ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው? – ክፍል አንድ

በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ

ታኅሣሥ ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በአንድ ወቅት በተሐድሶ መናፍቃን በተሰራጨ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ ላይ በሦስቱ ድርሳናት ማለትም በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል፤ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል፤ በድርሳነ ሩፋኤል ላይ ደግሞ ሩፋኤል ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት አዳናቸው ተብሎ ስለ ተገለጸ ‹‹ትክክለኛው ትምህርት የትኛው ነው? ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክስ ማን ነው?›› የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲነሣ ሰምተናል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት የምንመለከተውን የመሰሉ ጥያቄዎችን እያነሡ ገድላትን፤ ድርሳናትንና ሌሎች አዋልድ መጻሕፍትንም የሚነቅፉና የሚያስነቅፉ ሰዎች ቍጥራቸው በርከት እያለ መጥቷል፡፡ ከዚህም የተነሣ በተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ጽሑፎችና የምስል ወድምፅ ስብከቶች ይቀርባሉ፡፡ ይህም ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ወይም ምሥጢራት ግንዛቤአችን አነስተኛ የኾነብንን ሰዎች ሊረብሸን ይችላል፡፡ እኛም ነገሩን ከመሠረቱ ለመረዳት እንዲያመቸን ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን ብቻ ሳይኾን የማንጠየቃቸውንም ጭምር በአግባቡ ተረድተን እንድንጠቀም የሚረዳ መንገድ ለመጠቆም ይህንን ጽሑፍ አዘጋጅተናል፡፡ አስቀድመንም ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዴት ልንረዳ እንደምንችል ለማመላከት እንሞክራለን፤

በቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ሦስት ዓይነት መልእክቶችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው ታሪካዊ መልእክት ሲኾን ይህም ማለት ድርጊትን ሲዘግብልን ወይም የተጻፈው ደረቅ ትንቢትና ቀጥተኛ ትምህርት ማን መቼ ለማን በምን ምክንያት እንደ ተናገረው ስናጠና የምናገኘው ታሪካዊና ተጨባጭ መልእክት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ምግባራዊ መልእክት ሊባል የሚችለውና ምን ማድረግ እንዳለብን ወይም እንደሌለብን፤ እንዴትና መቼ ትእዛዛትን መፈጸም እንደሚገባን የሚያስተምረን ቀጥታ ልንተገብረው የሚገባንን ተግባር የሚያሳውቀን መልእክት ነው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ምሥጢራዊ ወይም መንፈሳዊ መልእክት ነው፡፡ የዚህም ዋና ዓላማው ምሥጢሩን ከተረዳን በኋላ በገቢር (በተግባር) እንድንገልጸው ቢኾንም ዋናውን መልእክት የምናገኘውም ምሳሌው ወይም ትንቢቱ ወይም ታሪኩ በውስጡ አምቆ የያዘው መለኮታዊ መልእክትን ስናውቅ ነው፡፡ ይህ ምሥጢራዊ ወይም መንፈሳዊ መልእክት ግን በግምት ወይም በመላምት የሚሰጥ ሳይኾን ከጥንት ከጌታችንና ከሐዋርያት ጀምሮ እነዚህን መጻሕፍት ያስተማሩ ቅዱሳን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ከተናገሩትና ካስተማሩት ትምህርት የሚገኝ ነው፡፡

ለምሳሌ ጌታችን ሉቃስንና ቀልዮጳን ወደ ኤማሁስ ከሚሔዱበት መንገድ የመለሳቸው እነርሱ እንደ ተናገሩት ‹‹ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተረጐመ›› ሲነግራቸውና በምሥጢራቱም ‹‹ልቡናቸውን ካቃጠለው›› በኋላ ነው /ሉቃ.፳፬፥፲፫-፴፭/፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም መልእክቶቻቸውንና ወንጌሎቻቸውን ብናይ በኦሪት የምናውቃቸውን ታሪኮችና ትእዛዛት መንፈሳዊና ምሥጢራዊ መልእክቶቻቸውን በሰፊው አስቀምጠውልናል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ እስራኤል ከግብጽ ሲወጡና ባሕረ ኤርትራን ሲሻገሩ የገጠማቸውን ነገር በሙሉ የጥምቀትና የመንፈሳዊ ወይም የጸጋ እግዚአብሔር ምግብና እንደ ኾነ ተርጕሞልናል /፩ኛቆሮ.፲፥፩-፭/፡፡ አጋርንና ሣራንም የኦሪትና የወንጌል ምሳሌዎች አድርጎ ልጆቻቸው እስማኤልና ይስሐቅ ለምን ዓይነት መንፈሳዊና ታላቅ ምሥጢራዊ መልእክት ምሳሌዎች እንደ ኾኑ ነግሮናል /ገላ.፬፥፳፪ እስከ ፍጻሜው/፡፡

የኋላ ሊቃውንትም በዚሁ በእነርሱ መንገድ ሔደው የቅዱሳት መጻሕፍትን ተዝቆ የማያልቅ መለኮታዊ መልእክት ወይም ምሥጢር በስፋት አስተምረውናል፡፡ አባታችን ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ሌሊት በሕልሙ ከላይ እግዚአብሔር ተቀምጦባት መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያያትን መሰላል በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የሚላኖ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አምብሮዝ ሲተረጕም፡- ‹‹መላእክት የተባሉት ከሐዋርያት ጀምሮ ያሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ናቸው፡፡ የመሰላሉ ቋሚዎች የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍት ሲኾኑ በቋሚዎቹ ላይ ያሉ ርብራቦች ደግሞ ከእነርሱ የሚገኙት ምግባራት ማለትም ጾም፣ ጸሎት፣ ቀዊም፣ ስግደትና የመሰሉት ናቸው፡፡ ሊቃውንት በእነዚህ በኩል ወደ ላይ በብቃት ይወጣሉ፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስም እስከ ሦስተኛው ሰማይ ይነጠቃሉ፡፡ ምሥጢራተ መጻሕፍትንም ይዘውልን ይወርዳሉ፤›› በማለት ያስረዳል፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢራዊ መልእክት አላቸው ሲባልም አንድ ሰው ከራሱ ዓለማዊ ዕውቀት ወይም ልምድ ብቻ ተነሥቶ ወይም ከአስተሳሰቡ አመንጭቶ የሚነግረን ሳይኾን ቅዱሳን ሊቃውንት ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ መሠረት ከእርሱ ተቀብለው የሚሰጡን ትምህርት ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት በሰው ቋንቋ የተጻፉ የእግዚአብሔር መለኮታዊ መልእክቶች ናቸውና ከቃላቱ መደበኛ ትርጕም ያለፈውን መለኮታዊ ምሥጢር ወይም መልእክት ልናገኘው የምንችለው ከእግዚአብሔር በሚሰጥ ጸጋ ብቻ ስለሚኾን ነው፡፡ በመጠኑም ቢኾን ስለ ትርጓሜ መጻሕፍት ምሥጢር ይህን ያህል ከጠቀስን አሁን ደግሞ ከላይ በርእሱ ስለ ተቀመጠው የኦሪት ጥቅስ ምሥጢራዊ መልእክት እንመልከት፤

በቅዱሳት መጻሕፍት ስለምንቀበለውና ስለማንቀበለው ትምህርት ከተነገረባቸው መንገዶች አንደኛው ምሳሌያዊ መንገድ ነው፡፡ ይህም ማለት ለጊዜው ቀጥታ ለሚተገበር ምግባራዊ ሕግ የተሰጡ መስለው ምሳሌነታቸውና ምሥጢራዊ መልእክታቸው ግን ሃይማኖታዊ ወይም ስለ ሃይማኖታችን ልንቀበላቸውና ላንቀበላቸው ስለሚገባን ትምህርቶች በምሳሌ የተገለጹ መኾናቸው ነው፡፡ ከእነዚህ መልእክቶች አንደኛውን ለማስታወስ ያህል፡- ‹‹የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ዅሉ ብሉ፤ ነገር ግን ከሚያመሰኩት፣ ሰኮናቸው ስንጥቅ ከኾነው ከእነዚህ አትበሉም፡፡ ግመል ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። ጥንቸልም ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። እርያም ሰኮናው ተሰንጥቋል፤ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፤ በድናቸውንም አትነኩም፡፡ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው፤›› ተብሎ በኦሪት የተገለጸው ትእዛዝ ይገኝበታል /ዘሌ.፲፩፥፫-፰/፡፡

በኦሪት ሕግ እንድንመገባቸውና እንዳንመገባቸው ለማድረግ እግዚአብሔር ያዘዘን እያንዳንዳቸውን በሙሉ በመዘርዘር ሳይኾን በቡድን በመመደብና ምሳሌ በመጥቀስ ነው፡፡ እንድንበላቸው የተፈቀዱት እንስሳት ሁለት ነገሮችን ሊያሟሉ ይገባቸዋል፤ ይኸውም በኦሪት ዘሌዋውያን እንደ ተጻፈው የሚያመሰኩና ሰኮናቸው የተሰነጠቀ መኾን ይኖርባዋቸል፡፡ ሁለቱንም መሥፈርት የማያሟሉ ብቻ ሳይኾን ከሁለቱ አንዱንም የማያሟሉ እንስሳት አይበሉም፡፡ ይህ ትእዛዝም ቀደም ብለን ባየነው ትምህርት መሠረት ሦስቱን መልእክታት ያስተላልፋል፤ ታሪካዊ መልእክቱ ይህ ነገር ሕግ ኾኖ መቼ? በማን? ለማን እንደ ተሰጠና የመሳሰሉትን ምሥጢራት ሲነግረን፣ ምግባራዊ መልእክቱ ደግሞ የፈጠራቸውን የሚያውቅ አምላክ ሳስቶና ወይም ተመቅኝቶን ሳይኾን እንስሳቱ በሰውነታችን ላይ በሚያመጡት ጉዳትና በመሳሳለው ችግር ምክንያት እንዳይበሉ አዝዞናል፡፡

ዳግመኛም በዘመነ ኦሪት እነዚህን እንስሳት መብላትና አለመብላት የመርከስና የመቀደስ ዋና ምክንያትም ነበረ፡፡ በሐዲስ ግን የማይበሉትን እንኳ የማንበላው ጥንቱንም ስለማይጠቅሙን ነው (ምንም ሲበሉ የኖሩትን ክርስቲያን ማድረጉ ወይም ክርስትና የሚቀድሳቸው መኾኑ የታወቀ ቢኾንም የማይበሉ የነበሩት ይብሉ ማለት አይደለምና) አይጠቅሙንምና አሁንም አንበላቸውም፡፡ ሐዋርያትም በዲድስቅልያ፡- ‹‹ወቦ እለ ይብሉ ሥጋ አኅርው ንጹሕ ባሕቱ ኢኮነ ንጹሐ አላ ርኩስ መፍትው ለነ ንርኀቅ እምዘ ከመዝ ግብር ወዘሰ ኮነ ንጹሐ በውስተ ሕግ ይብልዑ እምኔሁ፤ የእሪያዎች ሥጋ ንጹሕ ነው የሚሉ አሉ፤ ነገር ግን ርኩስ ነው እንጂ ንጹሕ አይደለም፡፡ ከእንደዚህ ያለ ሥራ እንርቅ ዘንድ ይገባናል፡፡ በመጽሐፍ ንጹሕ ከኾነ ግን ከእርሱ ይብሉ፤›› ሲሉ አዝዘውናል / አንቀጽ ፴፪፥፵፮-፵፯/፡፡

በዚህ ኃይለ ቃል ‹‹የሚያመሰኩና ሰኮናቸው የተሰነጠቀ ንጹሐን ናቸው›› የተባሉት በሃይማኖትና በምግባር የሚኖሩ መምህራንና ምእመናን ናቸው፡፡ የሚያመሰኳ (በአሁኑ አማርኛ የሚያመነዥክ ሲባል የምንሰማው ነው) ማለትም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢራት በሕሊናው የሚያመላልስ ማለት ነው፡፡ የሚያመነዥክ ወይም የሚያመሰኳ እንስሳ ሣሩንም ቅጠሉንም ከበላው በኋላ እንደ ገና ወደ ላይ ወደ አፉ እያመጣ ደጋግሞ እንደሚያላምጠው ቅዱሳንና እውነተኛ መምህራንም አንዴ በትምህርት የተቀበሉትን ምሥጢር ወይም ቃለ መጽሐፍ በሚገባ ከተረዱትና በልቡናቸው ካሳደሩት በኋላ ምሥጢሩን ወደ ሕሊናቸው እያመላለሱ፣ እያወጡና እያወረዱ የበለጠ እያራቀቁ ለራሳቸውም ለሌላውም ጤናና ሕይወትን የሚሰጥ ተስማሚ ምግብ ያደርጉታል፡፡ ‹‹ብፁዕ ብእሲ … ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ፤ ሕጉን ወይም ቃሉን በሌሊትም በቀንም የሚያስብ (ምሥጢራቱን የሚረዳ) ምስጉን፣ ንዑድ፣ ክቡር ነው፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ /መዝ.፩፥፫/፡፡

ሰኮናው የተሰነጠቀ ማለት ደግሞ በተራመደ ጊዜ መሬት በደንብ የሚቆነጥጥ፣ የሚጨብጥ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት የሚናገረውንና የሚያውቀውን በሕይወቱ ተግባራዊ አድርጎ የሚኖርበት ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ከላይ ከተጠቀሰው መዝሙሩ በማከታተል፡- ‹‹ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ፤ እንት ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ ወቈጽላኒ ኢይትነገፍ፤ እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይኾናል፤ የሚሠራውም ዅሉ ይከናወንለታል፤›› እንደ ጠቀሰው ማለት ነው /መዝ.፩፥፫/፡፡

የማያመሰኳ እንስሳ የዋጠውን መልሶ እንደማያደቀው መልሶ መላልሶ እንደማያኝከው ዅሉ መናፍቃንም አንድ ጥቅስን በኾነ መንገድ ጐርሰው ከዋጡት በኋላ ምሥጢር አያመላልሱም፤ ደጋግመውም አያኝኩትም፡፡ ማለትም የሚመላለሱ ምሥጢራትን አያገኙም፤ አይመረምሩም፡፡ ዳግመኛም ሰኮናቸው ስላልተሰነጠቀ መሬት አይቆነጥጡም፤ ሃይማኖቱንም በምግባር አይኖሩትም፤ እንዲሁ ሲያደናግሩ ይኖራሉ እንጂ፡፡ ይህም ማለት እንደ ግመል በአካል ገዝፈው ብናያቸውም ለሰኮናቸው የሚስማማ አሽዋ (ያልረጋ ልቡና) ፈልገው በዚያ ይኖራሉ እንጂ እንደ ሌሎቹ እንስሳት መሬት ቆንጥጠው ረግጠው ገደልና ተራራ አይሻገሩም፤ ሃይማኖት አቀበትን ሊወጡ ገደላ ገድል ተጋድሎዎችንም አልፈው ለምሥጢር፣ ለክብር ሊበቁ አይችሉም፡፡ በሃይማኖት ገና ያልረጋና እንደ አሸዋ የሚንሸራተት ልቡና ካለ የመናፍቃን ድፍን ሰኮና ይረግጠዋል፤ የበለጠም ያንሸራትተዋልና ዅላችንም ልቡናችንን ለማጽናት መትጋት ይገባናል፡፡

ከዚሁ ከሚበሉና ከማይበሉ እንስሳት ምሥጢር ሳንወጣ በባሕር ውስጥ ካሉት እንስሳት መካከል እንድንበላቸው የተፈቀዱልን ቅርፊትና ክንፍ ያላቸው ዓሦች ናቸው፡፡ ቅርፊት ለባሕር ፍጥረታት ጋሻቸው መጠበቂያቸው እንደ ኾነ ዅሉ በክርስትናም ከመናፍቃን የኑፋቄ ጦርና የክሕደት መርዝ ለመዳን የሃይማኖትና የምግባር ጋሻ መታጠቅ ያስፈልጋል፡፡ ዓሦች በክንፋችው ከላይኛው የባሕር ክፍል ድረስ እንደሚንሳፈፉበትና ወደ ታች እንዳይዘቅጡ እንደሚጠበቁበት ዅሉ በመንፈሳዊ ሕይወትና በንጽሕና ክንፍ ወደ ከፍተኛው የእግዚአብሔር ምሥጢርና መረዳት የማይወጡ እንደ ድንጋይ በከበደ በዚህ ዓለም ፍልስፍና እና ሥጋዊ ሙግት ወደ መሬታዊነትና ሥጋዊነት የሚዘቅጡት መናፍቃን ‹‹ርኩሳን›› ከሚባሉት መመደባቸውን ማወቅ፣ አውቆም ከኑፋቄ ትምህርታቸው መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ ከላይ እንደ ገለጽነው እነርሱ ከዘመን አመጣሽ ሐሳብና ክሕደት የሚጠበቁበት ቅርፊት (የሃይማኖት ጋሻ) የሌላቸው ናቸውና፡፡

አንዳንዶቹ ‹‹አስኳሉን እንስጣችሁ ስንላቸው ቅርፊቱን አትንኩብን አሉ›› ሲሉ እንደሚደመጡት፣ (በኤግዚቢሽን ማእከል በተደረገው የተሐድሶዎች ልፈፋ ላይ አንድ አባ ተብየ የተናገረውን አስታውሱ) ቅርፊቱ የእንቁላሉን አስኳል የያዘውና ከጉዳት የሚጠብቀው አካል መኾኑን እንኳ ማሰብ ተስኗቸው መጠበቂያ ቅርፊት የሌላቸው ብቻ ሳይኾኑ ካላቸውም ላይ መስበር የሚፈልጉ መኾናቸውን መንፈስ ቅዱስ ፊታቸውን ጸፍቶ፣ አፋቸውን ከፍቶ አናግሯቸዋል፤ በራሳቸውም ላይ አስመስክሯቸዋል፡፡

ስለዚህ ክርስቲያኖች ንጹሐን የሚበሉ (አምላካቸው የሚቀበላቸው) የሚኾኑት ጥርጥርንና ክሕደትን፣ ይህንም የመሰለ የመናፍቃንን የመዘባበትና የክሕደት ጦር የሚከላከል በቅርፊት የተመሰለ የሃይማኖት ጋሻ ሲኖረን ነው፡፡ ከጋሻዎቻችን ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ የሃይማኖታችንን ነገር፣ የቅዱሳት መጻሕፍትንም ምሥጢር ለብሶ ማለትም አውቆ መገኘት ነውና ጊዜ ወስዶ ቁጭ ብሎ መማር እንኳ ባይቻል በተገኘው አጋጣሚ ዅሉ ልቡናን ከፍቶ በወሬና በአሉባልታ ሳይጠመዱ መማር፣ መጠየቅና እንደ ተገለጸው እያመላለሱ በማኘክ (በማጥናት) ቃሉን በሚገባ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በሃይማኖት ልብን ማጽናት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ከኾነ ጠይቀን ያልገባንንና የማናውቀውን ምሥጢር እስከምንረዳው ድረስ ጊዜ እናገኛለን፡፡

ነገር ግን ብዙዎቻችን ትዕግሥት የለንም፤ ዛሬ ይህን ጽሑፍ ከምናነብበው እንኳ አንዳንዶቻችን ቀጥታ ነገሩን በቅርቡ ማግኘት ባለመቻላችን ልንበሳጭም እንችላለን፡፡ ነገር ግን አሁንም አስቀድመን አንዲት ጥያቄ ብቻ መልሰን እንሒድ፤

ይቆየን