ለአብነት ትምህርት ቤቶች የጽዳት እቃዎች ድጋፍ ማሰባሰቢያ ሳምንት በመካሄድ ላይ ነው

መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባበሪነት ለአብነት ትምህርት ቤቶች የጽዳት እቃዎች ድጋፍ ማሰባሰቢያ ሳምንት ከመጋቢት 21 እስከ ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በማኅበሩ ሕንፃ ላይ በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡

ተማሪው ምንም ዓይነት የምግብ፤ የመጠለያና የአልባሳት ድጋፍ ሳያገኝ ጥሬ ቆርጥሞ ፤ በሳር ጎጆ ተጠግቶ፤ በእራፊ ጨርቅ ተጠቅልሎ ትምህርቱን ይከታተላል፡፡ በቂ ምግብ ፤ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ፤ መጸዳጃ ቤት ባለማግኘቱ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችም ይጋለጣል፡፡  በአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጎልቶ የሚታየውን ችግር በተለይም ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የበሽታ ዓይነት ከግልና ከአካባቢ ንጽሕና ጉድለት የሚመጣ በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን ይህንን የጤና ችግር ለመቅረፍ 12000 /አሥራ ሁለት ሺህ/ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሐ ግብር ነድፏል፡፡     

በተነደፈው ፕሮጀክት መሠረት ለ10 የአብነት ትምህርት ቤቶች የጋራ መጸዳጃ ቤት ግንባታ ፤ ባለ 200 ግራም 12000 የልብስ ሳሙና፤ 10 ባለ 3000 ሊትር የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከር፤ የውኃ ማከሚያ ኬሚካሎች፤ ለውኃ መጠጫ፤ ለማብሰያ ፤ ለመመገቢያ ፤ ለገላና ለልብስ ማጠቢያ የሚያገለግሉ የተለያዩ መጠን ያላቸው ቁሳቁስ፤ መርፌና ምላጭ፤ . . . እንደሚያስፈልግ ከማኅበሩ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡  

የተማሪዎቹን ሕይወት ለማትረፍና ትምህርታቸውን በሚገባ ተምረው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉበት ሁኔታ ለመፍጠር በጎ አድራጊ ምእመናን በማኅበሩ ሕንፃ ላይ እሰከ ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ የበኩላቸውን ልገሳ እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል፡፡