Kalitie.GIF

ለጥምቀት ወጥታ የቆየችው ታቦት ወደ አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ገባች

የቃሊቲ ቁስቋም ማርያም ታቦተ ሕግ ባለፈው ጥምቀት ወጥታ ተመልሳ መግባት ፈቃዷ ባለመሆኑ የተፈጠረውን የምእመ ናንና የካህናት ጭንቅ፣ ሐዘን፣ ድንጋጤ በብዙ የሚክስ የደስታ ዕለት፡፡ ሐምሌ 25 ቀን 2001 ዓ.ም፡፡

Kalitie.GIF

 
በዚህ ዕለት ማለዳ ጀምሮ ወደ ደጇ ይጎርፍ የነበረው ምእመን አካባቢውን ጠጠር መጣያ አሳጥቶታል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ጸሎት፣ ምሕላ. . . ሲደረግ ተውሎ ከቀኑ 9፡30 ለሰባት ወራት ከርማ ከነበረችበት ድንኳን በብፁዓን አባቶች፣ በካህናትና በበርካታ ምእመናን ታጅባ የወጣችው ታቦተ ሕግ የምእመናኑን የደስታ ስሜት እጥፍ ድርብ አድርጋው ነበር፡፡

በእልልታው በዝማሬውና በምስጋና ታጅባ ከድንኳኑ አቅራቢያ ወደ ተሠራላት አዲስ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ስታመራ እርኩስ መንፈስ ያደረባቸው ብዙዎች ከተለያየ አቅጣጫ ሲጮሁ፣ ሲንፈራገጡ፣ ሰውነታቸውን ሲንጡ እና እልልታውን ለማወክ ሲጥሩ የተስተዋለበት ይህ አጋጣሚ በእርግጥም የእመቤታችን ክብር ምን ያህል እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያስችልም ነበር፡፡
በእመቤታችን ትእዛዝ አቶ ክንፈ ሚካኤል ረታ በተባሉ ምዕመን በተሠራው አዲሱ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ዑደት አድርጋ ወደ መንበረ ክብሯ የገባችው ታቦተ ቁስቋም ማርያም ታቦተ መድኃኔዓለም እና ታቦተ ጊዮርጊስንም አስከትላ ነበር፡፡

በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ይህ ዕለት ልዩ ያደረገው ብራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዋዜማው ዓርብ ምሽት ሦስት ነጫጭ ርግቦች የእመቤታችን ታቦት በከረመበት ድንኳን ላይ ማረፋቸው እና ከዚያ ቀደም ብሎ የንብ መንጋ ድንኳን ውስጥ መክተማቸው ነው፡፡
ዕለት ተዕለት የሕንፃ ቤተክርስቲያኑን ሥራ በመከታተል እመቤታችን ያዘዘቻቸውን የፈጸሙት አቶ ክንፈ ሚካኤል ረታ በዓውደ ምሕረቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ «ታቦተ ቁስቋም ማርያም በድንኳን እያለች እኛ ቤታችን አንገባም ብላችሁ ከእርሷ ጋር የቆያችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትና ምእመናን እንኳን ደስ አላችሁ!» ብለዋል፡፡

መጋቢት 29 ቀን 2001 ዓ.ም ለዮሐንስ አጥቢያ እመቤታችን ተገልጣላቸው ከዚህ ቀደም አስተውለውት ከማያውቁት ቦታ ሕንፃ ቤተክርስቲያኑን እንዲያንጹ ባዘዘቻቸው መሠረት በሁለት ወር ከ 10 ቀናት ውስጥ ሠርተው ያጠናቀቁት እርሳቸው የማያውቋቸው እግዚአብሔር የሚያውቃቸው እየተራዷቸው መሆኑንም አቶ ክንፈ ሚካኤል ተናግረዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ ¬ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት በክብረ በዓሉ ላይ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት «እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆቼ ሳይሰባሰቡ፣ እኔ እዚህ መሆኔን ሳያውቁ ሕሊናቸውና መንፈሳቸው ሳይደሰት አልነሳም የማለት ምልክት መስጠቷ እንጂ ድንኳን መክረም እምቢተኝነት አይደለም» ብለዋል፡፡  
«ታቦተ ቁስቋም ማርያም አልነሣም ማለቷ የተቸገሩትን ለማማለድ፣ የታመሙትን ለመፈወስና በአካባቢው የምትሠራው ብዙ ተዓምራት እንዳለ ለማሳየት ድንኳን ከርማለች፤ ዛሬ ግን ወጥታ ልጆቿን ባርካለች፤ እንኳን ደስ ያላችሁ!» ያሉት ቅዱስነታቸው፤ ዕለቱ እናታችን ቅድስት ማርያም በየጊዜው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እየተገለጸች ከልጆቿ የምትነጋገርበት ሀገራችን ሀገረ እግዚአብሔር መሆኗን የምንገነዘብበት ዕለት መሆኑን ተና ግረዋል፡፡ ይህ ሥፍራ የቃሊቲ ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም መሆኑንም አብስረዋል፡፡
በዚህ ታሪካዊ ዕለት ከተገኙት ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በሰጡት ትምህርት የቅድስት ድንግል ማርያም ድንቅ ሥራ ተነግሮ የማያልቅ ነው፡፡

«እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሀገራችንና ከሕዝባችን በተአምሯ፣ በበረከቷ ያልተለየችን የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ናት» ያሉት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሕዝባችን «ሰአሊ ለነ ቅድስት» የሚለው አጠራሩ አማላጅነቷን የቱን ያህል እንደሚያምንበት ያሳያል ብለዋል፡፡
ታቦተ ቁስቋም በቦታው ድንቅ ተአምር እንዲሠራበት ስለመረጠች ድንኳን መቆየቷን፣ በሰው እጅ ተሠራ ለማለት የሚያዳግት ሕንፃ ቤተክርቲያን በአጭር ጊዜ ተሠርቶ መጠናቀቁ፣ እመቤታችን በተአምሯ የሠራችው መሆኑን እንደሚያሳይ የገለጹት ብፁዕ ነታቸው፤ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ያሠሩት ምእመን ዕድለኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የእመቤታችንን ተአምር በመንገር ከደጇ ጠፍተው የማያውቁት አገልጋይ አባ ገብረሥላሴ መለሰ በሰጡት አስተያየት «ጸሎተ ምህላችንን ተቀብላ እመቤታችን ፈቃዷን ስለገለጸችልን ደስታችን ወሰን የለውም. . .» ነው ያሉት፡፡
«ሰኔ 25 ቀን 2001 ዓ.ም ታቦተ ቁስቋም ባረፈችበት ድንኳን ውስጥ አንዱን ንብ ተከትለው ጥቂት ንቦች ገቡ፤ ሐምሌ 16 ቀን ጀምሮ ግን ሦስት ቀፎ የሚገመት የንብ መንጋ ወንበሯን ተረክቦ ዛሬ ድረስ ይገኛል፡፡ ይህን ስናይ እመቤታችን ልጆቿን ልትጠራ፣ በረከቷን ልታወርድ መሆኑን ተረዳን፡፡ አዲሱ ሕንፃ ቤተክርስቲያን እንደ ምትገባልንም እምነታችን ሆነ፡፡ እንዳሰብነውም ተሳካ. . .» ያሉት አባ ገብረሥላሴ «ሐምሌ 24 ምሽት ድንኳን ላይ ያረፉት ሦስት እርግቦችም ሌላው ምልክታችን ነበር» ይላሉ፡፡

ጥር 16 ቀን 2001 ዓ.ም ታቦቷን አንግሠው ዳግም ወደ ቤተመቅደስ እንድትገባ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የቀረው ዛሬ ግን የእመቤታችን ፈቃድ እጅግ ያስደሰታቸው መሪጌታ ቤዛ የሻው «ሐዘናችን በደስታ ተለውጧል፡፡ ይህን ተዓምር ማየቴ ዕድለኛ ነኝ፡፡ ለእመቤታችን ክብር ምስጋና ይግባት» ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ ዕለት በእርግጥም የደስታ ዕለት ነው፡፡ ብዙዎች የሚሰጡት አስተያየት ከደስታ እንባ ጋር ነው፡፡ በዕለቱ እየተጨባበጡ፣ እየተቃቀፉ ደስታቸውን የሚገልጹ በዓውደ ምሕረቱ በእመቤታችን የተደረገላቸውን ተአምር የሚመሰክሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡

እሑድ ሐምሌ 26 ቀን 2001 ዓ.ም የቃሊቲ ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ሲከበር እጅግ ከፍተኛ ሕዝብ እንደተገኘም ታውቋል፡፡

ከአዘጋጁ- ባለፈው የጥምቀት በዓል ከቅዱስ ሚካኤል ታቦት ጋር ወደ ጥምቀተ ባሕር ሥፍራ ወጥታ ተመልሳ ወደ ቤተመቅደሷ ሳትገባ በራሷ ፈቃድ ድንኳን ስለከረመችው የቁስቋም ማርያም ታቦት ታሪክ በተከታታይ ስንዘግብ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ወደፊትም በዚሁ ሥፍራ ስለተከናወኑ ገቢረ ተዓምራት የምንገልጽ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር