ማዘንና መጸለይ
በዲ/ን ታደለ ሲሳይ
የሰው ልጅ በመጀመሪያ ሲፈጠር ዓለምን ከፈጣሪ በታች እየመራ፣ ፍጡራን ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ነበር፡፡ አዳም በተፈጠረ ጊዜም ጣርና ሐዘን፣ መከራና ስቃይ አልነበረበትም፤ ይልቁንም በድሎትና በደስታ ይኖር ነበር እንጂ፡፡ ይሁን እንጂ አድርግ የተባለውን ብቻ ማድረግ ሲኖርበት አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ የሞት ሞት አገኘው፡፡ አዳምና ሔዋን ስቃይና እንግልት፣ ፈተና፣ ሐዘንና መከራ ደረሰባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው የሰው ልጅ ኑሮው በችግርና በድሎት፣ በስደትና በመረጋጋት፣ በሐዘንና በደስታ፣ በማሸነፍና በመሸነፍ፣ በመርታትና በመረታት መካከል ሆነ፡፡ የሰው ልጅ ሕይወትም መውደቅና መነሣት፣ ማግኘትና ማጣት፣ መከፋትና መደሰት፣ ማዘንና መረጋጋት ልማዱ ሆነ፡፡
