ምኲራብ

                                                                                                                ገብረእግዚአብሔር ኪደ

ምኲራብ ማለት ቤተ ጸሎት ማለት ሲሆን ናቡከደነፆር ቤተ መቅደስን አፍርሶ አይሁድን ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን ለመማርና ለጸሎት በየቦታው የሰሩት ቤት ነው፡፡ በኢየሩሳሌም ብቻ ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ ማንም እስራኤላዊ በዓመት ሦስት ጊዜ አምልኮውን መፈጸም ግዴታው የነበረ ሲሆን፥ በምኵራብ ግን በየዕለቱ እየተገናኙ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነቡ፤ ይተረጕሙና ይሰሙም ነበር (ሕዝ.፲፩፥፲፮፣ ሐዋ.፲፭፥፳፩)፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ፥ በልብ መታሰቡ፣ በቃል መነገሩ፣ በቅዱሳት መጻሕፍትም መዘከሩ ከፍ ከፍ ይበልና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራበ አይሁድ እየተገኘ እንዳስተማረ፣ ድውያንን እንደ ፈወሰ፣ በዚያ ይነግዱ የነበሩትንም ማስወጣቱን አስመልክቶ በዐቢይ ጾም ከሚገኙት ሳምንታት መካከል ሦስተኛውን እሁድ ምኵራብ ብሎታል፡፡ “ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖትም ቃል አስተማረ፡፡ ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ፡፡ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባትዋ እኔ ነኝ አላቸው፡፡ የአባቴን ቤት የሸቀጥ ቦታ አታድርጉት፡፡ ቤቴ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራል፡፡ ወደ ምኵራብ ገብቶ ተቈጣቸው፡፡ ዝም እንዲሉም ገሠጻቸው፡፡ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩንም ጣዕም የንግግሩንም ርቱዕነት አደነቁ” በማለትም ይዘምራል – በጾመ ድጓው ! ከዚህም መረዳት እንደምንችለውም፡-

አንደኛ ቅዱስ ያሬድ ምኲራብን “የአይሁድ ምኵራብ” ብሎ እንደ ጠራው እንመለከታለን፡፡ በዕለቱ በሚነበበው ወንጌል ላይም፥ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ቀርቦ የነበረውን ፋሲካ “የእግዚአብሔር ፋሲካ” (ዘጸ.፲፪፡፥፲፩) ማለትን ትቶ “የአይሁድ ፋሲካ” ብሎ እንደ ጠራው እናያለን (ዮሐ.፪፥፲፪)፡፡ ሊቁ ራሱ ቀጥሎ እንደ ነገረን፥ አይሁድ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ ብለው እንደ ነበረ፥ ጌታችን ግን የሰው ሥርዓትንና ወግን ሳይኾን “የሃይማኖትን ቃል” ወይም ወንጌልን እንዳስተማራቸው እንገነዘባለን፡፡

ምንም እንኳን ከላይ እንደ ተናገርነው አይሁድ በዚያ በምኵራብ በየዕለቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያነበቡ የነበሩ ቢኾኑም፥ በገጸ ንባባቸው ብቻ ድኅነት የሚገኝ ይመስላቸው ስለ ነበረ ጌታችን “የሃይማኖትን ቃል” አስተማራቸው (ዮሐ.፭፡፥፴፱)፡፡ ዳሩ ግን ምን ያደርጋል፤ አብዛኞቹ ይህን አልተቀበሉትም፡፡ ይህን የተመለከተው አፈ ጳዝዮን ዮሐንስ አፈወርቅ በልደት ድርሳኑ ላይ እንዲህ አለ፡- “በአይሁድ ዘንድ ድንግል እንድትፀንስ ተነገረ፤ በእኛ ዘንድ ግን እውነት ኾነ፡፡ ትንቢት ለምኵራብ ሃይማኖት ለቤተ ክርስቲያን ነውና፡፡ ያቺ ትንቢትን ገንዘብ አደረገች፤ ይህችም ሃይማኖትን ገንዘብ አደረገች፡፡ ምኵራብ ምሳሌን ሰጠች፤ ቤተ ክርስቲያን አመነችበት፡፡ ምኵራብ ትንቢት አስገኘች፤ ቤተ ክርስቲያን ተቀበለችው፡፡ ምኵራብ ትንቢቱን በምሳሌ አስተማረች፤ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ጸናችበት፥ ረብሕ ጥቅም አደረገችው፡፡ ከዚያም የወይን ሐረግ (መስቀል) ተተከለ፤ በእኛ ዘንድ ግን የጽድቅ ፍሬ ተገኘ፡፡ ያቺ ወይንን በዐውድማ ረገጠች፤ አሕዛብ የምሥጢሩን ገፈታ ጠጡ፡፡ ያቺ የስንዴ ቅንጣትን ዘራች፤ አሕዛብ በሃይማኖት ሰበሰቡት፡፡ አሕዛብ ጽጌረዳን በቸርነቱ ሰበሰቡ (ሃይማኖትን ገንዘብ አደረጉ)፤ እሾኹ ግን በአይሁድ ዘንድ ቀረ፡፡ ይኸውም ክሕደት ኑፋቄ ነው፡፡ ትንሽ ወፍ ሰነፎች ተቀምጠው  ሳሉ  ጥላውን  ጥሎባቸው  ይኼዳል፡፡  አይሁድም በብራና የተጻፈውን መጽሐፍ ተረጎሙ፤ አሕዛብ ግን ምሥጢሩን ተረዱ” እያለ እንዳመሠጠረው (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐ.አፈ.፣ ፷፮፥፳፩-፳፬)፡፡

ሁለተኛ ቅዱስ ያሬድ “እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን” እንደሚወድ ነግሮናል፡፡ ይኸውም አብዛኛው አይሁድ ጌታችን እንደ ተናገረ ከአፍ ብቻ ሃይማኖታውያን የነበሩ በውስጣቸው ግን እንዳልነበሩ የሚያመለክት ነው (ማቴ.፳፫፡፳፯)፡፡ እግዚአብሔር ግን የሚፈልገው የልብ መታደስን፣ የሕይወት መዓዛ መለወጥን፥ በአጭሩ እግዚአብሔር መምሰልን ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን “የምሕረት አባትዋ እኔ ነኝ” እያለ ይህን ያስተምራቸው ዘንድ ወደ “አይሁድ ምኵራብ” እንደ ገባ እንመለከታለን፡፡ ምሕረት በሦስት መልኩ የምትፈጸም ስትሆን እነርሱም ምሕረት ሥጋዊ፣ ምሕረት መንፈሳዊና ምሕረት ነፍሳዊ ይባላሉ፡፡ ምሕረት ሥጋዊ የሚባለው ቀዶ ማልበስ ቈርሶ ማጉረስ ነው፡፡ ምሕረት መንፈሳዊም መክሮ አስተምሮ ክፉን ምግባር አስትቶ በጎ ምግባር ማሠራት ነው፡፡ ምሕረት ነፍሳዊ ደግሞ ክፉን ሃይማኖት አስትቶ በጎ ሃይማኖት ማስያዝ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችን ከየትኛውም ዓይነት መሥዋዕት ይልቅ ደስ ብሎ የሚቀበለው ይህን እንደ ሆነ ከዚህ እንማራለን፡፡

ሦስተኛ፥ ቤተ መቅደሱ ቤተ ምሥያጥ ሆኖ እንደ ነበረ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ነግሮናል፡፡ ቤተ መቅደሱ ከተመሠረተበት ዓላማ ርቆ፣ የገበያና የንግድ ቦታ ሆኖ፣ “ተዉ” ብሎ የሚቈጣ ሰው ጠፍቶ፣ “ርግብ ሻጮች” በዝተው እንደ ነበረ በዕለቱ ከሚነበበው ወንጌልም እንመለከታለን (ዮሐ.፪፥፡፲፬)፡፡ ስለዚህ ጌታችን ይህን ያደርጉ የነበሩትን ሲገለባብጥባቸው፥ አንደኛ- ዓላማቸውን ስለ መሳታቸው ሲነግራቸው፣ ሁለተኛ- መሥዋዕተ ኦሪትን ሲያሳልፍ፣ ሦስተኛ- ዛሬም ጭምር ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በሚፈተትበት ሥፍራ ይህን የሚያደርጉትን “ከቶ አላውቃችሁም” እንደሚላቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ዳግመኛም “ርግብ ሻጮች” የተባሉት በተጠመቁ ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ የተቀበሉትን መንፈሳዊ ሀብት ለምድራዊ ሥራ ለኃጢአት ንግድ የሚጠቀሙበትን “ከእኔ ወግዱ” እያለ በፍርድ ቃሉ ጅራፍ ወደ ውጭ ጨለማ እንደሚያወጣቸው የሚያስተምር ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ ሌላው የነገረንና በአራተኛ ደረጃ ልናየው የምንችለው፥ ክብር ይግባውና ጌታችን ሲያስተምራቸው ሁሉም እንደ ተደነቁ እንመለከታለን፡፡ ይኸውም እንደ ነቢያት “እግዚአብሔር እንዲህ አለ”፣ “ሙሴ እንዳዘዘ”፣ “ሳሙኤል እንደ ተናገረ” በማለት ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን እንደ ሠራዔ ሕግ “እኔ ግን እላችኋለሁ” እያለ ያስተምራቸው ስለ ነበረ ነው፡፡ ይህም የባሕርይ አምላክነቱን የሚገልፅ ነው፡፡

እግዚአብሔርን የምትወዱት፥ ይልቁንም እግዚአብሔር አብልጦ የሚወድዳችሁ ሆይ ! እንግዲያውስ እኛም እንፍራ፡፡ ከፈቃደ እግዚአብሔር ፈቀቅ ብለን መቅደስ ሰውነታችን የእግዚአብሔር ሳይሆን “የአይሁድ ምኵራብ” እንዳይባል እንፍራ፡፡ ደገኛ ዘር ይኸውም የወንጌል ዘር ተዘርቶብን ሳለ የክፋት ፍሬ ተገኝቶብን ያን ጊዜ እንዳናፍር አሁን እንፍራ፡፡ ምሕረት ሥጋዊን፣ ምሕረት መንፈሳዊንና ምሕረት ነፍሳዊን በቃል ያይደለ፤ እንደ ዓቅማችን በተግባር እንፈጽም፡፡ በእውነት ያለ ሐሰት ብርሃናችን በሰዎች ሁሉ ፊት በርቶ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔር የሚከብረው፥ እግዚአብሔርም እኛን የሚያከብረን ያን ጊዜ ነውና፡፡ ቤተ መቅደሱንና ቤተ መቅደስ ሰውነታችን ቤተ ምሥያጠ ኃጢአት አድርገነው እንደ ኾነ ወይም እንዳልኾነ ቆም ብለን እንይ፡፡ ርግብ ሻጮች ሆነን እንዳንገኝና ሥርየት የሌለው ኃጢአት እንዳያገኘን እንፍራ፡፡ ይህን ያደረግን እንደ ሆነም ጌታችን ዳግም በመጣ ጊዜ “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን” ከሚላቸው ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ክብርና ጌትነት የባሕርይ ገንዘቡ የሚሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በለጋስነቱና ሰውን በመውደዱ ይህን ለማግኘት የበቃን ያድርገን፥ አሜን !