ስብከተ ወንጌል የልማት መሠረት

ሐምሌ ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሒዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል በአምላካዊ ቃሉ ያዘዘውን መሠረት በማድረግና የቅዱሳን ሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ሰባክያንን እያስተማረች በየቦታው ስታሰማራ ኖራለች፤ ወደፊትም ይህንን ተልእኮዋን ትቀጥላለች፡፡

ምክንያቱም ስብከተ ወንጌል ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተማር ብቻ ሳይኾን የሰውን አእምሮ ለማልማት (መልካም አስተሳሰብን ለመገንባት) የሚያስችል ዋነኛው የቤተ ክርስቲያን መሣሪያ ነውና፡፡ ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ከየመጻሕፍት ቤቱና ከመንፈሳውያን ኮሌጆች በየጊዜው መምህራንን እያስመረቀች ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የምታሰልፋቸው፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማስፈጸም የተቋቋመው ማኅበረ ቅዱሳንም በየግቢ ጉባኤያቱ ትምህርተ ሃይማኖትን ከሚያስተምራቸው ወንድሞችና እኅቶች በተጨማሪ ከአባቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር በልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ በርካታ ሰባክያንን በየቋንቋው እያሠለጠነና በአባቶች ቡራኬ እያስመረቀ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሠማሩ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ማኅበሩ በዚህ ዓመትም ይህንን ተልእኮውን በመቀጠል አሠልጥኖ ያስመረቃቸው ሰባክያነ ወንጌል ከመኖራቸውም ባሻገር በአሁኑ ሰዓት እየሠለጠኑ የሚገኙ ወንድሞችም በርካታ ናቸው፡፡

ለዚህም በአዳማ ከተማ በአፋን ኦሮሞ ሠልጥነው የተመረቁ ሰባክያን፤ እንደዚሁም በአዲስ አበባና በሐሮ እየሠለጠኑ የሚገኙ ወንድሞች ማስረጃዎች ናቸው፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ከበጎ አድራዎች በተገኘ ድጋፍ ከልዩ ልዩ ገጠራማ ሥፍራዎች የተውጣጡ ፳፰ ሰባክያንን በአፋን ኦሮሞ አሠልጥኖ ሐምሌ ፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም አስመርቋል፡፡

Publication1

በምረቃ ሥርዓቱም የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት፣ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችና የየአድባራቱ አገልጋይ ካህናት፣ የአገር ሽማግሎች፣ በጎ አድራጊ ምእመናንና የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ተገኝተዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ትምህርተ ወንጌልና ዝማሬ የቀረበ ሲኾን፣ ምሩቃኑ በማእከሉ የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የነጠላ ስጦታ ከአባቶች እጅ ተቀብለዋል፡፡ እንደዚሁም ምሩቃኑ ሥልጠናውን እንዲያገኙ ላደረጓቸው የማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ልዩ ልዩ ስጦታ አበርክተዋል፡፡

ለሠልጣኞቹ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎችና የዝግጅት ክፍላችን አባላት በተገኙበት ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለሠልጣኞቹ የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል የተደረገ ሲኾን፣ በዕለቱ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢኾነኝ፡- “ይህንን ሥልጠና ካጠናቀቃችሁ በኋላ ስብከተ ወንጌል መስጠት ብቻ ሳይኾን የአብነት ትምህርት በመማር ሥልጣነ ክህነት ተቀብላችሁ የሚያጠምቃቸውና ቀድሶ የሚያቈርባቸው ካህን ላላገኙ ወገኖቻችን ልትደርሱላቸው ይገባል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሰይፈ ዓለማየሁ በበኩላቸው፡- “የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በቃል ብቻ ሳይኾን በሕይወትም የሚሰበክ ተልእኮ መኾኑን ሳትዘነጉ በምትሔዱበት ስፍራ ኹሉ ለምታስተምሯቸው ምእመናንም ኾነ ለሌሎች ወጣቶች መልካም ምሳሌ ልትኾኑ ይገባል” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

የአዳማ ማእከል ሰብሳቢ መ/ር ጌትነት ዐሥራት ደግሞ ሥልጠናው ሌሊትና ቀን ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ከትምህርተ ሃይማኖት በተጨማሪ የሥራ አመራር፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ የስብከት ዘዴ፣ ወቅታዊ ኹኔታ፣ አገልግሎት፣ የሕይወት ተሞክሮና ተዛማጅ መርሐ ግብራት በሥልጠናው መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰብሳቢው በመጨረሻም ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አባቶችና በጎ አድራጊ ምእመናን በማእከሉ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ከ፳፫ ጠረፋማ አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ሰባክያንን በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡

የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብሩ አስተባባሪ አቶ ጌትነት ወርቁ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጹት ከሰኔ ፳፮ ቀን እስከ ሐምሌ ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለአንድ ወር በሚቆየው በዚህ ሥልጠና የሚሳተፉ ሠልጣኞች ብዛት ፻፴ ሲኾን፣ ከእነዚህ መካከል ፵ዎቹ የዓቅም ማጎልበቻ፤ ፺ዎቹ ደግሞ የስብከተ ወንጌል ሥልጠና የሚወስዱ ወንድሞች ናቸው፡፡

ሥልጠናው የዓቅም ማጎልበቻ እና የስብከተ ወንጌል ሥልጠና በሚሉ አርእስት ለሁለት ተከፍሎ የሚሰጥ ሲኾን፣ የዓቅም ማጎልበቻው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በለቡ አቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት፤ የስብከተ ወንጌል ሥልጠናው ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጪ ወረዳ ቤተ ክህነት በሐሮ ደብረ ጽጌ ቅዱስ በዓለ ወልድ ወቅዱስ ዑራኤል ገዳም የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመሰጠት ላይ ነው፡፡

የዓቅም ማጎልበቻ ሥልጠናው ከዚህ በፊት የስብከተ ወንጌል ሥልጠና ወስደው በየቋንቋቸው ሲሰብኩ ለነበሩ ወንድሞች እንደተዘጋጀና ዓላማውም ሠልጣኞቹ እንደ እነርሱ ያሉ ብዙ ሰባክያነ ወንጌልን እንዲያፈሩ፤ እንደዚሁም የተጠመቁ ወገኖችን በማጽናት በየቦታው የጽዋ ማኅበራትንና ሰንበት ት/ቤቶችን እንዲመሠርቱ፤ የተመሠረቱትንም እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ተዘጋጀ፤ የስብከተ ወንጌል ሥልጠናው ደግሞ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌልን ለማፍራት የሚሠጥ ሥልጠና እንደ ኾነ አቶ ጌትነት አስታውቀዋል፡፡

ለሠልጣኞቹም የሶዶ ዳጪ ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህንና ሠራተኞች፣ የገዳሙ አበ ምኔትና ካህናት፣ የወረዳው አስተዳዳሪና ሠራተኞች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ልዩ ልዩ ክፍሎች አገልጋዮችና በጎ አድራጊ ምእመናን በተገኙበት ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሐሮ ደብረ ጽጌ ቅዱስ በዓለ ወልድ ወቅዱስ ዑራኤል ገዳም የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በዕለቱ በቦታው ተገኝተን ቃለ መጠይቅ ያደርግንላቸው የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህን መልአከ ኃይል ቀሲስ ጀምበር ደበላ “ሥልጠናው በሐሮ ገዳም መሰጠቱ የአካባቢውን ምእመናን ከእኛስ ምን ይጠበቃል? እንዲሉና ወረዳ ቤተ ክህነቱም ለተሻለ አገልግሎት እንዲተጋ ያደርገዋል” ካሉ በኋላ ሥልጠናው እስኪጠናቀቅ ድረስ ዓቅማቸው በሚፈቅደው ኹሉ ለሠልጣኞቹ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

የገዳሙ አስተዳዳሪ ሊቀ ጉባኤ አባ ኤልያስ ወልደ ሥላሴ ደግሞ “ሠልጣኞቹ ከ፳፫ አህጉረ ስብከት የተውጣጡ የልዩ ልዩ ብሔረሰብ አባላት ናቸው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ሐሮ ላይ ተሰብስባለች ማለት ይቻላል፡፡ እኛም በሠልጣኞቹ ፊት ስንገኝ በአበባ መካከል ላይ የቆምን ያህል ይሰማናል” ብለዋል፡፡ አያይዘውም “እግዚአብሔር ማኅበሩን ይጠብቅልን” ሲሉ ማኅበረ ቅዱሳንን መርቀዋል፡፡

የሶዶ ዳጪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ባጫ ኮምቦሌ በበኩላቸው “እንደዚህ ዓይነት ሥልጠና በእኛ ቀበሌ መሰጠቱ ለወረዳው ብቻ ሳይኾን ለአገር ሰላምና ልማትም የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት ሰላም ነው፤ ሃይማኖት ልማት ነው፡፡ ዛሬ የተካሔደው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም አንዱ የልማት ማሳያ ነው” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከአቀባበሉ ሥርዓት ቀጥሎም በቢትወደድ ባሕሩ አብርሃም አስተባባሪነት ጥሪ በተደረገላቸው እንግዶችና በሠልጣኞቹ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡ የችግኝ ተከላው ዓላማም ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ብቻ ሳይኾን ልማትንም እንደምታስተምር ለማመልከት መኾኑን ቢትወደድ ባሕሩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ለዚህ ሥልጠና ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አባቶች፤ ከአራት መቶ ሺሕ ብር በላይ በማውጣት የሥልጠናውን ሙሉ ወጪ ለሸፈኑት አንድ በጎ አድራጊ ወንድም፤ እንደዚሁም በአዳራሽ፣ በቁሳቁስ አቅርቦትና በመስተንግዶ በማገዝ ላይ ለሚገኙ ምእመናን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያው አስተባባሪ ማኅበሩን በመወከል ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡