ማእከሉ ያስገነባው G+5 ሕንፃ ተመረቀ

                                             

                                                                                                                                                              በጎንደር ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል ያስገነባው  G+5  ዘመናዊ ሕንፃ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የማኀበሩ አባላት በተገኙበት ግንቦት18 ቀን2010 ዓ.ም ተመረቀ፡፡

የጎንደር ማእከል አገልግሎቱን  የጀመረው  በቤተ ክርስቲያን ግቢ በሚገኙ መቃበር ቤቶች እና በግለሰቦች ቤት ሲሆን አገልግሎቱ እየጠነከረ ሲሔድ  ግን ጎንደር  ከተማ ቀበሌ 17 የጣውላ ቤት በመከራየት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከ1994-1999 ዓ.ም ሰፋ ያለ ቤት በመከራየት አገልግሎቱን  ሲያከናውን ቆይቶ  አባጃሌ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ  ሰፊ ቤት በመከራየት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ከ1999 ዓ.ም በኋላ አዲሱ ሕንፃ ከተገነባበት ቦታ ላይ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቢሮ እና አዳራሽ በመሥራት ከኪራይ ተላቆ አገልግሎቱን ለማስቀጠል በቅቷል፡፡

ማእከሉ ለቢሮ የሚሆንና  ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎት  የሚሰጥበት ቦታ የሌለው መሆኑን የሚገልጥ በቀን 06/05/1996 ዓ.ም እና 03/01/1997 ዓ.ም ለሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በመጻፍ ማዘጋጃ ቤት  ቦታ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን ሀገረ ስብከቱም ለጥያቄውን አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ለጎንደር ማዘጋጃ ቤት የቀበሌ ቤት እንዲሰጠው አሳውቋል፡፡በቀን 19/02/1997 ዓ.ም በድጋሜ በተጻፈ ደብዳቤ በአነስተኛ ኪራይ  የቀበሌ ቤት እንዲሰጠው የጎንደር ከተማ  ማዘጋጃ ቤትን ቢጠይቅም መልስ ሳያገኝ ቆይቷል ፡፡

የማእከሉ አዲስ ሕንፃ የተገነባበትን 2000 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ እንዲሰጣው ጥያቄ አቅርቦ በ02/10/1998 ዓ.ም በ290.40(ሁለት መቶ ዘጠና ብር ከ40 ሣ) በመክፈል  ቦታውን ተረከበ፡፡ ክርስቲን ሻዮ የተባሉ በጎ አድራጊ 20,000.00 ዩሮ ድጋፍ ስላደረጉ የመጀመሪያው ክፍያ ተፈጸመ፡፡

በ02/13/1999 ዓ.ም የዋናው ማእከል ሙያና ማኀበራዊ አገልግሎት ማሰተባበሪያ በበኩሉ 100,000.00 ብር የሚገመት ዲዛይን በነፃ ሠርቷል፡፡ የመሠረት ድንጋይ የተጣለው በ2000 ዓ.ም በአሁኑ ሰዓት ደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በሆኑት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ሲሆን ግንባታው በይፋ በ23/04/2000 ዓ.ም ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ሕንፃው ያረፈበት ቦታ 370 ካሬ ሜትር  ነው፡፡

በምረቃው ዕለት  ትምህርተ ወንጌል በየኔታ ዲበ ኩሉ ግርማይ የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም  ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ መዝሙር በማእከሉ መዘምራን፣ሪፖርት በማእከሉ ሰብሳቢ በአቶ ጌትነት መኳንንት የቀረበ ሲሆን  በመጨረሻም ለሕንፃው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ በጎ አድራጊ ግለሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡አቶ ጌትነት በሪፖርታቸው ለሕንፃው ማስፈጸሚያ  በጎንደር  ከተማ የሚገኙ  የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የቀን ሥራ ተቀጥረው የሚገኙትን ገንዘብ ለሕንፃ ግንባታው ይሰጡ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የጎንደር  ማእከል  አባላትም  የወር ደመወዛቸውን  ለሕንፃው ግንባታ እንደሰጡ  የገለጡት  ሰብሳቢው  የማእከሉ አባላትና የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች  ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን አበርክተዋል፡፡ በጎ አድራጊ ግለሰቦችም የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል ብለዋል፡፡፡፡