በቃጠሎ የወደመውን ቤተ ክርሰቲያን ለመገንባት እንቅስቃሴ ተጀመረ

 

በእንዳላ ደምስስ

ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም በቃጠሎ የወደመውን የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ሊቀ ኅሩያን መ/ር ወጋየሁ ደምሴ የባሌ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ ገለጹ፡፡

“በቃጠሎው ቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ ለሙሉ ወድሞ ነው የደረስነው፡፡ ሕዝቡም ከፍተኛ ሐዘን ነው የተሰማው፡፡ ሁላችንም ልባችን ተሰብሮ በዕንባ ስንራጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ አልቅሶ ብቻ አልተበተነም፡፡ዕንባውን አብሶ ገንዘብ የማሰባሰቡን ሥራ በመጀመር የመፍትሔ እርምጃ ነው የወሰደው፡፡” ሲሉ የገለጹት የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ናቸው፡፡ሀገረ ስብከቱ ካህናቱን፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትን፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ተወካዮችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በማሰባሰብ ዘጠኝ አባላት ያሉት የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ በማዋቀር ቤተ ክርስቲያኑን በድጋሚ ለመገንባት ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራው መጀመሩንና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ማሰባበሰብ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

ከገንዘብ በተጨማሪም ምእመናን የአንገት ሐብላቻውንና የጣት ቀለበታቸውን በመስጠት፣ እናቶች ከመቀነታቸው እየፈቱ በመንፈሳዊ ስሜትና ቁጭት አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ማበርከታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

ሙስሊሙ ኅብረተሰብም በቤተ ክርሰቲያኑ መቃጠል ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማውና በቦታው በመገኘት ገንዘብ በመለገስ፣ እንዲሁም የግንባታ እቃዎችን ለመስጠት ቃል በመግባት መሳተፋቸውን፣ ቤተ ክርስቲያኑን ለማሠራትም በመስጊድ ውስጥ ሙስሊሙን በማስተባበር ገንዘብ ለማሰባበስብ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ዋና ጸሐፊ ተናግረዋል፡፡

“በዛሬው ውሏችንም ለተቋቋመው የሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ እወቅና ለመስጠት ሰበካ ጉባኤው ለወረዳው ቤተ ክህነት፣ የወረዳ ቤተ ክህነቱም ለሀገረ ስብከቱ ደረጃውን ጠብቆ በደብዳቤ በመጠየቅ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡” ያሉት ሊቀ ኅሩያን መ/ር ወጋየሁ የባንክ ሒሳብ (አካውንት) በመክፈትም ሕጋዊነት ባለው አሠራር ገቢ የማሰባሰብ ሂደቱ እንደቀጠለ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎትን በተመለከተም ቤተ ክርስቲያኑ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ስላለው ከሰበካ ጉባኤውና ከሕንፃ አሰሪ ኮሚቴው ጋር በመመካከር አዳራሹን በማመቻቸት ሙሉ የቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት ማለትም ኪዳንና ቅዳሴ ሳይቋረጥ መቀጠሉንና የቃጠሎውን መንስኤ በተመለከተም የሕግ አካላት እያጣሩ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡