በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ …›› (ማቴ፲፣፳፰)
ከዲ/ን ተስፋዬ ቻይ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን የምሥራቹን ወንጌል ሰብከው የጨለመውን የሰው ልጅ ልቡና በወንጌል ብርሃንነት ያበሩ ዘንድ፣ ከጣዖተ አምልኮ አውጥተው የፈጠራቸውን የሚመግባቸውን እግዚአብሔር ያውቁና ያመልኩ ዘንድ፣ በጠላት ዲያቢሎስ አሳሳችነት የመረረ ሕይወታቸውን በወንጌል ጨውነት ያጣፍጡ ዘንድ ወደ ዓለም በላካቸው ጊዜ ጠላት ዲያሎስ በክፉዎች እያደረ መከራ እንደሚያመጣባቸው፣ ይህንንም እንደ እባብ ብልህ ፣እንደ ርግብ የዋህ ሆነው እንዲያልፉ ፣ሳይፈሩና ሳይሰቀቁ እንዲመሰክሩ አዘዛቸው ፤ መከራቸው ስደት ፣መጠማት፣ ግርፋትና ረኀብ ባቻ ሳይሆን ሥጋዊ ሞት( የነፍስ ከሥጋ መለየት) እንደሚገጥማቸውና ይህም አንዳች እንዳያስፈራቸው ነገራቸው፤ ምድራዊ ሩጫቸው በሰማዕትነት ቢገታም ሰማየያዊ መኖሪ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንዳለ የታመነውን ተስፋ ሰጣቸው፡፡ ቅዱሳን አበው ሐዋርያት ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በአርባኛው ቀን፣ ካረገ በአሥረኛው ቀን ባናገረው ትንቢት ፣በገባላቸው ቃል መሠረት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ላከላቸው፣በጾም በጸሎ መንፈሳዊ ተግባራቸውን ጀመሩ ፤እምነታቸው ጸንቶ፣ፍርሃት ርቆላቸው ጥቡዐን ( ደፋሮች) ሆነው የእውቀት ተከፍሎ ሳይኖርባቸው ፤ዓለምን በዕጣ ተከፋፍለው የምሥራቹን ወንጌል ማስተማር ጀመሩ፡፡
ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ከገባበት ከንቱ ሕይወት አውጥተው ወደ ሕይወት ይመሩት ጀመር፣ የእግዚአብሔርን አምላክነት፤ የድንግል ማርያምን ጸጋ በረከት፣ የቅዱሳንን ክብር እየገለጡ፣ የዲያቢሎስን ሐሰተኛነት ፣የጣዖት አምልኮን ከንቱነት እያጋለጡ፤ በወንጌል ብርሃንነት በክፋት የጨለመውን እያበሩ፣ በተስፋ መቁረጥ የመረረ ሕይወት ያጣፍጡ ጀመር፤ ሐሰተኛ የሐሰት አባት ጠላት ዲያብሎስ በአላውያን ነገሥታት እያደረ፣ ከአገር አገር ያሳድዳቸው፣መከራ ያጸናባቸው ጀመር፣ የተጠሩበትን ዓላማ ፣የሚጓዙበትን ፍኖት መዳረሻ ያውቃሉና በመከራው ፣በግርፋቱ ፣በመራብ መጠማቱ ፣በመታሠሩ ሰይሰቀቁ፣ሳይፈሩ ፤ወንጌልን አስተማሩ፡፡
የሰውን ልጅ በቅናት ከፈጣሪው አጣልቶ በኃጢአት ምርኮኝነት በባርነት ገዘቶ የነበረው ሰይጣን( ዲያሎስ) በመድሃኒት ክርስቶስ መከራ መስቀል ፣ሞትና ትነሣኤ ነጻ እንደወጡ የምሥራቹን በመስበካቸው ፤የመከራውን ዓይነት በቅዱሳን ሐዋርያት አደረሰባቸው እነርሱ ግን ‹‹…ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል መከራ ወይስ ጭንቀት፣ወይስ ስደት፣ወይስ ረኀብ፣ወይስ ራቁትነት፣ወይስ ፍረሃት፣ወይስ ሰይፍ ነውን፣ስለአንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን እንደሚታዱ በጎች ተቆጠርን…››( ሮሜ ፰፣፴፭) በማለት ሁሉን በሚያስችል አምላካቸው ሁሉን ችለው ወንጌልን ሰበኩ ፤የተሰጠው የተስፋ ቃል ፣የተነገረው ትንቢት፣ የተመሰለው ምሳሌ መፈጸሙን፣አዳምና ልጆቹ ከሲዖል እስራት፣ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሲዖል ወደ ገነት፣ከውረደት ወደ ክብር መመለሱን አወጁ፤ በአዳምና ልጆቹ ዕንባ መፍሰስ ይፈነድቅ፣ በሰቆቃቸው ይስቅ የነበረ ዲያቢሎስ መታሠሩን ሲዖል ተመዝብራ፣ ገነት መከፈቷን አበሠሩ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ አስቀድሞ እንደነገራቸው ፣እስራቱ፣ ግርፋቱ፣ በእሳት መተኮሱ በሾተል ( በሰይፍ) መመተሩ ተፈራረቆባቸው፤ ቅዱስ ኤፍሬም ቤዛዊት ዓለም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባወደሱበት የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ላይ ‹‹..አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወመዓዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሱ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት..›› ሰማዕታት የዚህችን ዐዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለ ምንግሥተ ሰማያትም መራረ ሞትን ታገሡ፡፡( ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ዳዊት ዘነግሠ) በማለት እንደገለጸው በእምነት ጸንተው በምግባር ጎልብተው ታገሡ፤ ብርኃናቸው በሰው ፊት በራላቸው፣ በሰገነት ላይ ስበኩ ያላቸውን እውነትና ፍቅሩን መሠከሩ ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡
ቅድስት ቤተክረስቲያን ስለክርቶስ ፍቅር መስክረው ሰማዕትነት የጠቀበሉ ቅዱሳን አበው ሐዋርያትን በስማቸው ቤተክርስቲን አንጻ ፣ መታሰቢያቸውን ታከብራለች በተሰጣቸው ቃልኪዳን ምዕመናን እንዲድኑ፣በረከታቸውን እንዲያገኙ ፣በቃል ኪዳናቸው ትማጸናለች፤ ሐምሌ አምስት ቀን መታሰቢያ ከሚደረግላቸው ፣ገድላቸው ከሚዘከርላቸው አባቻችን መካከል ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ የዮና ልጅ ስምዖን ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ስሙ ተጠቅሶ የምናገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ከቅዱስ እንድርያስ ወንድሙ ጋር በመሆን እንደ አባታቸው ዮና ዓሣ እያጠመዱ በመሸጥ ሕወታቸውን ይመሩ ነበር፤ጌታችን ‹‹ ስምዖን ሆይ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን እንድታጠምድ አደርግሃለሁ ›› በማለት ተከተሉኝ ብሎ ወንድማማቾቹን አስከተላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ አብረውት ከነበሩ ሐዋርያት መካከል ፈጣንና ጥያቄዎችን ይጠይቅ ነበረ ሊቀ ሐዋርትም ነው፤ጌታችን ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ ሲጠይቅ ፤ሰዎች የሚሉትን ከገለጸ በኋላ ‹‹ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ ›› ብሎ መሰከረ በዚህም ‹‹ብጹዕ ነህ ››ተብሎ ተመስግኗል ፡፡ (ማቴ ፲፮፤፩ ) ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን በተያዘባት በዚያች ሌሊት እስከ ቀያፋ ግቢ ድረስ ተከትሎ ነበር ፤ከጌታችን ጋር እንደሆነ ሲጠየቅ አላውቀውም ቢልም ንስሐ ገብቶ ተጸጽቶ ጌታችንም ይቅር ብሎታል፡፡
ጌታችን ከማረጉ በፊት ቅዱስ ጴጥሮስን ‹‹ ግልገሎቼን ፣ጠቦቶቼን ፣በጌቼን ጠብቅ በማለት እንዳዘዘው (አደራ እንደሰጠው ) ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በወንጌል ትምህርት እያዳነ ያላመኑትን አሳምኖ ወደ ክርስትና እምነት መልሷል ፡፡ወንጌልን ይሰብክ በነበረበት ወቅት ታስሮ ከወህኒ ቢገባም እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ከእሥር ቤት እንዲወጣ አድርጎታል ( የሐ.ሥራ 12፣1-) ፤ከማስተማር በተጨማሪም ሁለት መልዕክታትን ጽፏል ፤በወንጌል ተልእኮ በነበረ ጊዜ አግርጶስና አስታብዮስ የሚባሉ የሮም መኳንንት ሊያስገድሉት ሲሹ ምዕመናን እንዲሸሽ ግድ አሉት በዚህን ጊዜ ከሮም ከተማ ወጥቶ ሲሄድ ጌታን በዕለተ ዐርብ መስቀል ተሸክሞ እንደነበረ ሆኖ ተገለጸለት ቅዱስ ጴጥሮስም
‹‹ጌታ ሆይ በኢየሩሳሌም አይሁድ እንደሰቀሉህ በሮም ከተማ ልትሰቀል መጣህን ››አለ ጌታችንም ‹‹ በሮም ከተማ የሚሰቀልልኝ ካላገኘሁ እሰቀላለሁ ››አለው ቅዱስ ጴጥሮስም ወደ ሮም ተመለሶ ማስተማር ቀጠለ ኔሮን ቄሣር ይዞ አሰረው ፤ጌታችን አስቀድሞ ‹‹በሸመገልክ ጊዜ ወገብህን ያስታጥቁሃል›› በማለት ስለ አሟሟቱ ነግሮት ነበርና በስቅላት እንዲሞት ሲፈረድበት ‹‹እንደ ጌታዬ ወደ ላይ አትስቀሉኝ የቁልቁሊት ስቀሉኝ አለ ፤ ሊቀ ሐዋርያት ፣ትሁቱና ታታሪው ፣ፈጣኑ ፣ጠይቆ የሚረዳ ፣ተጸጽቶ የሚመለስ በአንደበቱ ትምህርት በተግባር ህይወቱ ክርስትናን የገለጠ የናቃትን ዓለም ዞሮ ያልተመለከተ ኃጢአትን በንስሐ ድል የነሣ አምላኩን ሁሉን ጥሎ የተከተለ ብዙዎችን በትምህርቱ ከጣዖት አምልኮ ወደ ክርስትና ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሞት ወደ ህይወት ያሻገረ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐምሌ አምስት ቀን በመስቀል የቁልቄሊት ሰቅለውት ሰማዕትትነት ተቀበለ ፡፡ ካረፈም በኋላ መርቄሎስ የሚባላው ደቀ መዝሙር ከመስቀል አውርዶ እንደ አገሩ ልማድ በወተት እና በወይን አጥቦ ሽቶ ቀብቶ በነጭ ልብስ ገንዞ በክብር ቫቲካን በሚባል ሥፍራ አኖረው ፡፡ ጸሎቱ በረከቱ በእኛ በሕዝበ ክርስቲያኖች ላይ አድሮ ይኑር አሜን !
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ፡– የቀድሞ ስሙ ሳውል ሲሆን ትርጉሙም ስጦታ ማለት ነው የትውልድ ሥፍራውም በጠርሴስ ከተማ ነው ዕድሜው 15 ዓመት ሲሆነው በኢየሩሳሌም ከተማ ከነበረው የገማልያል ትምህርት ቤት ገባ ፤በዚህም የአይሁድን ሥርዓት እየተማረ እስከ 30 ዓመቱ ቆየ በዚሁም እድሜው የአይሁድ ሸንጎ አባል ሆነ ፡፡ በአይሁድ ሸንጎ አባልነት ለሁለት ዓመታት በሠራበት ወቅት ለኦሪታዊ እምነቱ ቀናተኛ ፈሪሳዊ በመሆኑ ክርስቲያኖችን በማንኛውም አጋጣሚ ይቃወም ነበር ፡፡ሐዋርያት ወንጌልን በሚስተምሩበት ጊዜ ከሚቃወሟቸው መካከል እንዱም ነበር ቅዱስ እስጡፋኖስ በአይሁድ ሸንጎ በቀረበ ጊዜ የተከራከረው እንዲሁም የወጋሪዎችን ልብስ ይጠብቅ የነበረውም እርሱ ነው፡፡
ክርስቲያኖችን ሊያስር ወደ ደማስቆ ከተማ አመራ ጥቂት ሲቀረው ከሰማይ ብርሃን ወርዶ አካባቢውን አለበሰው ሳውልም ከምድር ወደቀ ማየትም ተሳነው ከሰማይም ‹‹ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ ›› የሚለውን ድምጽ ሲሰማ እየተርበተበት ‹‹…ጌታ ሆይ ማን ነህ ?›› በማለት በጭንቅ ውስጥ ሆኖ ጠየቀ ጌታችንም ‹‹አንተ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሪቱ ኢየሱስ ነኝ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል ›› ሲል ተናገረው፡፡ ከአሳዳጅነት ሕይወት አውጥቶ ወንጌልን የሚሰብክ ሐዋርያ አደረገው ፡፡
ቀድሞ ለአይሁድ ሥርዓት በነበረው ቅንዓት የሚታወቀው ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሊሰብክ በመነሳቱ አይሁድ በክፋት ተነሱበት ፤ቀድሞ ያሳድዳቸው የነበሩ ክርስቲያኖች የቅዱስ ጳውሎስን መመለስ ሊያምኑ አልቻሉም፤በሁለት በኩል ፈተናዎች ገጠሙት፤ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ ወንጌልን ሰበከ፤ለደቀመዛሙርቱ ( ለምዕመናን ክርስያን የሚለውን ስያሜ የሰየመው ቅዱስ ጳውሎስ ነው ። ‹‹ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ››የሐ ሥራ ፲፩፤ ፳፯ ቅዱስ ጳውሎስ ለወንጌል ተልዕኮ ሦስት ታላላቅ ጉዞዎችን ወደ ተለያዩ አገራት አድርጓል በዚህም አገልግሎቱ ብዙ መከራን ተቀብሏል ፡፡ አስረውታል ፣ገርፈውታል ብዙ እንግልትን ተቀብሏል፤ለቆሮንቶስ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ስለደረሰበት መከራ እንዲህ ገልጧል ‹‹ …በድካም አብዝቼ ፣በመገረፍ አብዝቼ ፣በመታሠር አትርፌ ፣በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ ፡፡አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ጅራፍ አምስት ጊዜ ገረፉኝ ፡፡ ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ ፣አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርኩ ፣መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ ፤ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድኩ በወንዝ ፍርሃት ፣በወንበዴዎች ፍርሃት ፣በወገኔ በኩል ፍርሃት ፣በከተማ ፍርሃት ፣በምድረ በዳ ፍርሃት ፣በባሕር ፍርሃት ፣በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም በመጦም በብርድና በራቁትነት ነበርሁ የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተክርስቲያናት አሳብ ነው ፡፡›› 2ኛ ቆሮ ፲፩፣፳፫-፳፱
ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ከአገር አገር እየዞረ ከማስተማሩ በተጓዳኝ 14 መልዕክታትን ጽፏል ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን በማስተማሩ ተይዞ ወደ ሮም ተወሰደ ኔሮን ቄሣር ቅጥ ባጣ ጥጋቡ የሮምን ከተማ ካቃጠለ በኋላ ሕዝቡ በከተማዋ መቃጠል በመቆጣቱ ፣በማዘኑ ጥፋቱን በክርስቲያኖች ላይ አሳበበ ክርስቲያኖችን ሲያሳድዱ ሲገርፉ ፣ሲገድሉ ቅዱስ ጳውሎስም በ65 ዓ.ም በኒቆልዮን ከተማ ሲያስተምር ተይዞ ወደ ወኅኒ ገባ ለሁለት ዓመታት ከስድስት ወር በጨለማ ቤት ታስሮ ከቆየ በኋላ በሮም ከተማ በተወለደ በ74 ዓመቱ ሐምሌ አምስት ቀን አንገቱን ተቀልቶ በሰማዕትነት አለፈ ፡፡በረከቱ ይደርብን አሜን ፡፡
ውድ ክርስቲያኖች የአባቶቻችንን ገድል ሰማዕትነት ስንሰማ፣ በዓላቸውን (መታሰቢያቸውን) ስናከብር፤ በረከታቸውን ለመቀበል ብቻ ሳይሆን ፈለጋቸውን በመከተል በምገባር ልንጎለብት በእምነት ልንጸና ይገባናል ዓለም ለክርስቲያኖች የድሎት ቦታ ሳትሆን የመከራ ስፍራ ናት፣ ጌታችን ‹‹ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ…›› በማለት እንደገለጸልን ፣በስሙ በማመናችን ጠላት ዲያብሎስ በተለያየ መልኩ ፈተናዎችን ያመጣልና በእምነታችን ጸንተን በትእግስት ሆነን ልንታገለው ይገባል። ቤተ ክርስቲያን በባህር ላይ እነደሚሄድ ወጀቡ ማዕበሉ እንደሚያንገላታው መርከብ ናት ግን ደግሞ አትሰጥምም ፤‹‹የገሃነም ደጆች አይችሏትም›› ( ማቴ ፲፮፣፲፰ ) ተብላልና ፤ይታገሏታል አያሸንፏትም፣ ቀስታቸውን ያስወንጭፋሉ ግን አይጎዷትም፤ምክንያቱም በጽኑ ዓለት ላይ ተመሠርታለችና፤ በዘመነ ሰማዕታት በዋሻ ውስጥ ሆና አልጠፋችም የመከራው ዘመን ሲያልቅ ዳግመኛ በራች፣ሰፋች፣ ውድቀቷን የሚመኝ ጠላት ዲያስን ድል አደረገች ፡፡ ውድ ክርስያኖች በክርስትና ሕይወት ስንኖር ፈተናው መልኩን ይቀይራል እንጂ አይቀርም፤ አምላካችን ደግሞ መሸከም ከምንችለው በላይ እይሰጠንም ‹‹ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜ ቀሊል…›› ( ማቴ፲፩፣፴ ) ብሎናልና ፤የአበው ቅዱሳን ሰማዕታትን ፈለግ በመከተል በእምነታችን ጸንተን፤ ከሞት በኋላ ላለው ሕይወታችን ‹‹ … ኑ እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን ምንግሥቴን ውረሱ››( ማቴ ፳፭፣፴፭) የሚለውን ሕይወት ቃል ለመስማት ያብቃን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
