ሰንበት ትምህርት ቤቶች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ መሳካት ያላቸው ሚና
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ትውልዱ ወደ ዘመናዊ ትምህርት በማዘንበል ሃይማኖቱን ችላ እንዳይል በማሰብ አባቶቻችን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶን በማወቅ የሚያድግ፤ መልስ ያለው ትውልድ ለመፍጠር ከ1935-1940 ዓ/ም ባለው ጊዜ ሰንበት ት/ቤትን እንደመሠረቱ የሚታወቅ ሲሆን ቀጥሎም በ 1953 ዓ.ም መመሪያ ወጥቶለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ትእዛዝ በየአጥቢያ ቤተ-ክርስቲያኑ ሰንበት ት/ቤት እንዲቋቋም የተደረገ ሲሆን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመን በቃለ ዓዋዲው የሰንበት ት/ቤት አወቃቀር በመመሪያ ተካተተ::
የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ዋና ተልእኮ እና ግብ ሰዎች በሃይማኖት፣ (ይህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በማመን እና ያመኑት ደግሞ ሥራቸው ይከተላቸዋልና) በሥነ ምግባር ጸንተው እንዲኖሩ በማድረግ ለመንግሥቱ ማብቃት ነው። በቃለ ዐዋዲው መሠረትም ይህንን ተልእኮ ለመወጣት በሕፃናትና በወጣቶች በኩል ያለውን ኃላፊነት ለሰንበት ትምህርት ቤት በይፋ ተላልፏል።
ሰንበት ትምህርት ቤቶችም እንደ ተቋም ከሕፃንነት እስከ የነገ ተረካቢ፥ ወጣቶች ድረስ ይህንን ትውልድ የመገንባት ሥራውን በሚገባ ለመወጣት በተናጥልም ሆነ በትብብር በአንድነት አደረጃጀቶችን በመጠቀም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ እየተወጡ ይገኛሉ።
ወጣቱ ትውልድ በአስተዳደግ፣ ፣ማኅበረሰባዊ ጫናዎች፣ የዘመናዊ ትምህርት መስጫና የብዙኀን መገናኛ ተቋማት በአብዛኛው መንፈሳዊነትን የማያበረታቱ፣ ይልቁንም ሚዛኑ እጅግ ወደ ሥጋዊውና የሰው ልጆች ፈቃድ ማሟያ፣ ዕውቀትና አኗኗር ላይ ትኩረቱን በማድረግ መንፈሳዊነትን እያዳከመ ሉላዊ ለመሆን እየተጓዘ ባለበት በአሁኑ ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን በዋጀ መልኩ ተከታዮቿን፤ በተለይም ወጣቱን ትውልድ በክርስትና የምታንጽበት ስልት ከማናቸውም ጊዜ በበለጠ ማጠናከር ይገባታል።
ሰንበት ት/ቤቶች አገልጋይ ከማፍራትና ትውልድ ከማነጽ አንጻር ምን እየሠሩ ነው?
ሰንበት ትምህርት ቤቶች የነገዋን ቤተ ክርስቲያን የሚረከቡ ሕፃናትን እና ወጣቶችን ዘመኑን በዋጀ መንገድ ለማብቃት የአገልጋይነት እሳቤን በሁሉም ዘንድ ታሰርጻለች። በነጻ የተቀበለውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በነጻ ለመስጠት የተዘጋጀ እና የሚተጋ አገልጋይን በመፍጠር ከሰጥቶ መቀበል ፅንሰ ሐሳብ በላይ የሆነውን ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው በማለት ለበረከት የሚጋደል አገልጋይን እያፈራ ይገኛል። ይህም የነገዋን ቤተ ክርስቲያን በተለያየ የሙያ ዘርፍ በማስተማር፣ በክህነት፣ በአስተዳደርና በልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚሳተፍ ለሀገር የሚበቃ ንጹሕ ትውልድን የማድረስ ሥራ ነው።
ለሰንበት ት/ቤቶች የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት ትግበራና ያስገኘው ውጤት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመሠረቷ ልጆችዋን የምትቀርጽበት፣ የምታስተካክልበት እና የምትገነባበት ሥርዓተ ትምህርት በገዳማት እና የአብነት ት/ት ተቋማት ቢኖራትም ሰንበት ትምህርት ቤት ከተቋቋመበት 1930ዎቹ ዓመተ ምሕረት ወዲህ ግን መነሻውና መድረሻው የታለመለት ወጥ ሥርዓት አልነበረም። ከ2011 ዓ/ም ጀምሮ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በኋላ በትግበራ ላይ የሚገኘው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ከ40 በላይ አህጉረ ስብከቶች በሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሙሉ እና በእርከን የተጀመረ ሲሆን ይህም በጎ የሆኑ ውጤቶችን ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ብሎም ለተማሪዎች አምጥቷል።
በተለይም ለአብዛኛዎቹ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ፈተና የነበረው ወጥ የሆነ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የመምህራን እና የተማሪዎች ግንኙነት በክፍለ ትምህርቶች፣ የጊዜ ሰሌዳ፣ የትምህርት ርእሶች፣ የፈተና ጊዜያት፣ ምዘናና እርከኖች በማስታረቅ የተሰናሰለ የትምህርት ወቅት እንዲኖር አስችሏል። ተማሪዎችም በየዕድሜ እርከኖቻቸው ለአእምሯቸው፣ ለክሂሎታቸውና እድገታቸው የተመጠነ ሃይማኖታዊ እሳቤን እንዲይዙ የሚያስችል ሲሆን ይህም ጎን ለጎን እንዲሁም ከታች ወደላይ በተግባባ እና በተቀናጀ መልኩ ለዋናው ግብ መሰላል እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
በተጨማሪም ለልጆቹ ምን እንዴት መቼ እና በምን ሁኔታ ላስተምር የሚሉትን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሥራ በመሥራት እነርሱ በሌሎች አስቻይ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ በመተግበር፣ በመገምገም እና የመፍትሔ ሐሳቦችን በመሰብሰብ ግብዐት የመላክ እና የማሻሻል ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እንዲያድረጉ ረድቷቸዋል።
ለሥርዓተ ትምህርቱ አጋዥ የሆኑ መማሪያ መጻሕፍት ተዘጋጅተው የተሰራጩ ሲሆን ይህም የማስተማሪያ ኖቶችን እና የምንጭ እጥረቶቹን በመቀነስ አገልግሎቱን ለማስኬድ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። በሥርዓተ ትምህርቱ የ4ኛ፣ 8ኛ፣ 10ኛ የአህጉረ ስብከት አቀፍ ፈተናዎችን እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናዎች መስጠት የተቻለ ሲሆን ይህም ቁጥሩ እያደገ እና በስትራቴጂክ እቅዱ የታለመውን የተማሪ ቁጥር ለማሳካት አይነተኛ ማሳያ ሆኖ ይታያል።
የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ
ሰንበት ትምህርት ቤቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር የተሳሰረ እና የተገመደ ለሌሎችም ጠቃሚ በሆነ መንገድ ኦርቶዶክሳዊ ማንነትን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ይሰጣሉ። ከእነዚህም መካከል ትውልዱን በሃይማኖት እና በሥነ ምግባር የማነጽ ውጤት ያላቸው ሲሆኑ ከራሳቸው አልፎ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን ሊጠቅሙ የሚችሉ ናቸው። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹም በማስተማር እና በማብቃት፣ የአገልግሎት ሱታፌን በማሳደግ (ይህም በበዓላት እና የውስጥ አገልግሎቶች)፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ለውስጥ እና በውጪ ላሉ መድረስ ለሚቻልባቸው፣የምእመናንን ተሳትፎ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማሳደግ፣ የዕቅበተ እምነት ሥራዎችን አባላትን በማጽናት ምእመናንን ማበረታታት የጠፉትን ወደ በረቱ የመመለስ ሥራ፣ ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ኦርቶዶክሳውያን በምጣኔ ሀብት ሊኖራቸው የሚገባውን ንቃተ ኅሊና የማስተካከል እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛል።
በአጠቃላይ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ መሳካት የሰንበት ት/ቤቶች ሚና ምን መምሰል አለበት?
ሰንበት ት/ቤቶች ሕፃናትን በምግባር ማሳደግ፤ ወጣቶችን በሃይማኖት ማጎልመስ እና የአባቶችን አደራ ተረክቦና ጠብቆ የሚያስረክብ ባለ ራእይ ትውልድ መፍጠር ዋና ዓላማው ነው፡፡ ሚናውም
- ሃይማኖቱን ጠንቅቆ ያወቀ መልስ ያለው ትውልድ መፍጠር
- ለቤተ-ክርስቲያንና ለሀገር የውስጥ ጉልበት፤ የውጭ ውበት የሚሆኑ ዜጎችን ማፍራት
- የቤተ-ክርስቲያንን ተልእኮ የሚያሳኩ፣ ጠላቷን የሚረቱ ባለ ራእይ ወጣቶችን መቅረጽ ነው።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
