ger.hawira 2006 2

ሐዊረ ሕይወት በሀገረ ጀርመን ተካሄደ

 ግንቦት 15 ቀን 2006 ዓ.ም.

ከጀርመን ቀጣና ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የጀርመን ቀጣና ማእከል በአውሮፓ የመጀመሪያውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ከግንቦት 8-10, 2006 በክሩፈልባክህ (Kroeffelbach) በሚገኘው የኮፕቲክger.hawira 2006 2 ቅዱስ እንጦንስ ገዳም (Sankt-Antonius Kloster) በደማቅ ሁኔታ አካሄደ።

በዚህ ከ80 በላይ ምእመናን በተሳተፉበት መርሐ ግብር ላይ ሰፊ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በተለይ ነገረ ድኅነት እና መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የተሰጡት ጥልቅ ትምህርቶች ተሳታፊዎች በጉዳዮቹ ላይ የነበራቸውን እውቀት በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደጉ እና ታዳሚው ሐዊረ ሕይወት በቅርቡ ይደገምልን የሚል ጥያቄን እንዲሰነዝር ያነሳሱ ነበሩ። በተጨማሪም መዝሙራት በዘማርያንና በሕብረት የቀረቡ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ቤት ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋትበተለይም በተመረጡ ጠረፍና ገጠር አብያተ ክርስቲያናት ላይ አቅዶ እያከናወነው ስላለው የስብከት ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም ገለጻ ተደርጓል።

ወደ ጀርመን ሀገር የሚመጡ አዳዲስ ስደተኞችን ከቅድስት ቤተክርስቲያን ለማስኮብለል የሚደረገውን የተቀናጀ ዘመቻም ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ይህንንም ለመከላከል ቀጣና ማእከሉ ከሀገረ ስብከቱ፣ ከሌሎች አገልጋዮች እና ከምእመናን ጋር በመተባበር የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ከተሳታፊዎች ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። አርብ ምሽት የተጀመረው መርሐ ግብር እስከ ቅዳሜ ምሽቱ 5 ሰዓት ድረስ በትምህርት፣ መዝሙርና ውይይት ከቀጠለ በኋላ ፍጻሜውን ያገኘው እሁድ ከግብፃውያን አባቶች ጋር ቅዳሴ በመሳተፍ ነበር።

ger. hawira 2006
በስደት አገር ይህንን የመሰለ ትልቅ ገዳም ሰርተው ይህንን የተሟላ ሊባል የሚችል ማረፊያ ቦታቸውን በነፃ የሰጡን የግብፃውያን ትጋት ለቦታው አዲስ የሆኑ ታዳሚዎችን ያስደመመ ሲሆን የሊቀ ጳጳሱ አቡነ ሚካኤል ደግነትና ትህትናም በቀላሉ የሚረሳ አይሆንም። መርሐ ግብሩ እሁድ ከምሳ በኋላ የተፈጸመ ሲሆን ሁለተኛ የምንገናኘው መቼ ነው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ይቆያል። ቀጣና ማእከሉ ለዝግጅቱ መሳካት የተለያዩ ድጋፍ ያደረጉ ምእመናንን ፣ በአገልግሎቱ የተሳተፉ መምህራንንና በገዳሙ በነጻ መጠቀም እንድንችል ለፈቀዱልን ለብፁዕ አቡነሚካኤል ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡