“ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” (ሥርዓተ ቅዳሴ)

መምህር ሃይማኖት አስከብር

ጥር ፬፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ምሥራቅ የቃሉ ፍቺ “የፀሐይ መውጫ” ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፮፻፹) በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ዲያቆኑ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” በማለት በዜማ ለምእመናኑ ያውጃል፤ በእርግጥ በቅዳሴ ጊዜ በመካከል የሚያነቃቁና የአለንበትን ቦታ እንድናስተውል የሚያደርጉ ሌሎች ዐዋጆች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል “እለ ትነብሩ ተንሥኡ፤ የተቀመጣችሁ ተነሡ” የሚለው ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ከታመመ ከአረጋዊ በቀር ማን ማንም አይቀመጥም፡፡ ሰው እያስቀደሰ እየጸለየ ልቡናው ሌላ ቦታ ይሆንበታል፤ ይባዝናል፤ ያለበትን ትቶ በሌላ ዓለም ይባዝናል፡፡ አንዳንዴ ጸሎት እየጸለይን ሐሳባችን ሊበታተን ይችላል፡፡ ከየት ጀምረን የት እንዳቆምንም ይጠፋብናል፤ መጀመራችን እንጂ እንዴት እንደጨረስነውም ሳናውቀው ጨርሰን እናገኘዋለን፤ ዲያቆኑ በቅዳሴ ጊዜ “የተቀመጣችሁ ተነሡ” ማለቱ “የቆማችሁ በማን ፊት እንደሆነ አስታውሉ” ሲል ነው፡፡

እንዲሁም “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” ሲባል ምን ማለት ነው? ዲያቆኑስ ምን እንድናደርግ ነው ያዘዘን? የሚለውን በመቀጠል እናያልን።

፩. ምሥራቅ የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ “ተመልከቱም” ማለቱ “እመቤታችንን አስቡ” እያለን ነው፤ ድንግል ማርያምን ስናስብ ክርስቶስን እናስባልን፤ አማናዊት ምሥራቅ ናትና፡፡ ለዚህም ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በስብሐተ እንዚረው ሲያመሰግናት እንዲህ ይላታል፤ “ኦ ጽባህ እንተ አልብኪ ጽልመት፤ ጨለማ የሌለብሽ ጨለማን የምታስወግጅ ጎሐጽባህ፤ የንጋት ወጋገን፡፡”

በተለይ በዚህ ወቅት የእመቤታችን ምሥራቅንት የምናስብበት ነው፤ ሌሊቱ አልፎ ጨለማው ሲወገድ ፀሐይ ስትወጣ ብርሃኗን ስትለቅ ዓይናችን ከፀሐይ ብርሃኗ በስተጀርባ ያለውን የምሥራቅ ሰሌዳ ይመለከታል፡፡ በምሥራቅ በኩል የወጣው ፀሐይ ጨለማን አሰወግዶ ለሰው ልጅ ብርሃንን አጎናጽፎ ደስታን ያድላል፡፡ ይህች ምሥራቅ የፀሐይ መገኛ አማናዊት ምሥራቅ ፀሐየ ጽድቅነ ክርስቶስን አስገኘች፡፡ ከእርሷ በተገኘው ጨለማው እንደሚወገድ ከእመቤታችን የተገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በሰው ልጅ ሠልጥኖ የነበረውን የሞት ኃጢአት ጨለማ አስወግዶታል፡፡ ከምሥራቋ ድንግል ማርያም የተገኘ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን ከአማናዊት ምሥራቅ እመቤታችን ተወለደለን። የዚህን ዓለም ብርሃን ጠፈር ደፈር ይከለክለዋል፤ ጨለማ ይጋርደዋል፤ እውነተኛ ብርሃን ክርስቶስ ነው፤ ጠፈር ደፈር ሳይከለክለው ጨለማን አሰወግደ ከአማናዊት ምሥራቅ እመቤታችን ተገኘ፤ ስለዚህም የእመቤታችንን ምልጃና ተራዳኢነት በማሰብ ዲያቆኑ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” የሚለው እመቤታችን በቅዳሴያችን እንድናስብና እንዳንዘነጋ ለማሳሰብ ነው፤ በእርሷ ጨለማ ተወግዷልና፡፡

የኃጢአት ጨለማ የተወገደባት ድንግል ማርያም አማናዊት ምሥራቅ ናት፡፡ ነቢያት አስቀድመው ወደ ምሥራቅ ሲመለከቱ በምሳሌ እመቤታችንንና ክርስቶስን ያዩ ነበር፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ዘወር ሲል የተመለከተው ድንግል ማርያምን እና ክርስቶስ ነበር፡፡ (ሕዝ.፵፬፥፩‐፬) ሊቁም “አንቲ ውእቱ ምሥራቅ ዘወፅአ እምኔኪ ፀሐየ ጽድቅ፤ እውነተኛው የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ የተገኘብሽ ምሥራቅ አንች ነሽ” ብሎ አመስግኗታል፡፡ (መጽሐፈ ሰዓታት መልክዐ ውዳሴ፤ ዘዐርብ) ስለዚህ በቅዳሴያችን ወደ ምሥራቅ እንድመለከት የምንታዘዘው እመቤታችንን እንድናስብ ነው፤ እመቤታችንን ስናስብ ደግሞ ክርስቶስን እናስባለን፤ ለያይቶ ማየት አይቻልምና፤ በዚህም አማናዊት ምሥራቅ እመቤታችን እንደሆነች እንረዳለን።

፪. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በምሥራቅ ነው። ወደ ምሥራቅ መመልከት ጌታችን የተወለደበትን ቤተልሔምን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ከእየሩሳሌም በስተምሥራቅ የምትገኘው ቤተልሔም ነች፤ ቤተልሔም ክርስቶስ የተወለደባት ስፍራ ናት፤ ሰብአ ሰገል የክርስቶስን መወለድ በሰሙ ጊዜ ወደ ቤተልሔም በኮከብ እየተመሩ ወደ ምሥራቅ ተጉዞው ጌታችን ወደ ተወለደበት ስፍራ ደርሰዋል፡፡ (ማቴ.፪፥፪) ሰብአ ሰገል ኮከቡን ያዩት በምሥራቅ ሲሆን ኮከቡም ምሳሌነቱ የእግዚአብሔር ምሕረት ነው፡፡ እነርሱን ወደ እግዚአብሔር እንዳደረሳቸው ሁሉ እኛንም ወደ ለመለመው መስክ ይመራናል፡፡ (ማቴ.፪፥፪፣መዝ.፳፪፥፲፬) ጌታችን ከሰማይ ወደ ምድር ወርዶ ሰው የሆነበት ምክንያት ለእኛ ድኅነት በመሆኑ ወደ ምሥራቅ በምንዞር ጊዜ የጌታችንን መወለድ እና ያደረገልን ውለታ ይታወሰናል፡፡ በመሆኑም በልቦናችን ቤተልሔምን እንድናስብ በዐዋጅ ይናገራል። (ወንጌል ትርጋሜ ምዕራፍ ፪)

፫. በዕለተ ዓርብ ለዓለም ድኅነት ሲል በቀራንዮ ዐደባባይ ጌታችን የተሰቀለው በምሥራቅ ነው፡፡ ወደ ምሥራቅ ስንመለከትም ወደ ቀራንዮ እንመልከታለን፡፡ ቀራንዮንን ስናስብ ክርስቶስን እናስባለን፡፡ ቀራንዮን ስናስብ የክርስቶስ ሕማሙ መከረውን እናስባለን፤ በምሥራቅ ድኅነታችንን አገኘን፡፡ ወደ ምሥራቅ ቀና እንል ዘንድ እርሱ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ዞሮ ተሰቀለልን፤ መከራ መስቀሉን በመሸከም ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያገኙ ጻድቃን የሚገቡባት እየሩሳሌም ሰማያዊት ምሥራቃዊት ከተማ ናት፡፡ ስለዚህም ወደ ምሥራቅ በዞርን ቁጥር የተሰቀለውን ክርስቶስንና ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እናስባለን።

፬. የመጅመሪያው ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተው በምሥራቃዊ እየሩሳሌም ነው፤ ይህም ለወንጌል መሰበክ መነሻ ነው። ሕገ ወንጌል በምሥራቅ ተጀምራ ለሰው ልጅ ብርሃን ሆናለች፤ ሕገ ወንጌል ብርሃን ናት፤ “በጨለማ ኃጢአት ለነበረ ሕዝብ ብርሃን የሆነችውን ወንጌልን ተመልከቱ፤ አስቡ፤ ተማሩ” ሲል ዲያቆኑ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” ይላል፡፡ ምሥራቅ የብርሃን መገኛ ናት፤ ብርሃን ደግሞ ሁሉንም ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፤ ወንጌልም ጽድቅን ከኃጢአት ኃጢአትን ከጽድቅ ለይታ የምታሳይ ብርሃናዊት ሕግ ናት። (ሥርዓተ ቅዳሴ ትርጓሜ)

ወንጌል የሕይወት ብርሃን ናት፤ የፀሐይ ብርሃን ከዓይናችን ሲዋሐድ ሲሆን ማየት እንጀምራለን፡፡ የወንጌል ሕግ ደግሞ በልቦናችን ሲዋሐድ ኃጢአትን ከጽድቅ ክፉውን ከመልካሙ ነገር ለይተን ማየት እንጀምራለን። መጸሐፍም “ሕግህ ለእግሬ መብራት ነው” እንዳለው የወንጌል ሕግ ለሕይወታችን መብራት ናት፤ (መዝ.፻፲፱፥፻፭) ወደ እርሷ መመልከት ብርሃንነረ ማየት ነው።

፭. የመጀመሪያው ሰው አዳም ይኖርባት የነበረችው ገነት የምትገኘው በምሥራቅ ነው፡፡ (ዘፍ.፪፥፰) በዚያም ሲኖር ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ የሞትን ፍሬ እንዲበላ እና ሕገ እግዚአብሔርን እንዲተላለፍ ሲያደረገው ከገነት ተባረረ፡፡ ከአምስት ሽህ አምስት መቶ ዓመት ፍዳ በኋላም አምላካችን እግዚአብሔር ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል በገባለት መሠረት ጌታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶና መከራ ተቀብሎ ሲያድነው ገነትም ዳግም ተከፍታለች፡፡ (ሉቃ.፳፫፥፵፫) በዚህም መሠረት ወደ ምሥራቅ በዘወትር የጸሎትም ሆነ በቅዳሴ ሰዓት ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ እየተመለከትን የአምላካችን የተስፋ ቃልና ምሥጢረ ድኅነትን እናስባለን፡፡

፮. በምጽአት ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ የሚመጣው ከምሥራቅ ነው። በመጽሐፍም “በዚያን ቀን እግሮቹ በእየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ይቆማሉ” (ዘካ.፬፥፲፬) “ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል” ተብሎ ተጽፏል፡፡ (ሐዋ.፩፦፲፩) ስለዚህም ወደ ምሥራቅ በተመለትን ቁጥር ትንሣኤ ሙታንን በመሳብ እና ዘወትር ለቅጣት ከሚዳረግን ኃጢአት በመራቅ እንድንኖር ይረዳናል፡፡

፯. ምሥራቅ የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ነው። (ኢሳ.፳፰፥፲፫) “እግዚአብሔርን በምሥራቅ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ፡፡” “የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ” እንዲል። (ሕዝ.፵፫፥፪) በመሆኑም ወደ ምሥራቅ ስንመለከት የፈጣሪያችን ክብር በማስብ እናመሰግነዋለን፤ እናወድሰዋለን፡፡

፰. በቀደሙት ዘመናት ቅዱሳን አበው ወደ እየሩሳሌም ያለውን መስኮት ከፍተው ጸሎት ያደርሱ የነበረው ወደ ምድራቅ ዞረው ነበር፡፡ (ዳን.፮፥፱) አምላካችን እግዚአብሔር ምሉዕ በኩልሄ (የሌለበት ቦታ የሌለ) መሆኑን ቢታወቅም ነገረ ድኅነቱን በማሰብ ጸሎት የምናደርሰው ወደ ምሥራቅ ዞረን ነው፡፡

፱. በቤተ መቅደስ ታቦተ ሕጉ በምሥራቅ በኩል የሚቀመጠውና በዚያም ሥጋወ ደሙ የሚፈተትበት ምሳሌ አለ፡፡ ይህም ጌታ በምሥራቅ ሀገር ጎለጎታ ለእኛ ሥጋውን መቁረሱ ደሙን ማፍሰሱን መታሰቢያ በማድረግ ነው። እናም በንስሓ ሆነን ለሥጋ ወደሙ መብቃትን ለማሰብ ወደ ምሥራቅ እንድንመለከት እንታዘዛለን፡፡

፲. ሰዎች ስንሞትና ስንቀበረ ራሳችን ወደ ምዕራብ እግራችን ወደ ምሥራቅ ሆኖ ነው፡፡ በሥርዓት ቀብሩ የአስከሬናችን ፊት ወደ ምሥራቅ የሚዞርበት ምክንያትም በዳግም ምጽአት ጌታችን ጻድቃንን በቀኙ ኃጥአንን በግራው በሚለይበት ጊዜ በትንሣኤ ሙታን ስንነሣ ፊታችን ወደ ጌታችን እንዲዞር እና እንድንመለከተው የሚያሳስብ ነው። ይህም ከዘለዓለማዊ ሞት ጌታችን እንድታድገንና መንግሥተ ሰማያትን እንዲያወርሰን ከኃጢአት በመንጻትና በቅድስና ሕይወት እስከ ዕለተ ሞታችን መኖር እንዳለብን ለማሳሰብ ወደ ምሥራቅ እንድንመለከት ዲያቆኑ ያሳስበናል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ፶፰፥፭)

ብርሃነ ሕይወት ክርስቶስን የምናይበት ልቡና ያድለን፤ አሜን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲተ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!