005siklet

ሕማማተ እግዚእነ በልሳነ አበው /የጌታችን መከራ በሊቃውንት አንደበት/

ሚያዝያ 1 ቀን 2007 ዓ.ም.

005sikletየእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ አለ

ታመመ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፣ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡

ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ሁሉን ያጠግባል፡፡ አይራብም፣ አይጠማም፣ አይደክምም፣ አያንቀላፋም፣ አይታመምም፣ አይሞትም ሕይወትን ለሁሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ፡፡

ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የወልድን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ

እጆቹን፤ እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ ሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማስተስረይ መከራ ተቀበለ እንዳለ፤ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲሆን በሥጋ የታመመ ነው፡፡ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል አለ፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው ሁሉ መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፡፡

የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ከላከው ሲኖዶሳዊ መልእክት የተገኘ

እርሱ መቼም መች ከመለኮቱ ሳይለይ የሰውነትን ሥራ ሁሉ ገንዘቡ አደረገ፡፡ ይኸውም መራብ፣ መጠማት፣ መንገድ በመሔድ መድከም፣ በመስቀል ላይ መሰቀል፣ በብረት ችንካር መቸንከር ነው፡፡ በሰውነቱ መቸም መች ሰው ነው፣ በአምላክነቱም ሰውን የፈጠረ ነው፡፡ ግን ከማይከፈል ተዋሕዶ በኋላ መከፈል የለበትም፡፡ ሰው እንደ መሆኑ ስለ እኛ የታመመው የሞተው እርሱ ነው፡፡ በመለኮቱ ግን መቸም መች አይታመምም አይሞትም፣ ሕማምንና ሞትንም አይቀበልም፡፡ በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፡፡ ሲኦልንም የበዘበዘው እርሱ ነው፡፡

የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ አለ

ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡

ሲኦል ተነዋወጠች፣ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፣ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ ክብርት ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት በርሷ ያለውንም ሁሉ ጠበቀ፡፡

ስለ ፍጥረት ሁሉ ሥጋውን በመስቀል እንደተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፤ ፍጥረትንም ሁሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡

ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሊቃውንት በአንድ ልብ እንዲህ አሉ

ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ ያይደለ፣ በባሕርዩ ከአባቱ ጋር አንድ የሚሆን፡፡ ሁሉ የተፈጠረበት ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ፣ በሰማይ በምድር ያለውም ቢሆን፡፡

እኛን ስለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ፡፡

የሠላሳ ዘመን ጎልማሳ ሆኖ በጶንጦስ ሰው በጲላጦስ የሹመት ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፣ ስለ እኛም ታመመ ሞተ ተቀበረ፡፡

የቂሣርያ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ባስልዮስ እንዲህ አለ

ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፣ ተጠማ እንጂ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን ከመጸብሐን ጋር በላ ጠጣ፣ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፣ እጁን እግሩን ተቸነከረ፣ ጎኑን በጦር ተወጋ፣ ከእርሱም ቅዱስ ምስጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ /ወጣ/፡፡

የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንዲህ አለ

የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፣ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም ሁሉ የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንዳይናገር አልተናገረም፣ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፡፡

ሰማዕት የሆነ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ፊልክስ እንዲህ አለ

በሥጋ መወለድ፣ በመስቀል መከራ መቀበል፣ መሞት መነሣት፣ ገንዘቡ የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ በመስቀል ላይ ሳለ ከጥንት ጀምሮ በመቃብር ያሉ ሙታንን ሁሉ አስነሣ፡፡

የሮማ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ አቡሊዲስ እንዲህ አለ

ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፣ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፣ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሁሉ ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለሁሉ ሕይወትን ሰጠ፡፡

የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አዮክንድዮስ እንዲህ አለ

በመስቀል በሥጋ ተሰቅሎ ሳለ ለመለኮት ከሥጋ መለየት የለበትም፡፡ አንዲት ሰዓትም ቢሆን የዐይን ጥቅሻ ያህል ስንኳ ቢሆንም መለኮት ከትስብእት አልተለየም፣ በመቃብር ውስጥ በሰላም መለኮት ከትስብእት አልተለየም፡፡

የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤራ ቅሊስ እንዲህ አለ

ከአብ ጋር አንድ እንደ መሆንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ ከእኛ ጋር አንድ እንደመሆንህ በፈቃድህ የሞትክ አንተ ነህ፡፡

በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፣ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፡፡ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርክ አንተ ነህ፣ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፡፡

ከሙታን ጋር የተቆጠርክ አንተ ነህ፣ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፣ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርክ አንተ ነህ፣ በዘመኑ ሁሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፡፡

በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ የእግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፡፡

የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ

ኃጢአታችንን ለማሥተሰረይ በሥጋ እንዲህ ታመመ፣ እንደሞተ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ እናምናለን፡፡

የቆጵሮስ ደሴት ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንዲህ አለ

ነብይ ዳዊትም ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም አለ፡፡ ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፣ የቀና ልቡና ዕውቀት በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ፡፡ ዳዊት እንደተናገረው እውነት ሆነ፣ ነፍስ መለኮትን ተዋሕዳ ወደ ሲኦል ወርዳለችና፣ ሥጋም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ሳለ መለኮት ከሥጋ አልተለየም፡፡ አምላክ ሰው የመሆኑን እውነት ያስረዳ ዘንድ፣ መለኮት ነፍስን ተዋሕዶ በአካለ ነፍስ የሲኦል ምስጢርን ገልጦ ፈጽሟልና በሲኦልም በቁራኝነት አልተያዘምና፡፡

ምንጭ ስምዐ ተዋሕዶ፤ ሚያዝያ 1-5 ቀን 2007 ዓ.ም.