በገጠር አድባራትና ገዳማት ያለው የመብዐ ችግር አሳሳቢ እንደሆነ ተገለጠ፡፡

26/2004 ዓ.ም.

ተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

•    የመብዐ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እየተካሔደ ነው፡፡

በጧፍ፣ በዕጣን፣ በዘቢብና በንዋያተ ቅድሳት እጥረት ምክንያት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ያቋረጡ ገዳማትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ “የመብዐ ሳምንት” በሚል የተዘጋጀው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተጀመረ፡፡ በገጠር አድባራትና ገዳማት ያለው የመብዐ ችግር አሳሳቢ እንደሆነም ተገለጠ፡፡

ከትናንትና በስትያ የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም በተደረገው የመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ባስተላለፉት መልእክት “ከዚህ ቀደም ‘ሁለት ልብሶች ያሉት’ በሚል መርሐ ግብር በአብነት ት/ቤቶችና ገዳማት ያለውን የአልባሳት ችግር ለመቅረፍ ምእመናንና የማኅበሩ አባላት እንደተረባረቡ አስታውሰው፣ ኢትዮጵያ ዘወትር ወደ እግዚአብሔር እጆቿን የምትዘረጋባቸው የአባቶቻችን እጆች እንዳይታጠፉ አሁንም መረባረብ አለብን” ብለዋል፡፡

ሊቀ ትጉሃን አያይዘውም፣ እንደ ሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት ለወደፊቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በደንቡ አጥንቶት ቤተ ክርስቲያናችን ራሷን አደራጅታ መባዎችን ለእግዚአብሔር እንደሚገባ በጥራት አዘጋጅታ ከሌሎች ጥገኝነት የምትላቀቅበት ጊዜ እስከሚመጣ ለጊዜውም ቢሆን ያለውን ችግር መቅረፍ እንድንችል በተለይ በዚህ የፆምና የጸሎት ሠዓት ከእኛ ብዙ ይጠበቃል በማለት አሳስበዋል፡፡

በክብር እንግድነት ተገኝተው መርሐ ግብሩን በይፋ የከፈቱት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል “በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ” ሉቃ. 13፥24 በሚል ርዕስ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ከትምህርቱ ጋር አያይዘው ባስተላለፉት መልእክት “መብዐ የክርስትና መነሻ፣ የሙታን ማስቀደሻ፣ የክብረ ቅዱሳን መወደሻ ነው፡፡ ተመስጋኙ እግዚአብሔር አመስጋኙ ሰው ቢሆንም፣ እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉ ቅዳሴ የለም፤ ቅዳሴ ከሌለ ደግሞ ሠላም የለም፤ ጠለ በረከትም ይቀራል ማለት ነው፡፡ ከተወደሰ ከተቀደሰ ግን ሰዎች ይሰማሉ፣ ይማራሉ፣ ይጸልያሉ፣ ይፆማሉ፤ እግዚአብሔርም ጠለ በረከቱን ይሰጣል፡፡ በዚህ መንገድም በረከት ይገኛል፡፡ የምትሰጡትንም ለእግዚአብሔር አደራ ስጡ” ብለዋል፡፡

“ከሁሉም ከባዱ የችግሩ አካል ክርስትና ማስነሻ መብዐ አለመኖሩ ነው፡፡” ያሉት ብፁዕነታቸው “በ40 በ80 ቀን ተጠምቆ ሥጋወደሙን በምን ይቀበለው?” በማለት በሀዘን ስሜታችውን ገልጠዋል፡፡

እርሳቸው በሚያስተዳድሩት ሀገረ ስብከት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የገለጡት ብፁዕነታቸው “ከአልባሳት ችግር አንፃር የካህናት ባለቤቶች የነበሩ እናቶች ሲሞቱ ሥጋወደሙ ሲቀበሉበት የነበረውን ቀሚሳቸውን መቀደሻ ይሁንልኝ እያሉ ተናዘው ይሞታሉ፡፡ በእናቶች ቀሚስ ነው የሚቀደሰው፡፡ ለክርስትና ማንሻም አንድ ወይም ሁለት ፍሬ ዘቢብ ታሽቶ ነው የሚቀደሰው፡፡ ይኸውም ከአንዱ ወደ ሌላው አጥቢያ የውሎ መንገድ ተጉዘው የሚያስቀድሱ፣ ክርስትናም የሚያስነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡” በማለት መራራውንና አሳዛኙን እውነት አስረድተዋል፡፡

መርሐ ግብሩ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት ከየካቲት 24 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ.ም በማኅበሩ ዋና ማዕከል ጽ/ቤት ላይ ይከናወናል፡፡ ምእመናን ከእነዚህ ቀናት በኋላም በክፍሉ ጊዜአዊ እርዳታ አሰባሳቢ አማካኝነት መብዐ ማስገባት እንደሚችሉ ታውቋል፡፡