DSC00379

በስልጤና ሀድያ ጉራጌ ሀገረ ስብከት የጋራሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በወረዳው ፓሊስ አባላት እንዲፈርስ መደረጉ ተገለጠ፡፡

ኅዳር 19/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባዬ

•    ቤተ ክርስቲያኑ የፈረሰው እኩለ ሌሊት እንደሆነም ታውቋል፡፡
•    የስልጢ 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎች በቤተ ክርስቲያኑ መፍረስ እንዲተባበሩ እየተቀሰቀሱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስልጤና ሀድያ ሀገረ ስብከት በስልጤ የጋራሬ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 15 ቀን 2004 ዓ.ም ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ እኩለ ሌሊት ላይ በወረዳው የፓሊስ አባላት የመፍረስ አደጋ እንደተጣለበት ከክልሉ የደረሰን ማስረጃ አረጋገጠ፡፡

በስልጤ ዞን በስልጢ ወረዳ በቆቶ ባለሦ ቀበሌ በቆቶ መንደር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የይዞታ ቦታው በሰነድ እንዲረጋገጥ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ለግብርና ገጠር ልማት ቢሮ ለተፈጥሮ ሀብትና የገጠር መሬት አስተዳደር ዘርፍ ባቀረበው ጥያቄ አግባብነት ያለው የመንግሥት የሥልጣን አካል በቀን 15/04/2003 ዓ.ም የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዱን ለደብሩ ሰበካ ጉባኤ መስጠቱን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡

DSC00379

በተሰጠው የይዞታ ቦታ ተደጋጋሚ የሆነ ክስ ይቀርብ እንደነበር የሚገልጡት የወረዳው ምእመናን የተፈቀደው ቦታ ለጥምቀተ ባሕር በመሆን ማንኛውም የእምነት ተከታይ አምልኮውን ሊፈጽም እንደሚችል በተቃራኒ ወገን አቤቱታዎች መቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም ከወረዳው ፍርድ ቤት እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድረስ ጉዳዩ በተደጋጋሚ ታይቶ የቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት በተፈቀደለት ቦታ መንፈሳዊ ሥራውን እንዲቀጥል በመዝገብ ቁጥር 05681 የተወሰነውን ውሳኔ በመጥቀስ የወረዳው ፍርድ ቤት በቀን 13/12/2003 ዓ.ም ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ደግሞ በቁጥር 16/507/23/205 በቀን 13/04/2003 ዓ.ም ባስተላለፈው ትእዛዝ አስታወቋል፡፡

የሕግ አግባብ ባለው መሥሪያ ቤት ተፈቅዶ መሠረቱ ተቀምጦ የተሠራው ቤተ ክርስቲያን ድንገት በመፍረሱ የተደናገጡት የስልጢ ምእመናን ጉዳዩን ለሚመለከተው የበላይ አካል ለማቅረብ ወደ ሐዋሳ አስተዳደር ጽ/ቤት በቀን 18/03/2004 ዓ.ም ጉዞአቸውን አቅንተዋል፡፡ በእለቱም የክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ቢሮ የምእመናኑ አቤቱታ አግባብነት ያለው በመሆኑ አጣሪ ኃይል ወደ ቦታው እንደሚላክ ምላሽ እንደተሰጣቸው ተገልጧል፡፡

ኅዳር 19 ቀን 2004 ዓ.ም የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው በስልጢ ከተማ ጥቂት አክራሪ ሙስሊሞች በሙስሊምና በክርስቲያኑ መካከል ግጭት እንዲፈጠር ቅስቀሳ እያደረጉ ነው፡፡ ከዚህም በተያያዘ በስልጢ ከተማ 1ኛ እና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ቤተ ክርስቲያኑ እንዲፈርስ የሚደረገውን ተግባር እንዲፈጽሙ መቀስቀሳቸውንና ተማሪዎቹ ተሰባስበው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመሔድ ነዳጅ ጨምረው ቤተ ክርስቲያኑን ሙሉ በሙሉ ማቃጠላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የስልጢ ምእመናን በሕግ ተፈቅዶ በተሰጣቸው ቦታ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው መገልገል ሊጀምሩ በተዘጋጁበት ወቅት ሕጋዊ ነኝ በሚል የፖሊስ አካል በመንፈቀ ሌሊት እንዲፈርስ መደረጉና በሕገ ወጥ ወጣቶች እንዲቃጠል መደረጉ እንዳሳዘናቸው አብራርተዋል፡፡

ቀጣዩ ሒደት እንደደረሰን የምናሳውቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡