ሰኔ ሚካኤል – የመጀመርያ ክፍል  

ከመጽሐፈ ስንክሳር

ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፱ .

አንድ አምላክ በኾነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሰኔ ዐሥራ ሁለት በዚች ዕለት የከበረ የመላእክት አለቃ የመልአኩ የሚካኤል የመታሰቢያውን በዓል ያከብራሉ፡፡ የሚያከብሩበትም ምክንያት እንዲህ ነው፤

እስክንድርያ በምትባል ከተማ አክላወበጥራ የተባለች ንግሥት የንጉሥ በጥሊሞስ ልጅ ዙሐል በሚባል ኮከብ ስም ያሠራችው ታላቅ ምኵራብ ነበረና በየዓመቱ ሰኔ በባተ በዐሥራ ሁለት ቀን በዚያ ምኵራብ ሕዝቡ ተሰብስቦ ታላቅ በዓል ያደርጉ ነበር፡፡ በዚያም ምኵራብ ውስጥ ዙሐል የሚሉት ታላቅ የነሐስ ጣዖት ነበረና በዓሉ በሚከበርበት ዕለት ብዙ ፍሪዳዎችን ያርዱለት ነበር፡፡

አባ እለእስክንድሮስ እስከተሾመበት ዘመን ድረስ ለዚያ ጣዖት እንዲህ ሲያደርጉ ኖሩ፡፡ ይኸውም ሦስት መቶ ዓመተ ምሕረት ተፈጽሞ በአራተኛው ምዕት ውስጥ ነበር፡፡ አባ እለእስክንድሮስ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ፣ ጻድቅ ቆስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት ስለ ተስፋፋች ያን ጣዖት ሊሠብረው ወድዶ ሳለ ጐስቋሎች ሰዎች ከለከሉት፡፡ እንዲህም አሉት፤ ‹‹እኛ በዚህ ቦታ ይህን በዓል ማክበርን ለምደናል፡፡ እነሆ ከአንተ በፊት ዐሥራ ስምንት ሊቃነ ጳጳሳት አልፈዋል፤ ይህን ልማዳችንንም አልለወጡብንም፡፡››

አባ እለእስክንድሮስ ግን ገሠፃቸው፤ አስተማራቸው፡፡ ስሕተታቸውንም በመግለጥ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹ይህ የማይጎዳና የማይጠቅም ነው፡፡ እርሱንም የሚያመልክ ሰይጣናትን ያመልካቸዋል፡፡ ምክሬንስ ብትሰሙ ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ ይህን በዓል እሠራላችኋለሁ፤ ይኸውም ቱን እንድንሰብረው፣ ምኵራቡንም እንድንባርከውና በከበረ መልአክ በመላእክት አለቃ በሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አድርገን እንድንሰይመው ነው፡፡ እኛም ይህን ታላቅ በዓል እንሠራለን፡፡ የሚታረዱትም ላሞችና በጎች ለድኆችና ለጦም አዳራዎች፣ ለችግረኞችም በከበረው መልአክ ስም ምግብ ይኹኑ፡፡ እርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነት ያለው ስለ ኾነ ስለ እኛ ይማልዳልና፡፡›› ይህንንም ብሎ በዚህ በጎ ምክር አስወደዳቸው፤ እነርሱም ታዘዙለት፡፡

ከዚህም በኋላ ያንን ምኵራብ አድሰው በዚህ የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ስም ቤተ ክርስቲያን አደረጉት፡፡ በዚችም ዕለት አከበሩዋት፡፡ እርሷም የታወቀች ናት፡፡ እስላሞችም እስከ ነጉሡበት ዘመን ኑራ ከዚያ በኋላ አፈረሱዋት፡፡ ይህም በዓል ተሠራ፤ እስከ ዛሬም ጸንቶ ይኖራል፡፡

ዳግመኛም በዚች ዕለት እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን በነገዱ ውስጥ በመላእክት ዅሉ ላይ በብዙ ክብር ሾመው፡፡ ይህም የከበረ መልአክ ክብር ይግባውና በጌታችን ፊት ስለ ሰው ልጆችና ስለ ፍጥረትም ዅሉ ይለምናል፤ ይማልዳልም፡፡ የዚህ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተአምራቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነርሱም አንዱ ይህ ነው፤

እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም የከበረ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ይልቁንም በሰኔ እና በኅዳር ወር አብልጦ ያከብር ነበር፡፡ በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፡፡ ይህን እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የሚካኤልን በዓል በሚያደርግበት ጊዜ ይጠላውና ያቃልለው ነበር፡፡ ለድኆች ስለ መራራቱም ይዘባበትበት ነበረ፡፡ የሕይወቱ ዘመንም ተፈጽሞ የሚሞትበትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ የክቡር መልአክ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ታደርግ ዘንድ፣ ምጽዋት ሰጭም ትኾን ዘንድ ሚስቱን አዘዛት፡፡ ከዚህም በኋላ ዐረፈና ገንዘው ቀበሩት፡፡

ሚስቱም ፀንሳ ነበረች፡፡ የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ ምጥ ያዛት፡፡ በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሳለችም እንዲህ ብላ ጸለየች፤ ‹‹የእግዚአብሔር መልአኩ ሆይ ራራልኝ፡፡ በእርሱ ዘንድ ባለሟልነት አለህና፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኔ ለምንልኝ፡፡›› ይህንንም በአለች ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ፡፡ ከችግርም ዳነች፤ መልአኩ ውብ የኾነ ወንድ ልጅንም ወለደች፡፡ የእግዚአብሔርም መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው፤ ‹‹ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለ ጠጋ ገንዘብና ሀብት፣ ጥሪቱንም ይህ ሕፃን እንዲወርስ እግዚአብሔር አዝዟል፡፡››

ባለ ጠጋውም በቤቱ፣ በዐልጋው ላይ ሳለ ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ፡፡ ይህንን በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ደረሰበት፡፡ ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ክብር ይግባውና ጌታ ይጠብቀው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ያ ባለጠጋ ምክንያት አዘጋጅቶ ‹‹የሚያገለግለኝ ልጅ ይኾነኝ ዘንድ ልጅሽን ስጪኝ፡፡ እኔም እየመገብኹና እያለበስኹ አሳድገዋለሁ፡፡ ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ፤›› አላት፡፡ ይህንንም ነገር ከባለጠጋው በሰማች ጊዜ ስለ ችግሯ እጅግ ደስ አላት፡፡ ልጅዋንም ሰጠችው፡፡ እርሱም ሃያውን ወቄት ወርቅ ሰጣት፡፡ ልጅዋንም ወሰደው፡፡ የምሻው ተፈጸመልኝ ብሎ ደስ አለው፡፡

ከዚህም በኋላ በልጁ ቁመት ልክ ሣጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አስገብቶ ዘጋበት፡፡ እስከ ባሕርም ተሸክመው ወስደው በባሕር ጣሉት፡፡ ክብር ይግባውና በጌታችን ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሠጥም ከዚያች አገር የሃያ ቀን መንገድ ያህል ርቃ ወደምትገኝ ወደ አንዲት አገር ወደብ እስከሚደርስ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ፡፡ በባሕሩም አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበርና ሣጥኑን በውኃ ላይ ተንሳፎ አየው፡፡ እርሱም ከባሕሩ አውጥቶ ወደ ቤቱ ወሰደው፡፡ ይህን ሣጥን እንዴት እንደሚከፍተው ያስብ ጀመረ፡፡ ይህንም ሲያስብ ወደ ባሕሩ ይሔድ ዘንድ ጌታችን በልቡናው ሐሳብ አሳደረበት፡፡ ወዲያውኑም ተነሥቶ ወደ ባሕሩ ሔደና አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰው አገኘ፡፡

ዓሣ አጥማጁንም ‹‹መረብህን በኔ ስም ጣል፡፡ ለሚያዘውም ዓሣ ዋጋውን እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡ አጥማጁም እንዳለው አደረገ፡፡ ያን ጊዜም ታላቅ ዓሣ ተያዘ፡፡ ዋጋውንም ይዞ ወደ ቤቱ ሔደ፡፡ ለራትም ይጠብሰው ዘንድ አረደው፡፡ በሆዱም ውስጥ መክፈቻ አገኘ፡፡ በልቡም ‹‹ይህ መክፍቻ ይህን ሣጥን ይከፍተው ይኾን?›› አለ፡፡ በሣጥኑ ቀዳዳም በአስገባው ጊዜ ፈጥኖ ተከፈተ፡፡ በውስጡም ይህን ታናሽ ብላቴና አገኘ፡፡ ልጅ የለውም ነበርና ታላቅ ደስታ ደስ አለው፡፡ ጌታችንንም አመሰገነው፡፡ ሕፃኑንም በመልካም አስተዳደግ አሳደገው፡፡ ሕፃኑም አድጎ ጐልማሳ ኾነ፡፡

ከብዙ ዘመናትም በኋላ ያ ባለ ጠጋ ተነሥቶ ወደዚያ አገር ሔደ፡፡ በመሸም ጊዜ ወደ በግ ጠባቂው ደጅ ደረሰ፡፡ በግ ጠባቂውን ‹‹እስከ ነገ የምናድርበት ማደሪያ በአንተ ዘንድ እናገኛለን? ኪራዩንም እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡ በግ አርቢውም ‹‹እንዳልኽ ይኹንና እደር›› አለው፡፡ ባለ ጠጋውም በዚያ አደረ፡፡ ራት በሚቀርብም ጊዜ ሕፃኑን ባሕራን› ብሎ ጠራው፡፡ ባለ ጠጋውም ሰምቶ ‹‹ልጅህ ነውን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ በግ ጠባቂውም ‹‹አዎን፤ ታናሽ ሕፃን ኾኖ ሳለ ከባሕር አግኝቼዋለሁና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጄ ነው›› አለው፡፡ ባለ ጠጋውም ‹‹በምን ዘመን አገኘኸው?›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹ከሃያ ዓመት በፊት›› ብሎ መለሰለት፡፡ ያን ጊዜም እርሱ ወደ ባሕር የጣለው መኾኑን ዐውቆ እጅግ አዘነ፡፡

በማግሥቱም ጎዳናውን ሊጓዝ በተነሣ ጊዜ ሰይጣናዊ ምክንያት አመካኝቶ በግ ጠባቂውን እንዲህ አለው፤ ‹‹ዕገሊት ወደምትባል አገር በቤቴ የረሳሁት ጉዳይ ስላለ እንድልከው ልጅህን ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ፡፡ እኔም የድካም ዋጋውን ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡ የብላቴናውም አባት ስለ ገንዘቡ ደስ ብሎት ልጁ ባሕራንን ሰጠው፡፡ እንዲህም ብሎ አዘዘው፤ ‹‹ልጄ ባሕራን፣ ይህ የከበረ ሰው ስለ ጉዳዩ ወደ ቤቱ ይልክህ ዘንድ ና፤ ወደ ቤትህም በሰላም ትመለሳለህ፡፡››

ያን ጊዜም ባለ ጠጋው ወደ መጋቢው እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ፤ ‹‹ይቺን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው፡፡ ማንም ዐይወቅ፡፡›› በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎ አሸጋት፤ ለባሕራንም ሰጠው፡፡ ለመንገዱም የሚኾነውን ስንቅ ሰጠው፡፡ ባሕራንም ተነሥቶ ጉዞውን ጀመረ፡፡ ሲጓዝም ሰንብቶ የአንዲት ቀን ጉዞ ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ‹‹አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው›› አለው፡፡ ‹‹ወደ ዕገሌ አገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለ ጠጋ የተጻፈች መልእክት ናት›› አለው፡፡ ‹‹ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ›› አለው፡፡ እርሱም ስለ ፈራ ሰጠው፡፡

ይቆየን