መምሪያው ለቤተክርስቲያን ወጣቶች ተፈጠረ እንጂ ወጣቶች ለመምሪያው አልተፈጠሩም

/ምንጭ፦ሐመር መጽሔት 19ኛ ዓመት ቁጥር 2 ሰኔ 2003ዓ.ም/

ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ 1ጴጥ. 5፣ 3

ቤተክርስቲያናችን በዚህ ዘመን ትኩረት ሰጥታ ልትፈጽማቸው ከሚገባት ተግባራት አንዱ፤ ወጣቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ በላይ ማሳደግና ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በዋናነት ግን ሥጋዊው ዓለም በቤተክርስቲያን ወጣቶች ሃይማኖታዊ ሕይወትና  መንፈሳዊ አኗኗር ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ነው፡፡ ከመረጃ ቴክኖሎጂ ማደግና እርሱን ተከትሎ እየሰፋና እያደገ የመጣው የሉላዊነትና ዘመናዊነት አሉታዊ ገጽታ ባመጣው ግፊት፤ ወጣቶች ባሏቸው ክርስቲያናዊ ኑሮና እሴቶች ላይ ፈተና ደቅኖባቸዋል፡፡

በርካቶች የዚህ ጫና ሰለባ በመሆን ለብ ወዳለ አኗኗር ራሳቸውን እየለወጡ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ ዓለሙን መስለው፣ የክርስትናን አስተምህሮ ሸርሽረው፣ ሕግና ትእዛዛቱን አሽቀንጥረው ጥለው ለሥጋ ፍላጎታቸው በሚመች መንገድ በራሳቸው ማስተዋል ባቋቋሟቸው ቤተ እምነቶች ወስጥ ታቅፈዋል፡፡ ይህም ሆኖ እንኳን ትክክለኛ ሃይማኖታቸውን ከልብ የተረዱና የዘመኑ የክህደት ማዕበል የተረዳቸው በርካታ ወጣቶች ያንን በመቋቋም የራሳቸውን ሕይወት ለመጠበቅና የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ፣ ትውፊትና ሥርዐት እንደተከበረ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር እየተጉ ነው፡፡ ለዚህም በየአጥቢያው ባሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ገብተው ሕግና ሥርዐት በሚፈቅደው መንገድ አገልግሎት እየሰጡና እየተቀበሉ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና ጊዜው ከሚጠይቀው ምላሽና ጥረት አንጻር እየተጫወቱ ያሉት ሚና በቂ አይደለም፡፡ ይሄ ውስንነት የተፈጠረው ግን በወጣቶቹ የተሳትፎ ፍላጎት ማጣት ሳይሆን፡፡ የወጣቶቹን ዘርፈ ብዙ የአገልግሎት ፍላጎት በቅልጥፍናና በበቂ ሁኔታ እምነትም በሚጣልበት አመራር ማስኬድ አለመቻሉ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ቤተክርስቲያን የአጠቃላዩን የወጣቶች አገልግሎት አሰጣጥና አቀባበል፣ ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አቋቁማ ለዓመታት እየሠራች ቆይታለች፡፡ መምሪያው በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ቢቆይም አሁን እያደገ ላለው የወጣቶች ተሳትፎ በሚመጥን ደረጃ ግን ራሱን ለውጧል ማለት አይቻልም፡፡ የዚህ ችግር መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ የቤተክርስቲያን ወጣቶችን የጊዜውን በጎ ፍላጎት ከግምት ያስገባ፣ ወጣቶች ያሉባቸውን ችግሮች ተደራሽ ያደረገ፣ ርእይና ተልእኮውን በውል ያስቀመጠ፣ መነሻና መድረሻው የሚታወቅ ስልታዊ ዕቅድ ያለው፣ ወጣቶች ለሀገርም ለቤተ ክርስቲያንም ዕድገት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ የሚያስችል አቅም የያዘ አለመሆኑ ነው፡፡ መምሪ ያው አፈጻጸሙ እንዲዳከምና የሚፈለ ገውን አስተዋጽኦ እንዳያበረክት ያደረ ገው የመምሪያው ሓላፊ በራሳቸው አቅምና ፍላጎት ብቻ አሠራሩን ለመገደብ ስለሚጥሩ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት አሁን ባለው በራሱ በማደራጃው አቅም ልክ ብቻ የወጣቶች ተሳትፎ እንዲወሰን ሲጥር እንጂ ከእርሱ እየቀደመ ስላለው የሰን በት ትምህርት ቤቶችና የማኅበራት እንቅስቃሴ በሚመጥን ሁኔታ የራሱን አቅምና የአገልግሎት አሰጣጥ ሲያሳ ድግ አይታይም፡፡ እንደውም እንዲቀጭጭ የሚፈልግ አካል በውስጡ መኖሩ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ አድርጎ ታል፡፡ ይህም ሁኔታ ማኅበረ ቅዱሳን እያደረገ ባለው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ላይ እየፈጠረ ያለው መሰናክል ለዚህ እንደ ማስረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በመላው ሀገሪቱ ያለውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመስፋፋት ዕድል ተጠቅሞ በየተቋማቱ ያሉትን የቤተክርስቲያን ወጣቶች በሃይማኖታዊ ሕይወታቸው ጸንተው እንዲቀጥሉና አስቀድመን የጠቀስናቸውን የዓለምን ወጣቶች እየተፈታተኑ ካሉ ዘመን አመጣሽ ጾሮች እንዲድኑ ለማ ድረግ እየሠራ ነው፡፡ ለዚህም የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት አሰጣጥ መሠረት ያደረገ ሥርዐተ ትምህርት ቀርጾ መዋቅሩንም አጠናክሮ እየተራመደ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአጥቢ ያዎችና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ባለው ተሳትፎ አባላቱ ጉልህ ሚና እን ዲጫወቱ እያደረገም ነው፡፡ ስብከተ ወንጌል እንዳይዳከም ገዳማትና አድባ ራት እንዳይዘጉ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዳይበተኑ፣ የቤተክርስቲያን ክብሯ፣ ታሪኳ እንዳይደፈር ለማድረግ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሌሎችም ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት በዚህ ደረጃ አገልግሎት መስጠት በሚ ያስችል ደረጃ ላይ ደርሰው ቤተክርስቲያናችን ከጌታዋ የተሰጣትን መንፈሳዊ አደራ በብቃት እንድትወጣ ጠንክሮ እየሠራ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ነው በተደጋጋሚ እየተሰማ እንዳለው የማደራጃ መመሪያው ሓላፊ በተለያዩ ሚዲያዎች ተገቢ ያልሆነና አንድ መምሪያ አገልግሎት በሚሰጣቸው አካላት ላይ ሊፈጽመው የማይገባ ስም ማጥፋት እየፈጸሙ የሚገኙት፡፡ ነገሩን የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ አገልግሎት እንዲሰጣቸው ታስቦ በሥሩ እየተንቀሳቀሱ በመላው ሀገሪቱ ላሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ አለመሠራቱ እየተነገረ ባለበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡና የሚቀበሉ ወጣቶች ለሀገርም ለቤተክርስቲያንም ፍሬ ያለው ተግባር እንዲፈጽሙ ለማበረታታት ፈቃደኝነት የማይታይበት መምሪያ የአገልግሎት ፍጥነት እየተጠየቀ ባለበት በዚህ ዘመን የማኅበረ ቅዱሳንን አገልግሎት ለማዘግየት መነሣቱ ከላይ ለጠቀስነው ለመምሪያው የመምራት ብቃት ማነስ ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

የዚህም መነሻ ጌታችን ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም እንዳለው ሥርዐት፣ መዋቅር፣ ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ ለክርስቲያኖች ሰላም ለሰውም በጎ ፈቃድ የሚዘጋጅ መሆኑን በውል ያለማጤን ችግር ነው፡፡ በተለይ የመምሪያው ሓላፊ ችግር ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ለመምሪያው የተፈጠሩ እንጂ መምሪያው ለእነርሱ የተፈጠረ አድርጎ ያለማሰብ እንደሆነም እናስባለን፡፡ ይህ ደግሞ ሰንበት ትምህርት ቤቶችንና ማኅበራትን የማገልገል ሳይሆን የመግዛት፤ በግለሰቦች ፈቃድም ላይ ተደግፈው እንዲሔዱ የማስገደድ ዝንባሌን አስከትሏል፡፡ ይህ እየተባባሰ ከመጣ ደግሞ ወጣቶች ዓለሙ እያስከተለባቸው ባለው ጫና ላይ የታከለ የውስጥ ፈተና ስለሚሆን ጥያቄ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በሰንበት ትምህርት ቤቶችና በማኅበራት ታቅፈው የጊዜያቸውን ፈተና ለመቋቋም ለተሰለፉ፣ የሚሰጣቸውን ሃይማኖታዊ አገልግሎት በጉጉት ለሚጠባበቁ ወጣቶች ቤተክርስቲያን የአገልግሎት አሰጣጧን በመፈተሽ ማስተካከያ ማድረግ አለባት እንላለን፡፡ ለዚህ ስምረት ደግሞ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን ተሞክሮ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ለዚህም ችግሮችን ከመቅረፍና ዘመኑን የዋጀ ተአማኒነት ያለው አሠራር ከመዘርጋት አንጻር የሚመለከታቸው የቤተ ክህነቱ አካላት ገንቢ የሆነ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ በተለይ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ማኅበራት የልባቸውን የሚያደርስ፣ ቤተክርስቲያንን የሚፈለገው ስኬታማ ደረጃ ላይ ለማድረስ የምናደርገውን እልህ አስጨራሽ እንቅስቃሴ የሚያፋጥን አመራር ማደራጃ መምሪያችን እንዲሰጥ ግፊት ማድረግ አለብን፡፡

ከምንም በላይ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት የማደራጃ መምሪያው አገልግሎት ተቀባዮች በመሆናቸው አገልግሎት የሚሰጣቸውን መምሪያ በሚያቅደው ዕቅድ ላይ የመወያየት፣ በአጠቃላይ የአፈጻጸም ሪፖርቱን የመገምገም፣ በየጊዜው ያለበትን አቅም እየፈተሹ በደካማ አሠራሩ የማሻሻያ አስተያየት የመስጠት ወዘተ ሓላፊነትና ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ቃለዐዋዲው ባስቀመጠው መሠረት የተሰጠውን ሓላፊነት ለመወጣት በየደረጃው ላሉ የማደራጃ መምሪያው ተወካዮች በቂ ድጋፍ እየሰጠ ተግባሩን ለማከናወን የሔደበትን ርቀት መለካት ይገባናል፡፡ ተጠሪ ለሆነለት አካል ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ሊሰጣቸው ቃልኪዳን ለተቀበለባቸው ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራትም ሪፖርት እያቀረበ የሚመዘንበትን አሠራር ለማስፈን መጣር ይኖርብናል፡፡

በዋናነትም ቅዱስ ሲኖዶስ ለማደራጃ መምሪያው ሊቀ ጳጳስ በመመደብ የጀመረውን ትኩረት የመስጠት እንቅስቃሴ፤ በቀጣይም የአገልግሎት ተቀባዮቹን የማኅበራትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አስተያየትና በጎ ፍላጎት ተቀብሎ እየመከረ ማስተካከያ በመስጠት ሊያጠናክረው እንደሚገባ ማሳሰብ ይጠበቅብናል፡፡ ቤተክርስቲያን ይህን ታላቅ ሓላፊነት የጣለችበትን መምሪያ በብቁ የሰው ኃይል፣ የበጀትና የማቴሪያል አቅምም እንዲኖረው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንላለን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከእነዚህ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተነጥላ የምትሰጠው አገልግሎት፤ ለአገልግሎቱ የምታስተባብረው ቅድሚያ የሚሰጠው አካል አለ ብለን እናምንም፡፡ ወጣቶች የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ብርቱ አገልጋዮች ለነገው ትውልድ ከማስረከብ አንጻርም የቤተክርስቲያን ማኅበረሰቡ እምብርት ናቸው፡፡

ስለዚህ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚኖረንን ድርሻ ከማስጠበቅ አንጻር በየደረጃው ካለው የቤተክርስቲያን አስተዳደር አካላት ጋር በመምከር በዚሁ ረገድ ያለንን የጸና አቋም ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በመግለጽ አገልግሎታችንን የሚያስተባብረው መምሪያ የአገልግሎት ተቀባዮችን በጎ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ያአሠራር ማሻሻያ እንዲደረግበት፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቤተክርስቲያኒቱ የተለያዩ መምሪያ ሓላፊዎችና ሠራተኞች በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ያሉ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር አካላት ሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መመሪያ እንቅስቃሴ አሁን እያደገ የመጣውን የቤተክርስቲያኒቱ ወጣቶች የአገልግሎት ተሳትፎን የሚመጥን አለመሆኑንና ከዚህም አልፎ በመምሪያው በሓላፊነት ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች አፍራሽ በሆነ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመግባታቸው ያለውን አሠራር መሸከም የማይቻልበት ደራጃ ላይ እየተደረሰ መሆኑን እንዲረዱን ይፈለጋል፡፡

ብዙ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶችንም እያደራጀ ውጤታማ ሥራ ከመሥራት ይልቅ፤ የተደራጁትም እንዲፈርሱ፣ ለግለሰቦች ግልጽና ስውር ፍላጎት እንዲንበረከኩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰው እንዲታዘዙ ለማድረግ ጥረት እየተ ደረገ ነው፡፡ በዚሁ ሁሉ ምክንያት ወጣቶች ጊዜው ካስከተለባቸው ፈተና በላይ በአሠራርና በቢሮክራሲ ስም ከፈተናው ለማምለጥ ከተሰበሰቡበት መርከብ ለማስወጣት የሚደረገው ጥረት አሳሳቢ ሆኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህ አስቀድመን የጠቀስናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር አካላት በማደራጃ መምሪያው ስም የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦችን ሩጫ በመግታት ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ የቤተክህነት ወገኖች የሚያከብሯቸውን፣ ተከብረውም እንዲኖሩ የሚፈልጉ ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤትና ማኅበራት አባላትን ጥያቄዎችና ስሜቶች በአግባቡ እያጤኑ መሔድ የቤተክህነቱ ወገኖች ሁሉ ሓላፊነት ነው፡፡ ይህም በዘላቂነት ከምእመናን ጋር ቤተክህነቱ ለሚያደርገው ግንኙነትና አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ተረድተው የመምሪያው አሠራሮች እንዲስተካከሉ መምከር አለባቸው እንላለን፡፡ ቤተክርስቲያንን ለትውልድ ለማስረከብ ተረካቢውን ትውልድ ትኩረት ሰጥቶ በአግባቡ  መቅረጽና ማደራጀት ተገቢ ነውና፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን አባላቱ በጋራም፣ በተናጠልም በየአጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቱና በመዋቅራቸው የሚያደርጓቸውን አገልግሎቶች በስፋት የማስቀጠሉን ጥረት አጠናክረው እንደሚሔዱ እየገለጸ ለአጠቃላዩ የወጣቶች የአገልግሎት ተሳትፎ ማደግና ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን በትጋት እየተንቀሳሱ መሆኑን መግለጽ ይፈልጋል፡፡