እንኳን ለእናታችን ለእመቤታችን ለቅድስተ ቅዱሳን ለድንግል ማርያም ሰኔ ጐልጐታና ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን (ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ ለታነጸበት) ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።
“ለዛቲ ቤት ሣረራ አብ ቀዲሙ ለዛቲ ቤት ሐነጻ ወልድ ወፈጸማ መንፈስ ቅዱስ”
(ይችን ቤት አብ ሠራት ወልድ አነጻት መንፈስ ቅዱስ ፈጸማት አከናወናት )
“ቅዱስ ያሬድ “
ክፍል አንድ
ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን
በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ቂሣርያ፣ ኬልቄዶንያ አውራጃ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ሰኔ ፳ ‹‹ሕንጸታ ቤታ›› ፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውኀ በሦስት ድንጋዮች ቤተ ክርስቲያኗን ያነጸበት ዕለት ነው።
አናጺውም ደግሞ ራሱ ባለቤቱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ቦታው በፊልጵስዩስ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኗ የተሰየመችው ደግሞ በእመቤታችን ስም ነው።
ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል አብራርቶታል –ተቀደሲ ወንሥኢ ኃይለ ኦ ቤተ እግዚአብሔር ፣ እስመ ናሁ ንጉሥኪ፣በጽሐ ዘያበርህ ለኪ በኃይሉ፣
ለዛቲ ቤት ሣረራ አብ ቀዲሙ፣
ለዛቲ ቤት ሐነጻ ወልድ፣
ለዛቲ ቤት ወፈጸማ መንፈስ ቅዱስ፣
የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆንሽ ቤተ ክርስቲያን ሆይ በኃይሉ የሚያበራልሽ ንጉሥሽ እነሆ ደርሷልና ክብርሽ ከፍ ከፍ ይበል ኃይልንም ያዥ ይልና
ይችን ቤት አስቀድሞ አብ ሠራት ወልድ አነጻት መንፈስ ቅዱስ ፈጸማት በማለት ይጨርሳል::
ጥንተ ነገሩስ (ታሪኩ) እንደምን ነው ቢሉ፤
ስም አጠራሩ የተመሰገነ ይሁንና አምላካችን መደኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ሑሩ ወመሐሩ ኵሎ አሕዛበ፤ አሕዛብን ሁሉ ሒዱና አስተምሩ፡፡›› /ማቴ. ፳፰፥፲፱/ ባላቸው ቃል መሠረት ሐዋርያት በወንጌል ያርሷት ዘንድ ይህችን ዓለም በዕጣ ተካፍለዋታል::
የሰው ልጅ ድኅነቱ የሚፈጸመው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበል ነውና (ዮሐ. ፮፥፶፮) አበው ሐዋርያት ቊርባንን በተመረጡ ሰዎች ቤት እያዘጋጁ ቀድሰው ያቆርቡ ነበር::
በመጀመሪያ በጽርሐ ጽዮን፣ቀጥሎም በተለያዩ ሰዎች ቤት እንዲህ ይከናወን ነበር፡፡ ለጸሎት ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ምኵራበ አይሁድን ይጠቀሙ ነበር:: እየቆየ ሲሔድ ግን ከአሕዛብ ያመኑ ሰዎች ቊጥር እጅጉን በመብዛቱ ጌታችን በዐረገ በስምንተኛው ዓመት ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ በርናባስ ወደ ፊልጵስዩስ ገብተው በክርስቶስ ስም አሳምነው ብዙ አሕዛብን ካጠመቁ በኋላ/በተለይ ቅዱስ ዻውሎስ ያሳመናቸው ለጸሎት እያሉ ወደ ጣዖት ቤት መግባት አመጡ::/ በዚህ ምክንያት መምህራን ሕዝቡን ‹‹ካመናችሁ በኋላ እንዴት ወደ ጣዖት ቤት ትገባላችሁ?›› ቢሏቸው ‹‹እኛ ምን እናድርግ! የምንጸልይበት ቤት የለን››ሲሉ መለሱላቸው:: ነገሩ ሲያያዝ ከደጋጉ ሐዋርያት ዻውሎስና በርናባስ ደረሰ::
ወዲያውኑ አንዳንድ ወንድሞች የጸሎት ቤት ‹‹ለምን አናንጽም?›› ብለው ነበር:: ቅዱስ ዻውሎስ ግን ‹‹ሊቀ ሐዋርያቱ ሳይፈቅድ አይሆንም›› አለ:: (ለዚህ ነው ዛሬም ሊቀ ዻዻስ ካልፈቀደ ቤተክርስቲያን የማይታነጸው፡፡) ከዚያ ቅዱሳን ዻውሎስና በርናባስ ሐዋርያቱ ወዳሉበት ሔደው ነገሩን ለቅዱስ ዼጥሮስ አስረዱ:: ሊቀ ሐዋርያቱ ቅዱስ ዼጥሮስም ‹‹የጌታችን ፈቃዱ መሆኑን እናውቅ ዘንድ ተያይዘን ሱባኤ እንግባ›› አለ::
በዚህ ጊዜ ሐዋርያት በያሉበት በአንድ ልብ ሱባኤ ገቡ:: በሱባኤያቸው መጨረሻም ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ላይ ሆኖ እልፍ አእላፍ መላአክትን አስከትሎ በግርማ ወደ እነርሱ ወረደ፤እመቤታችንም በቀኙ ነበረች የሞቱትን አስነሥቶ፣ ያሉትንም ጠርቶ ቅዱሳን ሐዋርያትን በፊልጵስዩስ አገር ሰብስቦ ‹‹በእናቴ በድንግል ማርያም ስም ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚሠራውን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ ላሳያችሁ፤ ሥርዓቱንም ላስተምራችሁ ሰብስቤአችኋለሁ›› ብሎ ወደ ምሥራቅ ይዟቸው ወጣ፡፡ በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮችንም የተራራቁትን አቀራርቦ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ፳፬፤ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት ሰም እሳት ሲያገኘው እንዲለመልም፣ ድንጋዩ በእጃቸው ላይ እየተሳበላቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሠርተው ፈጽመውታል፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራውም ጌታችን በዐረገ በ፲ኛው፤ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ሲኾን፣ በ፳፩ኛው ቀን (በማግሥቱ) ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችን ጋር ከሰማየ ሰማያት መጥቶ እመቤታችንን ታቦት፤ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ሆኖ ቀድሶ ካቈረባቸው በኋላ ‹‹እምይእዜሰ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ፤ ከዛሬ ጀምሮ እናንተም እንደዚህ አድርጉ›› ብሎ አዝዟቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡
ይህ ታሪክ ብዙ ምሳሌዎች አሉት፡፡ ይኸውም፡- የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመት በነገሥታት ዘመን የነበሩ ነቢያት፤ አንድም የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ሲሆን፣ ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ሲሆኑ፣ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፤ ከላይ ሕንጻቸው አንድ መሆኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያመለክታል።
ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በድጓው ላይ ስለ ክብረ ቤተ ክርስቲያን፦
“እንተ ተሐንጸት በስሙ፤ ወተቀደሰት በደሙ ወተዐትበት በዕፀ መስቀሉ ጊሡ ኀቤሃ እስመ ኀይለ እግዚአብሔር ላዕሌሃ” (በስሙ ታነጸች፤ በደሙም ከበረች፤ በዕፀ መስቀሉም ተባረከች፤ ወደ ርሷ (ቤተ ክርስቲያን) ሒዱ የእግዚአብሔር ኀይል በእርሷ ላይ ነውና) ይላል፡፡
አባ ጽጌ ድንግል በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ፡-
“በሠላስ አእባን ገጸ ሥላሴሁ ለአምሮ
ሐኒጸ ቤትኪ ድንግል ድኅረ ፈጸመ ሣርሮ
አመ ወረደ ለበዓል ምስሌኪ በአማኅብሮ
እንዘ ይብላ ቃለ ለዘምሮ
ልዑል ቀደሰ ማኅደሮ
ደናግል ለጽጌኪ ዘበጣ ከበሮ”
(ድንግል በአካል ሦስት መሆኑን ለመግለጽ በሦስት ድንጋዮች ቤትሽን መሥራት ከፈጸመ በኋላ፤ ከአንቺ ጋር ለበዓል በተገለጸ ጊዜ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ እያሉ ልጅሽን ለማመስገን ደናግል በከበሮ ምስጋናን አቀረቡ) በማለት ገልጿታል፡፡
……ይቀጥላል
