ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
በቀሲስ ኃይሉ ብርሃኑ
ሰኔ ፴ በዚች ዕለት ነቢይ ሰማዕትና ሐዋርያ የሆነ መጥምቁ ዮሐንስ ተወለደ።
ዮሐንስ ማለት እግዚአብሔር ጸጋ ነው ማለት ነው፡፡ትርጓሜ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላናደስታ) ይለዋል ፤ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና /ሉቃ.፩፥፲፬/፡፡በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ ሄሮድስ የመድኀኒታችን የክርስቶስን መወለድ ከሰብአ ሰገል ሲሰማ መንግሥቴን ይወስድብኛል ብሎ ስለሠጋ ጌታችንን ያገኘሁ መስሎት የቤተልሔም ሕፃናትን መግደል ጀመረ/ማቴ.፪፥፩-፲፮/፡፡
በዚህ ጊዜ ቅድስት ኤልሳቤጥ ልጇን ከሞት ለማዳን ስትል ሕፃኑ ዮሐንስን ይዛ ወደ በረሃ ተሰደደች።
በበረሃም ድንጋይ ቤት ሆኖላቸው፣እግዚአብሔርም ከብርድ፣ከፀሐይና ከአራዊቱ አፍ እየጠበቃቸው መኖር ጀመሩ፡፡ ወደ በረሃ ሲገቡ ቅዱስ ዮሐንስ የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሕፃን ነበር፡፡ ሕፃኑም አደገ ፤በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ /ሉቃ.፩፥፹/ተብሎ እንደተጻፈ፡፡
ይህም በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ ለእግዚአብሔር ልጅ የሰገደው ነው፣ በመድኅነ ዓለም ክርስቶስ ራስ ላይ እጁን ጭኖ በውኃ ያጠምቀው ዘንድ የተገባው ነው። በቅዱስ ወንጌል እንደ ተነገረ ወንድ ልጅን ትወልድ ዘንድ የኤልሳቤጥ የፅንሷ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወንድ ልጅን ወለደች፤ ዘመዶቿና ጐረቤቶቿ እግዚአብሔር ቸርነቱን እንዳበዛላት በሰሙ ጊዜ ስለእርስዋ ደስ አላቸው።
በስምንተኛውም ቀን ሊገዝሩት መጡ፣ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ጠሩት እናቱ ግን አይሆንም ዮሐንስ ይባል አለች። ”ከዘመዶችሽ ስሙ እንዲህ የሚባል የለም” አሏት። አባቱንም ጠቅሰው ”ማን ሊባል ትወዳለህ?”አሉት፤ እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ ዮሐንስ ይባል ብሎ ጻፈ ።ሁሉም አደነቁ ያን ጊዜም አንደበቱ ከድዳነት ተፈትቶለት ተናገረ፣ እግዚአብሔርንም ፈጽሞ አመሰገነው። ስለ ልጁና ስለ መድኃኒታችን መምጣት ልጁ ዮሐንስም የልዑል ነቢይ እንደሚባልና በእግዚአብሔርም ፊት እንደሚሄድ ትንቢት ተናገረ።
ሰብአ ሰገልም መጥተው ከሄዱ በኋላ ሄሮድስ ሕፃናትን በገደላቸው ጊዜ ስለ ሕፃኑ ዮሐንስ ለሄሮድስ ነገሩት። እርሱም እንዲገድሉት ጭፍሮችን ላከ ። ጭፍሮችም ወደ አባቱ ዘካርያስ መጡ ፤ሕፃኑንም ከእርሱ ፈለጉት። አባቱም አንሥቶ በትከሻዎቹ ተሸክሞ ወደ ቤተ መቅደስ ከእርሱ ጋር እንዲሄዱና ሕፃኑን ከዚያ እንዲወስዱት ወታደሮችን ለመናቸው።
ከዚህም በኋላ ሕፃኑን በመሠዊያው ጠርዝ ላይ አኖረውና ከዚህ ራሳችሁ ተቀብላችሁ ውሰዱት አላቸው ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መልአክ ነጥቆ ወደ በረሃ ወሰደው፤ ጭፍሮችም ባላገኙት ጊዜ አባቱ ዘካርያስን ገደሉት፤ ሕፃኑ ግን አድጎ ለእስራኤል እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ በበረሃ ውስጥ ኖረ።
በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ውስጥ ቅዱስ ወንጌል ላይ ከተጻፉት ከእመቤታችን ቀጥሎ ክብሩ የተገለጠለት የነዘካርያስን ቤተሰብ ነው። ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: “ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ”(ሉቃ.፩፥፮)
ከሁሉ አስቀድሞ “ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም” (ማቴ ፲፩፥፲፩) ተብሎ በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰከረለት ቅዱስ ዮሐንስ የተገኘው በጽናት በጸለዩ፣ በእግዚአብሔር ፊት በንጽሕና ከኖሩ ወላጆች ነው። ይህ የቅዱሳን ወላጆቹን የዘካርያስና የኤልሳቤጥን ጽናት፣ ዮሐንስን ለመወለድና ልጃቸውም ጌታችንን ለማጥመቅ እንዲመረጥ አድርጎታል።
በወንጌልም ቅዱስ ሉቃስ “የዘካርያስ ልጅ፣ የኤልሣቤጥ ልጅ” ብሎ ይጀምራል፡፡ ይህም የሆነው እንዲሁ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ “እንግዲያስ የዚህ ምክንያት ምንድን ነው?” ቢሉ፡- የጌታ የልደቱ ዘር ሲቈጠር የዮሐንስ ልደት ዘር መቈጠሩ የሰው ልጅ ከጌታ ጋር የሚቈጠርበት ዘመን እንደ መጣ ለማብሠር ነው፡፡ የጌታ ልደት እንደ ተጻፈ የሰው ልደት መጻፉ የሰው ልጅ ምን ያህል ክቡር እንደ ሆነ ለማጠየቅ ነው፡፡ ክብራችን እንደ ተመለሰ ለማብሠር ነው፡፡ለዚህ ደግሞ ስለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ልደት ሲናገር፦ “በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፡፡ ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ” ይላል(ሉቃ.፩፥፭)፡፡
በሌላ መልኩ በቅዱስ መጽሐፍ “አንድ ሰው ነበረ፣ አንድ ካህን ነበረ” የሚሉትና የመሳሰሉት አገላለጾች ከተነገረላቸው ቅዱሳን ደግሞ ካህኑ ዘካሪያስና ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መለኮት ይጠቀሳሉ፡፡ ምክንያቱም በምድር ሺህ ሞቶ ሺህ ተወልዶ እያደረ በያዘው ዓላማ ላይ የተገኘ ሰው ግን ከዚያ ሰው በቀር ሌላ ሰው ሳይኖር ሲቀር፦ “አንድ ሰው ነበረ” ብሎ ይናገራልና፡፡
ካህኑ ዘካርያስም እንደዚሁ “አንድ ካህን ነበረ” መባሉ በብሥራተ መልአክ የተወለደ ደግ ካህን፤ በእግዚአብሔር ፊት የጸደቀ ንጹሕ ካህን፤ ጸሎቱ የጻድቅ ሰው ጸሎት ከአፉ እስከ ጆሮ ነው” እንዲል ጸሎቱ የተሰማለት ባለሟል ካህን፣ ያለ ነውርያለ ነቀፋ የኖረ፣ ክህነቱ የጠራ ጽሩይ ካህን፤ ሕግን በመጠበቅ “ይህ ቀርቶታል” የማይባልና በውኃ ዳር የተተከለ የክህነት ዛፍ፤ “መከነች” ብሎ ሚስቱን ፈትቶ ክህነቱን ያልሻረ ጽኑዕ ባለ ተስፋ ካህን፤ የክህነተ ኦሪት መደምደሚያ፣ የብዙዎች ደስታ የዮሐንስ አባት ነቅዐ ፍስሐ ካህን፤ የአምላኩን መንገድ የሚጠርገውን ያበቀለ ንጹሕ ሥር ፤ እሳቱን በውኃ ያጠመቀውን ገሣሤ እሳት ምድራዊ ሱራፊ ሰማያዊ ሰው የወለደ ካህን፤ ሰው ሆኖ መልአክን የወለደ ካህን፤ ምድራዊ በግ እየሠዋ “የእውነተኛ በግዕ ሚዜ ልደት የሰማ ካህን፤ የሰማዕቱ ዮሐንስ አባት ሰማዕቱ ካህን፤ ፀሐየ ጽድቅን ያዘለች ሰማይ ቤቱን የባረከችለት ካህን፤ ባለ ትዳርነትንም፣ ጻድቅነትንም፤ ሰማዕትነትንም፤ ክህነትንም፣ ዐቂበ ሕግንም ሁሉ አስተባብሮ የያዘ የምግባር ቅመም ንጹሕ ካህን ስለሆነ ነው።
እንደ ዮሐንስ ያለ ሌሎች አልወለዱምና፥ ስለዚህ “አንድ ካህን” አለ።
ተብሎ ተናግሮለታል ለካህኑ ዘካሪያስ።
ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ከሆነ ምስክሩ ራሱ እግዚአብሔር ነው ፡፡ “አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስምዐ ይከውኑ – አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ምስክር ይሆናሉ” እንዳለ አባ ሕርያቆስ፡፡ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ጽድቃቸው በእግዚአብሔር ፊት ስለ ነበረ እግዚአብሔር ደግ ልጅ ሰጥቶ መሰከረላቸው።
ቅዱስ ዮሐንስ የካህኑ ዘካርያስ ልጅ ሲሆን ከመወለዱ በፊት የግብሩ ዓይነት፣ የትምህርቱ ስልት የአኗኗሩ ሂደት እንዴት እንደሆነ አስቀድሞ በነቢያት የተነገረለት በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ተፀንሶ ኋላ በአባቱ በዘካርያስ ትንቢት የተወለደ ነው።
ዮሐንስ ባለ አምስት መዓርግ ነው። ይህ ማለት ባሕታዊ፣ ሰማዕት፣ ነቢይ፣ ሐዋርያ፤ ካህን ነው።
ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹የጌታን መንገድ አዘጋጁ፣ ጥርጊያውንም አቅኑ›› እያለ
በምድረ በዳ የሚጮኽ የሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነው ፤በማለት የክርስቶስ ዐዋጅ ነጋሪ መስካሪ፣፣ የወንጌል አብሣሪ መሆኑን አስቀድሞ ትንቢት የተናገረለት ሳይበላ ሳይጠጣ በጾም በትሕርምት የኖረ ባሕታዊ እንደሆነ ቅዱስ ማቴዎስ ከጽቦልናል።(ማቴ ፫፥፫ )
የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!
እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ ደግሞ 100 ዓመት ደርሶ ነበር:: ፍጹም መታገሣቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ፣ ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. ፵:፫, ሚል. ፫:፩) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው።
ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና በመጠራጠሩና በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ፀንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእኅትማማች ልጆች ናቸው።
+የአምላክ እናቱ ስትደርስና “ሰላም” ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና፣ ዮሐንስ ደግሞ ገና በማኅፀን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በኋላ በዚህች ቀን (ሰኔ 30) ተወልዶ አባቱ ዘካርያስ “ዮሐንስ” ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል።
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፡-የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
- በማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት
- በበርሃ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
- እስራኤልን ለንስሐ ያጠመቀ
- የጌታችንን መንገድ የጠረገ
- ጌታውን ያጠመቀና
- ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው።
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ከላይ እንዳየነው ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት፣ጻድቅ፣ ገዳማዊ፣ መጥምቀ መለኮት፣ ጸያሔ ፍኖት፣ ቃለ ዐዋዲ ብላ ታከብረዋለች።
በመጨረሻም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ድንበር አታፍርሱ፤ዋርሳ አትውረሱ፤እያለ ንጉሡ ሄሮድስን እና ሄሮድያዳን በመገሠፁ ምክንያት መስከረም ፪ አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የራስቅሉ ክንፍ አውጥቶ በዓለም እየተዘዋወረ ፲፭ (አምስት ዓመት) ወንጌልን አስተምሯል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ በቤተ ክርስቲያን የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በእነዚህ ዕለታት ይከበራል።
1/ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት
2/ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤
3/ መስከረም ፪ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት
4/ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤
4/ የካቲት ፴ቀን ራሱ የተገኘችበት፤
5/ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ
የወጣችበት)፤
6/ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት)በዓል
በቤተክርስቲያናችን ይከበራል፡፡
- ከዚህ ቤተሰብ እኛ ብዙ ነገር የምንማርባቸው ሲሆን
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ጽናት ሲያስተምር እንዲህ ይላል፦
“እግዚአብሔር ልጅ የነሣቸው ስለጠላቸው ወይም ስለቀጣቸው አይደለም፤ ይልቁኑ ታላቅና ድንቅ የሆነውን ፍሬ በታላቅ ተአምር ሊሰጣቸው እንጂ። መካንነታቸው የሰማያዊው ዐዋጅ ነጋሪ መገኛ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔርን ክብር ገለጠ።” ይህም
- በትዕግሥት በመጸለይ፡ ባልና ሚስት ልጅ ሳይወልዱ እስከ እርጅና ዘመናቸው ድረስ በእምነትና በጸሎት ጸንተዋል። ይህም ምእመናን የጸሎት መልስ ባይሰጣቸው እንኳ ሳይታክቱ መጸለይ እንዳለባቸው ያስተምራሉ።
- በእግዚአብሔር ፊት በጽድቅ መመላለስ፣መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱንም “በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ የሚሄዱ ጻድቃን ነበሩ” ይላቸዋል። ይህ ለክርስቲያን ባለትዳሮችና ለቤተሰብ ታላቅ አርአያ ነው።
- የእግዚአብሔርን አሠራር ማክበር፡ ሕፃኑ ሲወለድ ዘመዶቻቸው በቤተሰብ ስም “ዘካርያስ” ሊሉት ሲሉ፣ ኤልሳቤጥና ዘካርያስ ግን መልአኩ የነገራቸውን መለኮታዊ ትእዛዝ አክብረው “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብለዋል። ይህም ለፈቃደ እግዚአብሔር መገዛትን ያስተምራል።
ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በበኩሉ የዮሐንስንና የጌታችንን ትስስር በማኅፀን ውስጥ ሲገልጥ፦
“ክብርት የምትሆን ኤልሳቤጥ ድምፅሽን በሰማች ጊዜ ማኅፀኗ የመቅደስ ታቦት ሆነ፤ በውስጡም ያለው ሕፃን (ዮሐንስ) እንደ ካህን ሆኖ በደስታ ለጌታው ሰገደ።”ይህም ክብርያገኘው፡-
- ንጽሕናና ራስን መግዛት፡ ቅዱስ ዮሐንስ በበረሃ በምናኔ (በትሕርምት) ያደገ፣ ከአልኮልና ከዓለም ምቾት የራቀ ነበር። ይህ ለወጣቶች ራስን ከዓለም ፍትወት፣ ከሱስና ከአልባሌ ነገሮች ጠብቆ በንጽሕና ለመኖር ትልቅ አቅም ይሆንላቸዋል።
- እውነትን መመስከር (ባለመለማመጥ)፡ ቅዱስ ዮሐንስ ኃያሉን ንጉሥ ሄሮድስን ሳይፈራ “የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም “( ማር ፮፥፲፰) በማለት ስለ እውነት መስክሯል። ይህም ወጣቶች ለጥቅም ወይም ለሰው ፍርሃት ሳይሉ ለእውነትና ለጽድቅ እንዲቆሙ ያስተምራል።
- ትሕትና፡ ቅዱስ ዮሐንስ ታላቅ ክብርና ተሰሚነት እያለው፣ ስለ ክርስቶስ ሲናገር “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል። ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የባሕርይው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል።“ ዮሐ ፫፥፴-፴፩” ብሏል። የጫማውን ጠፍር እንኳ ለመፍታት እንደማይበቃ በመግለጽ የትሕትና ጥግ አሳይቷል። ይህ ዛሬ ላለው ትውልድ ከትዕቢት የመራቅን ምሥጢር ያስተምራል።“ዮሐንስ ሕዝቡ ሁሉ እንደ መሲሕ ሊያከብረውና ሊከተለው ሲፈልግ፣ እርሱ ግን በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጎ የክርስቶስን ታላቅነት መሰከረ። የጫማውን ጠፍር ለመፍታት እንኳ እንደማይበቃ የተናገረው ቃል ዛሬ ላለን ክርስቲያኖች በትዕቢት እንዳንወድቅ የትሕትና ታላቅ መስተዋት ነው።“
ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን የምታስተላልፈው መልእክት
- የንስሐ ሕይወት፡ የቅዱስ ዮሐንስ ዋና ስብከቱ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” የሚል ነበር። ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘወትር በንስሐ ታድሰው ለቅዱስ ቁርባን እንዲበቁ የምታስተምረው እሱን አብነት አድርጋ ነው።
- መንገድ ጠራጊ መሆን፡ ቅዱስ ዮሐንስ ለክርስቶስ መንገድ እንደጠረገ፣ ምእመናንም በበጎ ምግባራቸው፣ በፍቅራቸውና በደግነታቸው ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ (መንገድ ጠራጊ) መሆን እንዳለባቸው ትመክራለች።
“ዮሐንስ በሥጋ የሚኖር መልአክ ነበር”። ምድራዊ ምቾትንና የዓለምን ፈቃድ ትቶ በበረሃ በመኖሩ፣ የሰው ልጅ በጾምና በጸሎት ራሱን መግዛትና ከኃጢአት መራቅ እንደሚችል በተግባር አሳይቶናል። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
“ዮሐንስ የነቢያት ፍጻሜና የወንጌል መጀመሪያ ነው።” የብሉይ ኪዳንን ሕግ አክብሮ፣ የሐዲስ ኪዳንን በግ (ክርስቶስን) በጣቱ ያመለከተ የታላላቆች ታላቅ ነው። ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድሪያ
ጸሎቱ ወበረከቱ ለቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ይኅድር በላዕሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን❗️
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ
ጸያሔ ፍኖት
መዝገበ ቅዱሳን በተመሳሳይ የሚጠሩ ቅዱሳን ስም
የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ
ኆኀተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ ፩
