ማኅበረ ቅዱሳን የኢቢኤስ የቴሌቪዥን ሥርጭርቱ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ገለጸ

ኅዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም

ዝግጅቱን በኦን ላይን፣ በስልክ እና በአሜሪካ የማኅበረሰብ ቴሌቪዥኖች ማሠራጨቱን ይቀጥላል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ አገልግሎት /EBS/ አማካይነት የሚያቀርበው ሳምንታዊ የአንድ ሰዓት መንፈሳዊ የቴሌቪዥን አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የተቋረጠበትም ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በተጠቀሰው ማሠራጫ ጣቢያ አማካይነት በቤተ ክርስቲያኗ ስም ትምህርት የሚያስተላልፉትን አካላት ማንነትና ዓላማ አጣርቶ መመሪያና ፈቃድ እስከሚሰጥ በቤተ ክርስቲያኗ ስም የሚሠራጩ መርሐ ግብራት እንዲቆሙ በደብዳቤ በጠየቀው መሠረት ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኗ ዕውቅና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ታቅፎ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ያለ በመሆኑ የተጻፈው ደብዳቤ ይመለከተዋል ብሎ ባያምንም፤ አባቶች በጣቢያው አማካይነት የሚተላለፉትን መርሐ ግብራት ይዘትና ዓላማ በአግባቡ አጣርተው መመሪያና ፈቃድ እስከሚሰጡ ሥርጭቱን ማቆሙን መርጧል፡፡

በአስቸኳይ አገልግሎቱን ለመጀመር በሚችልበት ሁኔታም ከቤተ ክርስቲያኗ የበላይ አካላት ጋር እየተወያየ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በሀገር ውስጥና በተለይ በአረብ ሀገራት መርሐ ግብሩን በቀጥታ በኢቢኤስ ማሠራጫ ጣቢያ ሲከታተሉ የነበሩ ምእምናን በትእግስት እንዲጠብቁ ጠይቆ፤ የቴሌቪዥን ሥርጭቱ እስከሚጀምር ድረስ http://onlinetv.eotc.tv/ በስልክ አሜሪካ ለሚገኙ ምእመናን በ605-475-81-72፣ ካናዳ (604)-670-96-98፣ አውሮፓ (ጀርመን 0699-432-98-11፣ እንግሊዝ(ዩኬ) 033-0332-63-60 መከታተል እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

እኛም ሁኔታውን እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡