መንፈሳውያን በዓላት እና አሉታዊ አስተሳሰቦች – ክፍል አንድ

ketera1

በዳዊት አብርሃም

የካቲት ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዓል ‹‹አብዐለ-  አከበረ፤ አስከበረ›› ከሚለው ግስ የወጣ ሲኾን ትርጕሙም የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፤ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፤ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎት፣ ለብሶ፣ አጊጦ የሚዘምርበት፤ ዕልል የሚልበት ማለት ነው (ኪ.ወ.ክ. ገጽ ፪፸፰-፪፸፱)፡፡ ከዚህ መዝገበ ቃላዊ ፍቺ በርከት ያሉ ጽንሰ ሐሳባዊ ትርጕሞችን የምናገኝ ሲኾን የተወሰነቱን እንደሚከተለው እንመልከት፤

በዓላት የሚከበሩ ናቸው

በዓላት ምእመናን ከዘወትር ሥራዎቻቸው አርፈው በምትኩ መንፈሳዊ ተግባራትን በማከናወን የሚያከብሯቸው ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስለ በዓላት አከባበር በተሠራው ቀኖና በበዓላት ወቅት የማይፈጸም መንፈሳዊ ሥራ ስግደት ነው፡፡ ስግደት ሥጋን የሚያደክም ስለኾነ በበዓላት ወቅት አይሰገድም፡፡ ሌሎች መንፈሳዊ ሥራዎች ግን በበዓላት እንዲፈጸሙ ይፈቀዳል፡፡ ተግባረ ሥጋን በበዓላት መተው አስፈላጊ የሚኾንበት ምክንያት መንፈሳዊ ሥራ ለመሥራት እንዲቻል ነው፡፡

በዓላት የደስታ ዕለታት ናቸው

‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና የምስጋና ቃል አሰሙ›› (መዝ.፵፩፥፭) እንደ ተባለው፤ በዓል የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ ከምግብ የሚከለከሉበት ወይም የሚጾሙበት ዕለት ሳይኾን ደስ የሚሰኙበት፣ በደስታ ውስጥም ኾነው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ቀን ነው፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹ደስ ያለው ይዘምር›› (ያዕ. ፭፥፲፬) እንዳለው የደስታ ቀን በኾነው በበዓል ስብሐተ እግዚአብሔር በስፋት ይቀርባል፡፡

በዓላት የዕረፍት ቀናት ናቸው

ሌሎች ቀናት የሥራ ቀናት ናቸው፡፡ በዓላት ግን ከእነዚህ ከብዙዎቹ ቀናት ተለይተው ሰው ከሥራው (ከተግባረ ሥጋው) የሚያርፍባቸው ዕለታት ናቸው፡፡ የበዓላት ጥንት የኾነችው ቀዳሚት ሰንበት እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ ያረፈባት በመኾኑ እግዚአብሔር ሰዎች እንዲያርፉባት፤ በዕረፍትም ኾነው እንዲያከብሯት አዝዟል (ዘፍ. ፪፥፩-፫)፡፡ ኾኖም ማረፍ ማለት እጅና እግርን አጣጥፎ መዋል ማለት አይደለም፡፡ በዓላት ከተግባረ ሥጋ የሚታረፍባቸው ዕለታት ቢኾኑም በበዓላት ወቅት መንፈሳዊ ሥራ መሥራት ተገቢና አስፈላጊ መኾኑ ‹‹ክርስቲያኖች እንደ አይሁድ በዕለተ ቀዳሚት ሥራ ፈትተው መዋል አይገባቸውም፡፡ ይልቁንም ለክርስቲያን እንደሚገባ ሥራ ሊሠሩ ይገባቸዋል፤›› ተብሎ በፍትሐ ነገሥት ታዝዟል፡፡

በዓላት የመታሰቢያ ዕለታት ናቸው

እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ከሥራው ያረፈባትን የሰንበት ዕለት እንድናስባት አዝዞናል፡፡ ተአምራት ያደረገባቸውን፣ እስራኤል ዘሥጋን በግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣበትንና የመሳሰሉትን ዅሉ በበዓላት እንዲታሰቡ አዝዟል (መዝ. ፻፲፥፬)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ‹‹ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› በማለት አዝዟል (ሉቃ. ፳፪፥፱)፡፡ የፈጣሪን ሥራም ብቻ ሳይኾን ቅዱሳን ጻድቃንንና ሥራዎቻቸውን መዘከር የበዓላት አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል›› ተብሎ መጻፉም ስለዚህ ነው (መዝ. ፻፲፯፥፳፬)፡፡

የበዓላት አከባበር

በዓላት በልዩ ልዩ መንገዶች ይከበራሉ፡፡ በበዓላት የሚከናወኑ መንፈሳዊና ሕዝባዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ የተወሰኑ በዓላትን ሕዝብ ወደ ዐደባባይ በመውጣት በጋራ ያከብራቸዋል፡፡ አከባበሩም በዋናነት በጋራ ኾኖ የሚፈጸመውን ሥርዓተ አምልኮና የምስጋና ሥርዓት የሚያመለክት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እስራኤል ዘሥጋ በዓላትን ሊያከብሩ ወደ ዐደባባይ ሲወጡ ይዘምሩ ነበር፡፡ ይዘምሩዋቸው ከነበሩ ዝማሬያት መካከልም በመዝሙረ ዳዊት ከመዝሙር ፻፲፱ እስከ ፻፴፫ ያሉት የመዝሙር ክፍሎች ይገኙባዋል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፴፩)፡፡ ክቡር ዳዊትም በታቦቱ ፊት በቤተ መቅደስ ምስጋና የሚያቀርቡ ካህናትን መድቦ ነበር (፩ኛ ዜ.መ. ፲፮፥፬)፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ በዐደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል ቤተ ክርስቲያን የምታውቃቸው ሁለት ዋና ዋና በዓላት የሚገኙ ሲኾን እነዚህም በዓለ መስቀልና በዓለ ጥምቀት ናቸው፡፡ ከዐደባባይ በዓላት መካከል በዓለ መስቀል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ተርታ ለመመዝገብ የበቃ ታላቅ በዓል ሲኾን ጥምቀትም በዐደባባይ በዓልነቱ ከአማንያኑ በተጨማሪ የብዙዎችን በተለይም የውጪ ቱሪስቶችን በመሳብ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ በዓል ነው፡፡ ከወር በፊት በድምቀት ያከበርነው በዓለ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያናችን ታቦታትን በማውጣት የምታከብረው ዐቢይ በዓል ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የማስተማር ሥራውን የጀመረው በጥምቀት ነው፡፡ በየዓመቱ የጥምቀት በዓል የሚከበረውም ይህን ምሥጢር ለመዘከርና ለመመስከር ነው፡፡

ጌታችን ያሳየውን ትሕትና እና ለእኛ አርአያ መኾኑን ለመመስከር፣ ለጥምቀት ኀይልን ለመስጠት እንደዚሁም ውኃን ለመቀደስ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀቱን በየዓመቱ ታከብራለች፡፡ በየዓመቱ ውኃ ዳር ሔዶ ማክበር በየዓመቱ መጠመቅ ተብሎ እንዳይተረጐምና ሰዎችን እንዳያሳስትም ታስተምራለች፡፡ ይህንኑ ትምህርት ለማስገንዘብም ‹‹የጠበሉን መረጨት አይተው በቀድሞ ዘመን ወደ አገራችን መጥተው የነበሩ ኢየሱሳውያን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ታጠምቃለች ብለው አጥላልተው ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ይህን የምትፈጽመው ጌታችን ለኛ ብሎ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከር፣ የጌታን በረከተ ጥምቀት ለምእመናን ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ምእመናን እየደመለሰች በየዓመቱ አታጠምቅም፤›› ሲሉ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጽፈዋል (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገጽ ፻፳፫)፡፡

የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዓት ከሌሎቹ በዓላት የተለየ ነው፡፡ ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው በበዓሉ ዋዜማ በሕዝብ ታጅበው ወደ ወንዝ ዳር ይወርዳሉ፡፡ በዚያ ዳስ ተጥሎ፣ ከተራም ተከትሮ ሌሊቱን መዘምራኑ በማኅሌት ካህናቱ በሰዓታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡ ይህም ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሔዱ ምሳሌ ነው፡፡ ሲነጋም ጸሎተ ቅዳሴው ተጠናቅቆ ወደ ወንዙ በመሔድ ጸሎተ አኮቴት ተደርሶ፣ ዐራቱ ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል፣ ወንዝም ሲሆን ሰዎች እየገቡ ሊጠመቁ ይችላሉ፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያንም፣ ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ዓባይ ወንዝ ወርደው በድምቀት ያከብሩት ነበር፡፡ ከዐረቦች መግባት በኋላ ግን ከሊፋዎቹ (ሡልጣኖቹ) ስለከለከሏቸው በቤተ ክርስቲያን ብቻ ለማክበር ተገድደዋል (The Coptic encyclopedia P.1103)፡፡

ከበዓለ መስቀል እና በዓለ ጥምቀት በተጨማሪ ‹‹አሸንዳ›› (‹‹አሸንድዬ››) በመባል የሚታወቀውና በሰሜን ኢትዮጵያ የሚከበረው የዐደባባይ በዓልም ሙሉ በሙሉ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚከናወን በዓል ባይኾንም ሕዝቡ በአለባበሱ፣ በአዘማመሩና በሚያደርጋቸው ሌሎች ክዋኔዎች በዓሉ እንደ ሌሎች ሕዝባዊ ባህሎች አረማዊ ወግን ያልተከተለ መኾኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

የበዓላት ፋይዳ

በዓላት በቀዳሚነት የሚከበሩት መንፈሳዊ ዓላማ ይዘው ነው፡፡ ኾኖም በዓላት በሕዝብ የሚከበሩ እንደ መኾናቸው ሌሎች ጥቅሞችም አሏቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰው መሥራት ብቻ ሳይኾን ማረፍም አለበትና በዓላት ለማረፍና ለመዝናናት ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በዅሉም ሀገራት ያሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ግብይትን በማሳለጥና የገንዘብ ዝውውርን በማፋጠን ለአገር ኢኮኖሚ ማደግ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የመስኩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ሌላው የበዓላት ጥቅም ደግሞ ማኅበራዊ ግንኙነትን ማዳበር ነው፡፡ በበዓላት ሰዎች ይገናኛሉ፤ ስጦታዎችን ይለዋወጣሉ፤ ይገባበዛሉ፡፡ በዚህም ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ያዳብራሉ፡፡ በበዓላት ወቅት ችግረኞች ርዳታ ያገኛሉ፡፡

ከዚህም በላይ በዓላት ለባህል ግንባታ ለመልካም ዕሴት መፈጠር ምክንያት ኾነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ በዓላት የቱሪስት መስሕቦችም ናቸው፡፡ እንደ በዓለ መስቀል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኙ፣ እንደ ጥምቀት ብዙ ሕዝብን የሚያሳትፉ በዓላት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከመፍጠራቸውም ባሻገር የውጪ አገር ሰዎች ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው መጥተው እንዲጐበኙ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ በዚህም አገር የውጪ ምንዛሪ ታገኛለች፡፡ ከዅሉም በላይ በዓላት የአገርን ገጽታ ይገነባሉ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን በመሰለች ስሟ በድርቅና በረኀብ ለምትነሣ አገር በዓላት መጥፎ ገጽታንና ክፉ ስምን የሚቀይሩ ፍቱን መድኀኒቶች ናቸው፡፡

ስለ በዓላት አሉታዊ አስተሳሰቦች

የቤተ ክርስቲያን በዓላት የተጠቀሱትና ሌሎች ያልተጠቀሱ በርካታ ጥቅሞች እንዳሏቸው የታወቀ ቢኾንም አንዳንድ ወገኖች ግን በማወቅም ይኹን ባለማወቅ በዓላትን የሚዘልፉና የሚያንቋሽሹ ወይም የበዓላቱን ዓላማ የሚቃረኑ ሐሳቦችን ያዛምታሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከእነዚህ የተቃርኖ ሐሳቦች መካከል ጥቂቶቹን በመጥቀስና የሐሳቦቹን ድክመት በማሳየት ምላሽ እንሰጥባቸዋለን፤

ይቆየን