ዘመነ ክረምት
እንኳን አደረሳችሁ!!!
ክፍል አንድ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡
በቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት፣ በመጽሐፈ ግጻዌ እንደ ተገለጸው እነዚህም፡- ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡
ከላይ ላሉት አራቱ ወቅቶች አራት መጋብያነ ከዋክብት አሏቸው። እነሱም ፦
፩) ምልክኤል___መጋቢት 26- ሰኔ 25
፪) ሕልመልሜሌክ___ሰኔ 26-መስከረም 25
፫) ብርክኤል____መስከረም 26-ታኅሣሥ 25
፬) ናርኤል__ታኅሣሥ 26-መጋቢት 25
ከአራቱ ወቅቶች መካከል ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡
የዘመነ ክረምት ቀናት ብዛት 90 ነው። የጳጉሜን ዕለታት እያንዳንዳቸው አራቱ ዘመናት ሲካፈልዋቸው አንድ አንድ ይደርሳቸዋል አንዲት ብቻ ትቀራለች። እሷም ዕለተ ምርያ ትባላለች። 90×4 =360 ጳጉሜን 5 ሲደመር 365 ይሆናል ማለት ነው።
ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ድጓዉን ሲደርስም በአራት ዓበይት ክፍሎች ነው የከፈለው። እነሱም፦
፩.ዮሐንስ ፫.ጾመ ድጓ
፪.አስተምህሮ ፬.ፋሲካ ናቸው።
በአራት የተከፈሉበት ምክንያትም ምሳሌ ስላለው ነው።
፩.ዘመነ አበው——–ከአዳም እስከ ሙሴ
፪.ዘመነ መሳፍንት —ከሙሴ እስከ ሳሙኤል
፫.ዘመነ ነገሥት ——-ከዳዊት እስከ ዘሩባቤል
፬.ዘመነ ካህናት ——–ከዘሩባቤል እስከ ክርስቶስ ያለዉን ያስታውሳል።
ክረምቱ የሚጀምረው ሰኔ ፳፮ ቀን ነው።
መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስረዱን ክረምት” የሚለው ቃል ’”ከርመ ”፣ ከረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ወርኀ ዝናም፣ ወርኀ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ… የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፤ እንደዚሁም ዕፅዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡
ዘመነ ክረምት በሰባት ንዑሳን ክፍሎች ይመደባል፤ የክፍፍሉ መሠረት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲሆን፣ ክፍሎቹም የሚከተሉት ናቸው።
፩ኛ ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ያለው ጊዜ በአተ ክረምት ወይም ዘርዕ፣ ደመና፤
፪ኛ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ያለው ጊዜ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል፤
፫ኛ ከነሐሴ ፲ – ፳፯ ቀን ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ፤
፬ኛ ከነሐሴ ፳፰ እስከ ጳጉሜን ፭ (፮) ቀን ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባህ፣ ብርሃን፣ መዓልት፤
፭ኛ ከመስከረም ፩ – ፯ ቀን ዮሐንስ፤
፮ኛ ከመስከረም ፰ – ፲፬ ቀን ፍሬ፤
፯ኛ ከመስከረም ፲፭ – ፳፭ ቀን ፀአተ ክረምት (የክረምት መውጫ) ወይም ዘመነ መስቀል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለስም አጠራሩ ምስጋና ይሁንና “ሽሽታችሁ (ስደታችሁ) በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” ብሎናልና (ማቴ. 24:20) :: በዘመነ ክረምት ቅጠል እንጂ ፍሬ የለበትምና ፍሬ ምግባር ሳናፈራ ሞት እንዳይመጣ፣አንድም ክረምት የዝናብና የጭቃ ጊዜ በመሆኑ እንኩዋንስ ለስደት ለኑሮም አይመችምና ። ሊቃውንትም በክረምት እንዲህ ብለን እንድንጸልይ ይነግሩናል።
“በዝንቱ ክረምት በመዋዕሊነ:
እንበለ ፍሬ እንዘ በቆጽል ኀሎነ:
ናስተበቁዐከ እግዚኦ ኢይኩን ጉያነ::”
(ክረምት በተባለ በእኛ እድሜ:
ፍሬ ሳናፈራ በቅጠል /ያለ መልካም ሥራ/ ሳለን:
አቤቱ ጌታ ሆይ ስደትን አታምጣብን)
“አርኬ”
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም “ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነድያን፣ ይጸግቡ ርሁባን፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናም በዘነመ ጊዜ ችግረኞች ይደሰታሉ፤ ረሀብተኞችም ይጠግባሉ፡፡” በማለት በድጓው የዘመረው ይገኝበታል፡፡
ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፡፡ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እምሕያው”፡፡ ሰማዮችን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃልና፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም” መዝ ፻፵፯፥፰ በማለት የዘመረው ይሰበካል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናም የምትጠጣ መሬት ለሚያርሷትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከት ታገኛለች፤ እሾህንና ኩርንችትን ግን ብታወጣ የተጣለች ናት፡፡ ለመረገምም ትቀርባለች፤ መጨረሻዋም መቃጠል ነው፡፡” በማለት ያስተማረው ትምህርት ይነበባል፡፡(ዕብ.፮፥፯-፰)
በዘመነ ክረምት ውኃ ይሰለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህ ዘመን ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው።
ዘመነ ክረምት፡- የዝናም፣ የዘርና የአረም ወቅት በመሆኑ ምድር በጠል ዝናም ትረካለች፡፡ ዕፅዋት አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ በሥነ ጽጌያት የምታሸበርቅበት፣ ወቅት ነው፡፡በመሆኑም በሀገራችን ብዙው የግብርና ሥራ የሚካሄደው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
ወርኃ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፤ ገበሬ በወርሃ ክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሳል፡፡ ክርስቲያንም በዚህ ምድር ላይ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ይታገሳል፤ ክርስቲያንም በዚህ ምድር የሚደርስበትን መከራ ሁሉ በጸጋ የሚቀበለው በዚያኛው ዓለም ስለሚያገኘው ተድላና ደስታ ነው፡፡
ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “እለ ይዘርዑ በአንብዕ ወበሐሤት የአርሩ፡፡ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ፡፡ ወጾሩ ዘርዖሙ፡፡ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ፡፡ በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ፡፡” በማለት የመንፈሳዊ ጉዞ ምሥጠርን ከግብርና ሙያ አንጻር አመልክቶአል፡፡(መዝ.፻፳፭፥፮)
እግዚአብሔር ክረምትን ሲያመጣና ዝናምን ሲያዘንም ብዙ ነገሮችን ልናስተውል ይገባናል፡፡ ፈጣሪያችን ፈጣሬ ዓለማት ብቻ ሳይሆን መጋቤ ዓለማት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ መግቦቱም ከፍጥረቱ እንዳልተለየ ይህ አማናዊ መግቦቱም ፍጥረቱን እንደሚያስተምር እንረዳለን፡፡
“በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፤ ብርድና ሙቀት፤ በጋና ክረምት፤ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም፡፡”(ዘፍ.8፥22) በማለት አምላካችን እግዚአብሔር ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በጋና ክረምቱ፤ ብርድና ሙቀቱ፤ ቀንና ሌሊቱ በተወሰነላቸው ጊዜ እየተፈራረቁ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ አድርጓቸዋል።
ይቀጥላል……
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
