ሥጋ ለነባቢት ነፍስ እንድትታዘዝና የፈቲው ፆርም እንዲደክም- ጾም

ግንቦት 28ቀን 2007ዓ.ም

በፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ አንቀጽ 15 እንደተገለጸው ቅዱሳን አባቶቻችን ሥጋ ለነባቢት ነፍስ እንድትታዘዝና የፈቲው ፆርም እንዲደክም የሚያደርግ የሰውን ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ የለመነውም ልመና መልስ እንዲኖረው የሰይጣንን ፍላጻ ለመስበር የሚያስችል ኃይል ያለው መሣሪያ ጾም ነው ብለው ጽፈዋል፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር«በእግዚአብሔር አምላካችን ፊት ራሳችንን ዝቅ እናድርግ፣ በእርሱም ዘንድ ጾምን አወጅኩኝ ስለዚህ ነገር ጾምን፣ ወደ እግዚአብሔርም ለመንን እርሱም ተለመነን፡፡» እንዳለ የሰው ልጅ የነፍሱን ነገር በማሰብ በጾም እግዚአብሔርን ሊለምን ሊማጸን የሚፈልገውን ሁሉ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ከነቢዩ ዕዝራ የምንማረው በጾም ለሕዝብና ለራስ ለምኖ ዋጋ ማግኘትን ነው፡፡ 

ዐወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ «ይህ ነገር ያለጾምና ያለጸሎት አይወጣም» /ማቴ.17-2/ ሲል የሚያስረዳን ትልቅ ምስጢር አለ፡፡ እርስ በእርሳችን የሚያጣላን የሚያቀያይመን ይባስም ብሎ ከአምላካችን ጋር እንድንለይ የሚያደረገውን በዐይናችን የማናየውን የዘወትር ጠላታችን ሰይጣንን ድል መንሳት የምንችለው በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ለዚህም ነቢዩ«ጾምን ለዩ ምህላንም አውጁ» እንዳለ /ኢዩ.2-11/ የሰው ልጅ ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ ለማስገዛት ጾምን በራሱ ላይ ሊያውጅ ወይም ሊያነግሥ ይገባል፡፡

ዐበብሉይ ኪዳን ዘመን እጅግ ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችን በጾም የጠየቁትን ሁሉ አግኝተዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ እስራኤልን በሚመራበት ወቅት አሕዛብ እንዳይሰለጥኑበት፣ ወገኖቹም እስራኤል የአሕዛብን አምልኮት ተከትለው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዳይለዩ፣ እንዳይራቡ፣ እንዳይጠሙ፣ በተለይም ዘወትር ለመንፈሳዊ ጉዟቸው የሚያሰፈልጋቸውን ሕጉ የተጻፈበትን ቅዱስ ታቦት የተቀበለው 40 ቀንና 40 ሌሊት በሲና ተራራ በመጾም በመጸለይ ነበር፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስም ይህችን ረብ ጥቅም የሌላትን ጊዜያዊና ኃላፊ ዓለም ትቶ የሚበልጠውን መንፈሳዊውን ዓለም ለማግኘት ወደ ሰማይ ያረገው በጾም ኃይል ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል መንፈሳዊ ኃይል ተሰጥቶት ታላቋን የባቢሎንን ከተማ በማናወጥ በሥጋ ሐሳብና ኃይል የማይቻለውን ድንቅ ነገር ማድረግ የቻለው የአናብስትን አፍ የዘጋው በጾም በጸሎት ነው፡፡ ሦስቱ ሕፃናትም ሳይቀሩ ከነበልባል እሳት የዳኑት በጾም ኃይል እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የማስተማር ተግባሩን ሳይጀምር ለሥራው ሁሉ ተቀዳሚ ያደረገው ጾምን ነው፡፡ በጾሙም ወቅት ዲያብሎስ ስለተፈታተነው በቀረበለት ፈተና ሁሉ ድል ነሥቶታል፡፡ ከዲያብሎስ የቀረቡለትም ፈተናዎች ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ ነበሩ፡፡ ክርስቶስም በስስት የመጣውን በትዕግሥት፣ በትዕቢት የመጣውን በትሕትና እንዲሁም በፍቅረ ንዋይ የመጣውን በጸሊአ ንዋይ ዲያብሎስን ድል ነስቶታል፡፡ ማቴ.1-1-11፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጾመው ጾም የምንማረውም የኃጢአት ሁሉ ሥር የሆነውን ዲያብሎስን ድል መንሣት ሲሆን ይኸውም በጾም፣ በጸሎት፣ በትዕግሥት፣ በትሕትና፣ በሃይማኖት፣ በጸሊአ ንዋይ ወይም ገንዘብን በመጥላት ወዘተ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ስለሆነም በዚህ ታላቅ የጾም ወቅት ሁላችንም ትችት፣ ሐሜት፣ ቅናት፣ ተንኮል ወዘተ ፍላጎቱ የሆነውን የሥጋ ፈቃዳችንን ለነባቢት፣ ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ ፈቃድ በማስገዛት የሥጋ ፈቃዳት የተባሉትንም በማሸነፍ የፈቲው ጾርንም በማድከም ከልብና በሃይማኖት ልንጾም ይገባል፡፡ ብዙ ሰዎች ከጊዜያዊ እህል ውኃ ይጾማሉ ወይም ያስቀድሳሉ ይጸልያሉ ብዙ መንፈሳዊ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡

ጾም ክርስቲያኖች የሆኑ ሁሉ በጠባብ በር ወደ ተመሰለው ፈቃደ ነፍስ ለመግባት ሊሽቀዳደሙበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ «ብፁዓን ይርኅቡ ወየጸምኡ በእንተ ጽድቅ እስመ እሙንቱ»፤ ስለጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው ይጠግባሉና ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.5-6/፡፡ ስለጽድቅና ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲሉ ከሚበሉት እየቀነሱ ለጦም አዳሪዎች የሚሰጡ ብፁዓን ይባላሉ፡፡ በመንግሥተ ሰማያት አይራቡምና፡፡ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ገንዘብ ሳይሰስቱ ለተራቡ የሚሰጡ፣ በትሕትናቸው ብዙ መንፈሳውያን የትሕትና ሰዎችን የሚያፈሩ በትዕግሥታቸው ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርቡ ምክንያት የሚሆኑ ሰዎች ይህን መዋዕለ ጾም አስበውታል የጾም ትርጉሙም ገብቷቸዋል ማለት ያስችላል፡፡ እየጾሙ፣ እየሰበኩ፣ እየዘመሩ፣ እያስተማሩ ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ከሌላቸው ክርስቶስን መስለውታል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም ጾም ስናውጅ ትርጉም ያለው ለንስሐ የሚያበቃ ጾም እንዲሆንልን ፍቅራችን፣ መተሳሰባችን ሊጨምር ይገባዋል፡፡

ሁላችንም እንደ ዘኬዎስ ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን የምንወጣበት ዛፍ ግን እጅግ ያስፈራናል፡፡ ሁሉንም በእግዚአብሔር እንድንችለው ትሕትና፣ ፍቅር ሃይማኖት ሊኖረን ይገባል፡፡ እንዲሁም አቅማችንን በማወቅም ደረጃ ብዙ ይቀረናል፡፡ ሰው ሁል ጊዜ ታናሽ እንደሆነ ክርስትናውም ዕለት ዕለት ማደግ እንዳለበት ካላመነ እጅግ ከባድ አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ የለም፣ የማይኖርበትም ጊዜ የለም ለኃጢአተኛም ይሁን ለጻድቅ ሰው እግዚአብሔር ቅርብ ነው፡፡ በድለን በደላችንን በመንገር የሚደመስስልን ቸር አምላክ፤ ኃጢአት ሠርተን በኃጢአታችን የማያጠፋን ይቅር ባይ ታጋሽ ጌታ ስለሆነ እግዚአብሔርን ከምንምና ከማንም በላይ በፍጹም ፍቅር መቅረብና መማጸን ይገባናል፡፡

ጾም ከደዌ ሥጋና ከደዌ ነፍስ ለመፈወስ የምንችልበት መንፈሳዊ ኀይል ስላለው የሚሰጠውን ጥቅም ማወቅና መረዳት ይኖርብናል፡፡ ይህም ከሆነ በጾም ሥጋ ለነባቢት ነፍስ እንድትታዘዝና የፈቲው ፆርም እንዲደክም ያስችላል ማለት ነው፡፡ ጾመን የበረከቱ ተሳታፊዎች እንድንሆን በዚህ ለሥጋችንም ፈቃድና ሐሳብ ሳይሆን ለነፍሳችን ዘለዓለማዊ ሕይወት እንድናስብ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር