የደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም የ፬ቱ ትርጓሜ መጻሕፍት ምስክር ጉባኤ ቤት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት አስመረቀ።
የደብረ ልዑላን መድኃኔ ዓለም የ፬ቱ ትርጓሜ መጻሕፍት ምስክር ጉባኤ ቤት ላለፉት አምስት ዓመታት ያስተማራቸውን ፳፫ ደቀ መዛሙርት ግንቦት ፲፮/፪፳፲፰ ዓ/ም አስመርቋል።
በማማያዝ ጉባኤ ቤቱ ዘመናዊ ባለ ሁለት ወለል የጉባኤ ቤቱን መንታ ሕንጻ ማስመረቁም ተነግሯል።
የደብረ ልዑላን መድኃኔዓለም የ፬ቱ ትርጓሜ መጻሕፍት ምስክር ጉባኤ ቤት በአጼ ቴዎድሮስ መሠረት ጣይነት የተጀመረና ጥንታዊ ጉባኤ ቤት ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት መቶ ዓመታት ተቋርጦ መቆየቱ ተነግሯል።
ከመቶ ዓመታት መቋረጥ በኋላ በ ፪፳፲፩ ዓ/ም በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሚካኤል መልካም ፈቃድ እና በሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ መሠረት ጣይነት ጉባኤ ቤቱ እንደገና ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል።
ጉባኤ ቤቱ በመጀመሪያ ዙር ፳፪ ደቀ መዛሙርትን አስተምሮ ያስመረቀ ሲሆን ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ፳፫ ደቀ መዛሙርትን አስመርቋል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ቃለ ምዕዳን የሰጡት የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከደቀ መዛሙርቱ ብዙ እንደምትጠብቅና ደቀ መዛሙርቱም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንዲያገለግሏት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን ቀሲስ ምሕረት ሞላ በበኩላቸው ሀገረ ስብከቱ ከጉባኤ ቤቱ ጋር ተናቦ እየሠራ መሆኑን ገልጸው ለዚህም አጥጋቢ ፍሬ ማየት እንደተቻለ ተናግረዋል።
የምስክር ጉባኤ ቤቱ መምህር መምህረ መምህራን በጽሐ ዓለሙ ” እስካሁን እየተማራችሁ ትፈተኑ ከነበረበት እየተፈተናችሁ ወደ ምትማሩበት ትሄዳላችሁ ” በማለት ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን አደራ እንዲወጡ አሳስበዋል።
መምህረ መምህራን በጽሐ ዓለሙ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት በፍጹም መንፈሳዊነት ሕዝባቸውንና ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ አደራ ያሉ ሲሆን ተመራቂ ደቀ መዛሙርትም ምእመናኑን እጅ በመንሳትና ቃል በመግባት የመምህራቸውን አደራ ተቀብለው በይፋ ተመርቀዋል።
ማኅበረ ቅዱሳን ለጉባኤ ቤቱ አንድ መምህርና ለ፳፫ ደቀ መዛሙርት ወርኃዊ ድጎማ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ሰማንያ አሐዱ ግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ ለእያንዳንዳቸው ተመራቂ ደቀ መዛሙርት በስጦታ አበርክቷል።
በምርቃት መርሐ ግብሩ ንግግር ያደረጉት በማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች ዳይሬክተር ዲ/ን ደረጀ ጋረደው በበኩላቸው “ጉባኤ ቤቱ የቀደምት መምህራንን ታሪክ ዳግም እውን አድርጎ ያሳየ መሆኑን አንስተው ተመራቂ ደቀ መዛሙርት የዚህ ታሪክ ተካፋይ ሆናችሁ በመመረቃችሁ ማኅበረ ቅዱሳን ታላቅ ደስታ ይሰማዋል” ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉባኤ ቤቱ ዘመናዊ የሆነና በውስጡ በርካታ ክፍሎችን የያዘ ባለ ሁለት ወለል መንታ ሕንጻ ማስመረቁ ተነግሯል። የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሕንጻውን በይፋ መርቀዋል።
ጉባኤ ቤቱ ከዚህ በፊት ባልተሟላና በአስቸጋሪ ሁኔታ በአጼ ቴዎድሮስ ባድማ ይካኼድ የነበረ ሲሆን አዲሱ ሕንጻ ግን ማደሪያ ክፍሎችን ጨምሮ መማሪያ አዳራሽ፣ ደረጃውን የጠበቀ ዲጂታል ላይብሪ ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ማማከሪያ ክፍል፣ መመገቢያና ሌሎች ክፍሎችን በማሟላት ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርጓል።
መምህረ መምህራን በጽሐ ዓለሙ ሕንጻው ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ርብርብ ያደረጉ ኦርቶዶክሳውያንን አመስግነው ” እውነተኛ የተግባር ሥራ ያየንበት ቢሆንም ሥራችንን ግን ገና አልጨረስንም” ሲሉ ተናግረዋል።
በደቀ መዛሙርቱ እና በጉባኤ ቤቱ ሕንጻ ምርቃት መርሐ ግብር ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የአካባቢው ምእመናንና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ተከናውኗል።
