የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፭

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፩.፭ ሥርዓተ ተክሊል

ቅድስት ቤተ ክርስቲያ፣ አምነው ለሚመጡ ምእመናን ዂሉ ጸጋ እግዚአብሔርን በነጻ ታድላለች፡፡ ለምእመናን ጸጋ የምታድልባቸው መሣሪያዎችም ‹ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን› ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህም፡- ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቍርባን፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ንስሓና ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው፡፡  ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መካከል አንዱ የኾነው ምሥጢረ ተክሊል፣ ክብራቸውን ጠብቀው የኖሩ ደናግል ጋብቻ ሲመሠርቱ የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ ክብረ ንጽሕናቸውን ጠብቀው የኖሩ ደናግል ከተጫጩና በፈቃዳቸው ለመጋባት ከተስማሙ በኋላ ጋብቻቸው በሥርዓተ ተክሊል ይፈጸማል፡፡

ከቃሉ ትርጓሜ ስንጀምር ‹ተክሊል› ማለት ‹መቀዳጀት› ማለት ነው፡፡ ይህም ሙሽራውና ሙሽራይቱ የጋብቻ ሥርዓታቸው በሚፈጸምላቸው ጊዜ እንደ ንጉሥና ንግሥት በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተው፣ የክብር ካባ ደርበው፣ በነጭ ልብስ ደምቀው መታየታቸውን ያመለክታል፡፡ ይኸውም ለሙሽሮች የሚፈጸመዉን ጸሎትና ቍርባን የሚያሳይ ሲኾን፣ አፈጻጸሙም ሥርዓተ ተክሊል ይባላል፡፡ ሥርዓተ ተክሊል ሲፈጸም ጸሎቱ፣ ልብሱ በጆሮ የሚሰማ፤ በዓይን የሚታይ ቢኾንም በሙሽሮቹና በዕለቱ በተገኙ ምእመናን ላይ የሚያድረው ጸጋና በረከት ግን በዓይን የማያዩት፤ በእጅም የማይዳስሱት፤ በጆሮም የማይሰሙት ረቂቅ ነውና ሥርዓቱ ምሥጢረ ተክሊል ይባላል፡፡

በሥርዓተ ተክሊል ጋብቻቸዉን የሚፈጽሙ ምእመናን እስከ ሞት ድረስ ላይለያዩ በፍጹም ፍቅር ይዋሓዳሉ፡፡ ሽንገላና ግብዝነት በሌለበት እውነተኛ ፍቅር ይጣመራሉ፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈሩና ወላጆቻቸውን የሚያከብሩ ልጆችንም ያፈራሉ፡፡ ጥንዶቹ የመከባበርና የመፈቃቀር፣ የመረዳዳትና የመተማመን፣ የመስማማትና የመተማመን ጸጋ ይታደላሉ፡፡ ፍቅራቸውም ወረተኛ ማለት ከጥቅማ ጥቅም ጋር የተሳሰረ ሳይኾን በመተሳሰብና በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ ይኾናል፡፡ በኑሯቸው የሚያጋጥሙ ፈተናዎችንም በጸሎትና በትዕግሥት የሚወጡበትን ጥበብ ይታደላሉ፡፡ ይህን ጸጋ በመገንዘብ በጋብቻ ሕይወት ለመኖር ዓላማውና ዕቅዱ ያለን ዂሉ በዘፈቀደ መንገድ ከመነዳትና ሰይጣናዊ ባህልን ተከትሎ ከመጥፋት ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በመጠበቅና አንድ ለአንድ በመጽናት በዚህ ቅዱስ ሥርዓት ጋብቻችንን መመሥረት ይገባናል፡፡ በዚህም እኛ ተጠቅመን ለመጭው ትውልድም አርአያና ምሳሌ ለመኾን እንችላለን፡፡

ከላይ እንደ ተመለከትነው ምሥጢረ ተክሊል ለደናግል ማለትም ክብረ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለኖሩ ክርስቲያኖች ብቻ የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ ሥርዓቱ በዓላማ ጸንተው ክብራቸውን ጠብቀው ለቆዩ ዲያቆናትና ምእመናን ይፈጸማል፡፡ ከዚህ ላይ የዲያቆናት የጋብቻ ሥርዓት ከምእመናን የተለየ መኾኑን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ምክንያቱም ወደ መዓርገ ቅስና የሚሸጋገሩበት አንዱ መሥፈርት ነውና፡፡ በሕግ የተወሰኑ ማለትም ትዳር የመሠረቱ ዲያቆናት (ቀሳውስት) በሞት ወይም በሌላ አስገዳጅ ምክንያት ከትዳር አጋራቸው ጋር ቢለያዩ ሁለተኛ ሚስት ማግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ ካገቡም በመዓርገ ክህነት ማገልገል አይችሉም፡፡ ስለዚህም ዲያቆናት ሚስት በሚያጩበት ጊዜ ከምእመናን በተለየ መልኩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

በእርግጥ ምእመናን እንዲሁ ሳይጠናኑ ይጋቡ ለማለት ሳይኾን የክህነት ሕይወት ከምእመንነት ሕይወት ስለሚለይ ዲያቆናት አስተውለው ወደ ሕይወቱ እንዲገቡ ለማስታዎስ ነው፡፡ ምእመናን ከትዳር አጋራቸው ጋር በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ቢለያዩ ሁለተኛ ማግባት ይፈቀድላቸዋል፤ ዲያቆናት (ቀሳውስት) ግን ከአንድ ጊዜ በላይ ሚስት ማግባት አይችሉም፡፡ በክህነታቸው ለመቀጠል የግድ መመንኰስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕጉን ተላልፈው ወይም ፈቃደ ሥጋቸዉን ማሸነፍ አልችል ብለው ሁለተኛ ጋብቻ ከመሠረቱም ሥልጣነ ክህነታቸው ይያዛል (ይሰረዛል)፡፡ ከቀሳውስት (ዲያቆናት) በተለየ ሥርዓት ምእመናን ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ቢፋቱ የተለያዩበት ምክንያት ተጣርቶ ሁለተኛ ጋብቻ መመሥረት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁለተኛ ጋብቻ በቍርባን እንጂ በተክሊል አይፈጸምም፡፡ ምክንያቱም ምሥጢረ ተክሊል ተጋቢዎቹ (ሁለቱም) ድንግልናቸውን አክብረው ከቆዩ ብቻ የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነውና፡፡

፩.፮ ሕይወት በጋብቻ ወቅት

የጋብቻ ሕይወት፣ በእግዚአብሔር ፈቃድና በሰዎች ምርጫ የሚመሠረት የአንድነት ኑሮ ነው፡፡ በጋብቻ ከተዋሐድንበት ጊዜ ጀምሮ ያለው ወቅት ከነጠላነት ወደ ጥንድነት፣ ከብቸኝነት ወደ ሁለትነት ብሎም ወደ ሦስትነት (ልጅ ሲመጣ) የምንሸጋገርበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ከቀድሞው በበለጠ መልኩ በጾም በጸሎት መትጋት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ወቅት ለራሳችን ብቻ ሳይኾን ለትዳር አጋራችን ብሎም ለልጆቻችን ሕይወት የምናስብበት የሓላፊነት ጊዜ ነውና፡፡ በመኾኑም ከቤት ጀምሮ እስከ ጎረቤት ያለን ማኅበራዊ ግንኙነት የጠነከረ፣ ፍቅራችንም የሠመረ መኾን ይገባዋል፡፡ ጋብቻ ከመሠረትን በኋላ ከትዳር አጋራችን ጋር ተቻችለን ሳይኾን ተስማምተን በፍቅርና በሰላም መኖር ይጠበቅብናል፡፡

በእርግጥ በኑሯችን ላይ ልዩ ልዩ ፈተናዎች ሊመጡብን ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ደዌ ሥጋ፣ ስንፈተ ሩካቤ ወይም በተፈጥሮ ሩካቤ ማድረግ አለመቻል፣ ሊፈወስ የማይችል በሽታ (ለምሳሌ ኤድስ)፣ የአባላዘር በሽታዎችና እነዚህን የመሰሉ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሉባልታ ወይም በሰዎች ጣልቃ ገብነት ለመግባባትና በአንድነት ለመቀጠል እንቅፋት የሚኾኑ ችግሮች ሊገጥሙን ይችላሉ፡፡ ለዚህም መፍትሔው ቢቻል ዂሉን ነገር ከመጋባት በፊት መወያየትና ለችግሮች መፍትሔ መስጠት ነው፡፡ የጤና እክሉ ወይም አለመግባባቱ ከጋብቻ በኋላ የመጣ ከኾነ ሕመሙን በጠበልና በሕክምና አለመግባባቱን ደግሞ በመወያየት፣ በጾምና በጸሎት መፍታት ይገባል፡፡ ከዚህ በተረፈ በየሰበቡ መጨቃጨቅም መናተረክም አስፈላጊ አይደለም፡፡

የባልና ሚስት ሕይወታቸው በአንድ አሳብ፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ ምክርና የጋራ ፈቃድ ሊመራ ይገባዋል፡፡ እንደዚሁም በመፈቃቀር፣ በመከባበር፣ በመተሳሰብ፣ በመተዛዘንና በመደጋገፍ ሊኖሩ ያስፈልጋል፡፡ ልጆችን በክብካቤና በመንፈሳዊ ሥርዓት ማሳደግም ሌላው የባልና ሚስት ሓላፊነት ነው፡፡ በአጠቃላይ ባል ለሚስቱ፤ ሚስትም ለባሏ መታዘዝ የሕይወታቸው መርሕ መኾን አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር በቤት ውስጥም ኾነ ከቤት ውጪ ክርስቲያናዊ ምግባርን ገንዘብ በማድረግ ለልጆቻቸው መልካም አርአያ ሊኾኑ ይገባቸዋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የባልና የሚስት ሕይወት እንዴት መቀጠል እንዳለበት ሲያስረዳ የሚከተለውን ትእዛዝ ከምሳሌያዊ ማብራሪያ ጋር ሰጥቷል፤ “ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ኾነ ባልም የሚስት ራስ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በዂሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፡፡ ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፡፡ ባሎች እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል፤ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፤” (ኤፌ. ፭፥፳፪-፴፫)፡፡

ከኃይለ ቃሉ እንደምንረዳው ባልና ሚስት ‹‹በአንተ ይብስ፤ በአንቺ ይብስ›› ተባብለው የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ በመፍታት፣ የሕይወት ምሥጢራቸውን በመጠበቅ በመንፈሳዊ ፍቅር መኖር ይገባቸዋል፡፡ በባልና በሚስት መካከል አንዱን የበላይ፣ ሌላውን የበታች የሚያደርግ ልዩነት ሊኖር አይገባም፡፡ ባል ስለ ሚስቱ፣ ሚስትም ስለ ባሏ ሰውነታቸዉን ለመከራ አሳልፈው እስከ መስጠት ድረስ በፍጹም ፍቅር መዋደድ ይገባቸዋል፡፡ ሁለቱም ከእናትና አባታቸው ተለይተው በአንድነት መኖር ጀምረዋልና (ዕዝራ ፬፥፳-፳፭)፡፡

ይቆየን