመልካም ሥራ ሲዳብር ግን መጭው ዘመን ብቻ ሳይኾን ያለፈው ዘመንም አዲስ ነው፡፡

በዘመናት ዑደት ውስጥ ሕይወታቸውን በሙሉ በጽድቅ የሚያሳልፉ ወይም ኀጢአታቸውን በንስሐ የሚያጸዱ ብዙ ጻድቃን ምእመናን ቢኖሩም ሰውነታችንን ጥለን በክፉ ምግባር እየኖርን  ዕድሜያችንን የምንቈጥር ኃጥኣን ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ስለኾነም በኀጢአት ያሳለፍነውን ዘመን በማሰብ መጭውን ዘመን ለመልካም ሥነ ምግባር ልናውለው፤ አንድም ለንስሐ መግቢያ ልናደርገው ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለ ልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት፣ በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል›› በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ አስተምሮናልና (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፫)፡፡ እናም ለአዲስ ዓመት አዲስ ሕይወት እንደሚያስፈልግ በመረዳት ራሳችንን በንስሐ ሳሙና አሳጥበን በንጽሕና ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ታጠቡ፤ ሰውነታችሁንም አንጹ፡፡ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፡፡ ክፉ ማድረግን ተዉ … ልባችሁን አንጹ፤ ሰውነታችሁንም ንጹሕ አድርጉ›› ተብለን ታዝዘናልና (ኢሳ.፩፥፲፮፤ መጽሐፈ ኪዳን)፡፡

በአጠቃላይ በዚህ አዲስ ዓመት ከክፉ ምግባር ዅሉ ተለይተን፣ ከዚህ በፊት በሠራነው ኀጢአታችን ንስሐ ገብተን፣ ለወደፊቱ በጽድቅ ሥራ ኖረን እግዚአብሔርን ልናስደስት ይገባናል፡፡ ‹‹ይደልወነ ከመ ንግበር በዓለ ዐቢየ በኵሉ ንጽሕና እስመ ይእቲ ዕለት ቅድስት ወቡርክት፡፡ ወንርኀቅ እምኵሉ ምግባራት እኩያት፡፡ ወንወጥን ምግባራተ ሠናያተ ወሐዲሳተ በዘቦቶን ይሠምር እግዚአብሔር፤ አሁንም በፍጹም ንጽሕና ታላቅ በዓልን አድርገን ልናከብር ይገባናል፡፡ ይህቺ ዕለት ከሌሎች ዕለታት ተለይታ የተባረከች ናትና፡፡ ከክፉ ሥራዎችም ተለይተን እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝባቸውን አዳዲስ የኾኑ በጎ ሥራዎችን እንሥራ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መጽሐፈ ስንክሳር፣ መስከረም ፩ ቀን)፡፡

የተወደዳችሁ ምእመናን! ‹‹ዐዘቅቱ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ዅሉ ዝቅ ይበል፡፡ ጠማማውም የቀና መንገድ ይኹን፡፡ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይኹን፡፡ ሥጋም የለበሰ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ›› ተብሎ እንደ ተነገረው (ሉቃ. ፫፥፫-፮) በኑፋቄ የጎደጎደው ሰውነታችንን በቃለ እግዚአብሔር በመሙላት፤ በትዕቢት የደነደነውን ተራራውን ልቡናችንን በትሕትና በማስገዛት፤ በክፋት የተጣመመው አእምሯችንን በቅንነት በማስጓዝ፤ በኀጢአት የሻከረውን ልቡናችንን በንስሐ በማስተካከል አዲሱን ዓመት የመልካም ምግባር ዘመን እናድርገው፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትኾኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ›› በማለት እንዳዘዘን (፩ኛ ቆሮ.፭፥፯)፣ በኀጢአት እርሾ የተበከለውን ሰውነታችንን በጽድቅ ሕይወት እናድሰው፡፡ በአዲሱ ዓመት በክርስቲያናዊ ምግባር መኖር ከቻልን ከጊዜ ጋር የሚጣጣም አዲስ ሕይወት ይኖረናል ማለት ነው፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም የደስታችን መጠን በልክ መኾን አለበት፡፡ አሁን አሁን የበዓሉን መንፈሳዊነት የሚያጠፉ እንደ ከልክ በላይ መመገብና መመጣት፣ መስከር፣ መጨፈር፣ መጮኽ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የውጭ ዓለም የባህል ወረራዎች በየከተሞች ተስፋፍተዋል፡፡ እነዚህ ሰይጣናዊ ድርጊቶች ወጣቱን ትውልድ ለጥፋት የሚጋብዙ የኀጢአት መሣሪያዎች ናቸውና ለራሳችንም ለአገራችንም ህልውና ሲባል አጥብቀን ልንከላከላቸው ይገባል፡፡ አዲሱን ዓመት ለማየት እንደ ጓጉ በልዩ ልዩ ምክንያት ለመድረስ ያልታደሉትን፤ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው በየጠበሉና በየሆስፒታሉ የሚሰቃዩትን፤ በጦርነት፣ በረሃብ፣ በስደት፣ ወዘተ. በመሳሰሉ ችግሮች የሚጨነቁትን ወገኖቻችንን በማሰብና መንፈሳዊ ትውፊቱን የጠበቀ አከባበርን መሠረት በማድረግ ዓመት በዓሉን ማክበር ይጠበቅብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡