የማቴዎስ ወንጌል

የካቲት 2 ቀን 2007 ዓ.ም.

ምዕራፍ ዐሥራ አራት

በዚህ ምዕራፍ፡-
1. ስለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አሟሟት
2. ጌታችን አምስት ሺሕ ሰዎችን ስለመመገቡ
3. ጌታችን በባሕር ላይ ስለመራመዱ እንመለከታለን

1.የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አሟሟት
እሥራኤል በአራት ክፍል ተከፍላ በምትዳደርበት ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆኖ እስከ 39 ዓ.ም. በገሊላ የገዛው ሄሮድስ አንቲጳስ ይባል ነበር፡፡ ይህ ሰው የወንድሙን የሄሮድስ ፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ፣ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ሳይፈራና ሳያፍር ገሰጸው፡፡ ዘሌ.18፡16 በዚህም ምክንያት ዮሐንስን አሲዞ አሳሰረው፡፡ እንዳይገድለው ግን ሕዝቡን ፈራ፡፡

ሄሮድስ የልደቱ በዓል ባከበረበት ቀን የሄሮድያዳ ልጅ በዘፈኗ አስደሰተችው፡፡ ከደስታውም የተነሣ የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት ቃል ገባላት፡፡ እርስዋም በእናትዋ ተመክራ የመጥምቁን ዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት አድርገህ ስጠኝ አለችው፡፡ ለጊዜው በያዝንም ነገር ግን ስለ መሐላው አንድም በዙሪያው የተሰበሰቡ ሰዎች “ቃሉ ግልብጥብጥ ነው፤” ይሉኛል ብሎ ፈርቶ የጠየቀችውን ፈጸመላት፡፡ በወጭት መሆኑም ለጊዜው እስራኤል ደም ስለማጸየፉ ሲሆን፤ ለፍጻሜው ግን የከበረች የቅዱስ ዮሐንስ ራስ በዚህች በርኲሰት እጅ እንዳይያዝ እግዚአብሔር በጥበብ ያደረገው ነው፡፡

ሄሮድስን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጠባዩ ቀበሮ ብሎታል፡፡ ሉቃ.23፡6-12 ቀበሮ የተንኮለኛና የደካማ ሰው ምሳሌ ነው፡፡ መኃ.2፡15፣ ነህ.4፡3፡፡ ጲላጦስ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዞ በላከበት ጊዜም በንቀት ዘብቶበታል፡፡ ሉቃ.23፡6-12፡፡

2.አምስት ሺህ ሰዎችን እንደ መገበ
ጌታችን የቅዱስ ዮሐንስን ሞት ሰምቶ ወደ በረሃ ፈቀቅ አለ፡፡ ሕዝቡም ሰምቶ ተከተለው፡፡ በመሸም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሕዝቡን እንዲያሰናብት ጠየቁት፡፡ ይህም ለዚያ ሁሉ ሕዝብ የሚሆን ምግብ ስለሌለ የሚበሉትን እንዲገዙ ነበር፡፡ እርሱ ግን ለጊዜው የተገኘውን አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ ባርኮ ሁሉንም እስኪጠግቡ ድረስ መገባቸው፡፡ ተርፎም አሥራ ሁለት መሶብ ተነሣ፡፡ የተመገቡትም ሕዝብ ሴቶችና ሕፃናት ሳይቆጠሩ አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ፡፡ ሴቶቹ ያልተቆጠሩበት ምክንያት በአደባባይ ሲበሉ በሃፍረት ዳር ዳር ስለሚሉ ነው፤ ሕፃናት ደግሞ ከሚበሉት የሚፈረፍሩት ስለሚበዛ ነው፡፡

ጌታችን ያን ሁሉ ሕዝብ በመንደር አጠገብ መመገብ ሲችል ርቆ ወደ ምድረ በዳ የወጣበት ምክንያት ነበረው፡፡ ይህም፡-

 

1ኛ “ጥንት አባቶቻችሁን ከመንደር አውጥቼ /ከግብፅ አውጥቼ/ አርባ ዘመን ሙሉ መና የመገብኋቸው እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በሥልጣኔ፣ በተአምራቴ መገብኋችሁ፡፡” ሲላቸው ነው፡፡

 

2ኛ. ተአምራቱን ከመንደር አጠገብ አድርጐት ቢሆን ኖሮ “ፈጣን ፈጣን ደቀመዛሙርቱን በጐን ወደ መንደር እየላከ ያስመጣው ነው፤” ብለው በተጠራጠሩ ነበር፡፡ ስለሆነም ለጥርጥር ምክንያት እንዳይኖራቸው አድርጎ ተአምራቱን ገልጦላቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በበረሃ ያውም በምሽት ሕዝቡን በውኃ አጠገብ በሣር ላይ አስቀምጧቸው መመገቡ “በፍጻሜው ዘመን በምቹ ሥፍራ በመንግሥተ ሰማያት መንፈሳዊ ምግብ እመግባችኋለሁ፡፡ በውኃ /በጥምቀት/ በሚገኝ ክብርም አከብራችኋለሁ፡፡” ሲላቸው ነው፡፡

 

በዚህ ታሪክ ውስጥ አምስቱ እንጀራ የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ እነኚህም፡- 

1ኛ. ምሥጢረ ሥላሴ
2ኛ. ምሥጢረ ሥጋዌ
3ኛ. ምሥጢረ ጥምቀት
4ኛ. ምሥጢረ ቁርባን
5ኛ. ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡

ሁለቱ ዓሣ ደግሞ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔር ማለት እግዚአብሔር አምላክን በፍጹም ነፍስና በፍጹም ሐሳብ መውደድ ነው፡፡ ፍቅረ ቢጽ ደግሞ ባልንጀራን እንደራስ አድርጐ መውደድ ነው ዘዳ.6፡5፣ ማቴ.22፡37 በተጨማሪም እንጀራውና ዓሣው የሥጋውና የደሙ ምሳሌ ነው፡፡

3.በባሕር ላይ እንደተራመደ
ጌታችን በተአምራት ሕዝቡን መግቦ ካሰናበተ በኋላ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፡፡ እንዲህም ማድረጉ “ተአምራት ተደረገልን ብላችሁ ጸሎታችሁን አትተዉ” ለማለት ለአብነት ነው፡፡ ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ዘባነ ባሕርን /የባሕርን ጀርባ/ እየተረገጠ በማዕበል ስትጨነቅ ወደ ነበረችው ወደ ደቀመዛሙርቱ ታንኳ መጣ፡፡ ደቀመዛሙርቱ ግን ምትሃት መስሏቸው ፈርተው ጮኹ ወዲያውም “አይዟችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ፤” አላቸው፡፡

 

ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ከሆንክስ እዘዘኝና ወደ አንተ ልምጣ፤” አለው፡፡ ጌታም “ባሕሩን እየተረገጥክ ና” ብሎ አዘዘው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስ ግን መጓዝ ከጀመረ በኋላ ነፋሱን አይቶ ፈራ፡፡ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ “ጌታ ሆይ አድነኝ” ብሎ ጮኸ፤ ጌታም እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ ለምን ተጠራጠርህ” አለው፡፡ “ከርሱ ጋር ሳለሁ ጥፋት አያገኘኝም ፣ አትልም ነበር” ሲለው ነው፡፡ በመርከብ ያሉትም “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤” ብለው ሰገዱለት፤ ተሻግሮም በጌንሴሬጥ ብዙ ሕሙማንን ፈወሰ፡፡ ሕሙማኑም የተፈወሱት የልብሱን ጫፍ በእምነት በመዳሰሳቸው ነበር፡፡

በዚህ ታሪክ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል መባሉ እሥራኤላውያንን ሰዓተ ሌሊቱን በአራት ክፍል ስለሚከፍሉት ነው፡፡ ይህም፡-
1ኛ. ከምሽቱ እስከ ሦስት ሰዓት
2ኛ ከሦስት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት
3ኛ. ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት
4ኛ. ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ንጋት ነው፡፡ /በዚህ ክፍል ሌሉቱ እያለፈ ነው፣ እየነጋ ነው ይባላል፡፡/ ይህ ሰዓት ማዕበል ፈጽሞ የማይነሣበት ሰዓት ነው፡፡ ነገር ግን ተአምራቱን ለመግለጽ የፈለገ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ሰዓቱ ማዕበል እንዲነሣ አድርጓል፡፡ እንዲህ ባይሆን ኖሮ “ድሮም ማዕበል ይነሣል፣ ደግሞም ጸጥ ይላል፤ ምን አዲስ ነገር አለ” ባሉ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአራተኛው ሰዓተ ሌሊት ወደ ባሕር መምጣቱ በአራተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ዓለም የመምጣቱ ምሳሌ ነው፡፡

በአራት የተከፈሉት ዘመናትም፡-
1ኛ. ዘመነ አበው
2ኛ. ዘመነ መሣፍንት
3ኛ. ዘመነ ነገሥት
4ኛ. ዘመነ ካህናት ናቸው፡፡

የነፋሱ ኃይልም የጽኑ መከራ ምሳሌ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ባሕር የዓለም ምሳሌ ስትሆን ታንኳይቱ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የሚነሣባትን የመከራ ማዕበል ፀጥ የሚያደርግላት አምላክ አላት፡፡ ለዚህም ሳይታክቱ “እግዚኦ፣ እግዚኦ፣ እግዚኦ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 5ኛ ዓመት ቁጥር 3 ታኅሣሥ 1990 ዓ.ም.