ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ …/ዮሐ.3-19/

ብርሃን ወደ ዓለም ስለመጣ፣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው፡፡ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፡፡ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጐ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፡፡ /ዮሐ.3-19/

ለዚህ እትም መልእክታችን መግቢያ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ከእውነት ይልቅ ሐሰትን የመረጡ ሰዎችን ማንነት ለመግለጥ የተናገረውን አምላካዊ ቃል መርጠናል፡፡ ብርሃን እውነት፤ ብርሃን የጠራ አሠራር፤ ብርሃን የዘመድ አሠራር ባላንጣ፤ ብርሃን የሕገ ሲኖዶስ መከበር፤ ብርሃን የቤተ ክርስቲያን ልዕልና መገለጫ ነው፡፡ ጨለማ ግን የብርሃን ተቃራኒ ነው፡፡

ካሳለፍነው ወርኃ ግንቦት መጋመሻ ጀምሮ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን የአስተዳደር ችግር በሠለጠነ መንገድ፣ በመወያየት፣ በመተማመን ለመፍታት ሁሉም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ባለፈው እትም ከመንበረ ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት የወጣውን መረጃ መሠረት በማድረግ አሰንብበናል፡፡

በቤተ ክርስቲያን አባቶች ዘንድ ተፈርቶ ይፋ ሳይወጣ ለዘመናት ሲጉላላ የቆየው የአስተዳደር ችግር፣ የቤተ ዘመድ አሠራር፣ ሙስና፣ ተገቢውን ሰው በተገቢ ቦታ አለመመደብ፣ የተዝረከረከ የሒሳብ አሠራር እና ተገቢ ያልሆነ የሀብት አጠቃቀም ችግር ይፋ ወጥቶ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ በቃለ ጉባዔ ሰፍሮ መቀመጡ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን ዕድገት አንድ እርምጃ ነው፡፡

«አትስረቅ፣ መመለጃ አትቀበል፣ እውነቱን እውነት በሉ» የተባሉት አምላካውያት ቃላት መመሪያዋ በሆነ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሠናይ ይልቅ እኩይ ሥነ ምግባሮች በቅለው ሐዋርያዊ ጉዞዋን በፍጥነት እንዳይካሔድ የኋሊት ሲጓተት እያዩ «ሆድ ይፍጀው» ብለው ማለፍ ቀርቶ ብፁዓን አባቶች ችግሮችን አፍረጥርጠው መነጋገራቸው ያስደስታል፡፡

በቤተ ክርስቲያን አባቶች መኖራቸው የታመነባቸው ችግሮች እንዲፈቱ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሥራ አስፈጻሚ አባላት መመረጣቸውም ይታወሳል፡፡ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጣቸው ሓላፊነት መሠረት የቤተ ክርስቲያን ችግር ለመፍታት ሲንቀሳቀሱ በተፈጠረው አለመግባባት ችግሩ ወርኃ ሐምሌ ላይ ደርሷል፡፡ እኛም የተፈጠረው ችግር ከምንም በላይ የቤተ ክርስቲያን ክብር ባስቀደመ መልኩ እንዲፈታ ሐሳባችን ሰንዝረናል፡፡ በመግቢያችን እንደጠቀስነው «ብርሃን ወደ ዓለም ስለመጣ» የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር ይፈታ ስለተባለ፤ ሥራቸው ክፉ የነበረው «የዘመድና የብልሹ አሠራር ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር መፍታት ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ወደ ብርሃን አንመጣም አሉ፡፡ ጨለማን ተገን አድርገው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ቤት መዝጊያ ሰበሩ፣ ፎከሩ፣ አስፈራሩ፣ ዛቱ፣ ቆይ ትኖራላችሁ አሉ፡፡ ዛቻና የድብደባ ሙከራ የተፈጸመባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንደገለጹት ድርጊቱ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ዝቅ ያደረገና አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው «ክፉን የሚያደርግ ብርሃንን ይጠላልና ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም» እንደተባለው  ክፉ የሚያደርጉ ቤተ ክርስቲያንን የሚመዘብሩ ሰዎች ብርሃንን ስለሚፈሩ ነው፡፡

ብርሃን እውነትን የሚፈሩ የጨለማው ቡድን አካላት፤ «በሊህ እገሪሆሙ ለኪኢወ ደም፤ ደም ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው» «ሐሳር ወቅጥቃጤ ውስተ ፍኖቶሙ፤ ጥፋት ጉስቁልና በመንገዳቸው አለ፤ የሰላም መንገድ አያውቋትምና እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም» ሲል ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት የገለጣቸው ዓይነት ናቸው፡፡ መዝ. 13-6፡፡ በኃይል፣ በዛቻና በማስፈራሪያ የቤተ ክርስቲያን ችግር ስለማይፈታ የእነዚህ ቡድኖች ዓላማ ቤተ ክርስቲያን ወደተሳ ሳተ ጐዳና የሚመራ ነው፡፡ የጨለማ ቡድን ዘመቻ ከቤተ ክርስቲያን ልጆች አልፎ ወደ ብፁዓን አባቶች አምባ መደረሱ እጅግ ያሳዝናል፡፡

ሕገ ሲኖዶስ እንዳይከበር እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የጨለማው ቡድን አባላት» እውነት ተድበስብሶ እንዳይወጣ የሚያደርጉት እኩይ ጥረት ከሠመረ ቤተ ክርስቲያን «ቤትየሰ ትሰመይ ቤተ ጸሎት አንትሙሰ ረሰይክምዋ በአተ ፈያት ወሠረቅት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ትባላላች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ» አደረጋችኋት፡፡ የሚለው ዕጣ ይገጥማታል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከጨለማ አስተዳደር ወደ ብርሃን እንድትወጣ «እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጐ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል» እንደተባለ የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር እንዲፈታ ጨለማ የሆኑ ወደ እውነት እና ወደ ብርሃን መምጣት አለባቸው፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተመረጠው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሥራውን እንዲቀጥል እገዳ እንደተነሳለት ከመንበረ ፓትርያርክ የተሰጠው መግለጫ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የመረጣቸውና ሓላፊነት የተሰጣቸው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አሉ የተባሉ ችግሮች እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ሓላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ያለው ብልሹ አሠራር መፈታት ከምእመናን ጀምሮ እስከ መንግሥት አካላት እንደ ሚደግፉት እናምናለን፡፡

ችግሩን ለመፍታት ሐሳብ የሰጡ ብፁዓን አባቶችን የማሸማቀቅ አሳፋሪ ተግባር ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ስለተፈጸመባቸው መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡ የብፁዓን አባቶች ዓላማ መንፈሳዊ ዓላማ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ችግር ከመፍታት ውጪ የተለየ አንዳች ዓላማ እንደሌላቸው ከሰጡት ሐሳብ መረዳት ይቻላል፡፡

በመሆኑም ምንጊዜም የሕዝብን በሕይወት የመኖር መብት የሚያስከብረው መንግሥት ጨለማን ተገን አድርገው የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ነፃነት ደፍረው በብፁዓን አባቶቻችን ላይ የመዝጊያ ሰበራ፣ የድብደባ ሙከራ የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር አውሎ የእርምት ርምጃ መወሰድ አለበት፡፡

ከሀገር ሀገር ዞረው «በእንተ ስማ ለማርያም» ብለው የተማሩ አባቶች ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ በእግርና በፈረስ ተዘዋውሮ ቤተ ክርስቲያን ያገለገሉ «ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሕገ ሲኖዶስ ይክበር» በማለታቸው ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ የመዝጊያ ሰበራ ሲፈጸምባቸው መሰማት ቤተ ክርስቲያን ወደየት እየተጓዘች ነው ያሰኛል፡፡

በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች መከራ መቀበል የአባቶች ሕይወት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል በቅዱስ መሰዊያው ፊት ቃል ኪዳን የገቡት አባቶቻችን ስለቤተክርስቲያን ክብር ዛቻና እንግልት ቢፈጸምባቸው እንኳ መከራውን በአኮቴት ተቀብለው ሓላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በሰላማዊ መንገድ በሠለጠነ መንገድ ችግሮች እንዲፈቱ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ መወያየት የጀመሩትን ከፍጻሜ ማድረስ አለባቸው፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት፣ የሰበካ ጉባኤ አካላት፣ በአጠቃላይ ምእመናን ምን ጊዜም እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን በማዕበል የምትገፋ መሆኗን ተረድተው በተፈጠረው ችግር መረበሽ የለባቸውም፡፡ የተፈጠረው የአስተዳደር ችግር በጠራና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እስከሚፈታ ድረስ በመረጋጋት፣ በጾም፣ በጸሎት መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡

«የገበያ ግርግር ለቀጣፊ ያመቻል» እንዲሉ የተፈጠረውን ችግር መነሻ በማድረግ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ምዝበራ፣ ዘረፋ፣ ሕገ ወጥ ድርጊት እንዳይስፋፋ ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ንብረት ንብረታቸው፤ ሕልውናዋ ሕልውናቸው ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡

 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር