ወርኀ ጳጉሜን
ከመምህር ተስፋማርያም ክንዴ
ወርኀ ጳጉሜን
ጳጕሜን የሚለው ቃል ኢፓጎሜን(epagomene) ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም የተረፉ ትርፍ ቀናት ማለት ነው። ከምን የተረፈች ካልን ዘመኑ በዓመት ዓመቱ በወራት ወራቱ በሳምንት ሳምንቱ በቀናት ቀናቱ በኬክሮስ ኬክሮሱ በካልዒት ካልዒቱ በሣልሲት ሣልሲቱ በራብዒት ራብዒቱ በሐምሲት ሐምሲቱ በሣድሲት ሲለካ ከዓመታቱ የተረፈች ማለት ናት። የተረፈችውን የቁጥር ሊቃውንት ከኬክሮስ ባነሱ በካልዒት በሣልሲት በራብዒት በሐምሲትና በሳድሲት ቀምረው ሰፍረው አምስት ዕለት ከ፲፭ኬክሮስ አድርገው ይህችንም ጳጕሜን ብለዋታል። ከዚህም ፲፭ ኬክሮስ በአራት ዓመት አንዴ በዘመነ ሉቃስ መጨረሻ በዘመነ ዮሐንስ መጀመሪያ ጳጕሜን ስድስት የሚያደርጋት ነው።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ጳጉሜንን እንዲህ ይተረጕሟታል፤ ጳጉሜን ማለት ጭማሪ ተውሳክ፣ አምስት ቀን፣ ከሩብ፣ ከዐውደ ወር ተርፎ በዓመቱ መጨረሻ የተጨመረ ስለሆነ ትርፍ ተጨማሪ ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ ፱፻፭)
እንዲሁም ጳጉሜን ማለት በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ፀሐይ ከገባች በኋላና ከመውጣቷ በፊት ለተወሰነ ሰዓት የምታበራው ጎህ ብርሃን ማለት ነው።“ይህም የብርሃን መጠን ምን ያህል ነው?” ከተባለ በቀን ፀሐይ ከመግባቷ በፊት ፳፮ ካልኢት ፲፭ ሣልሲት ፴ ራብዒት ከገባች በኋላም እንዲሁ ፳፮ ካልኢት ፲፭ ሳልሲት ፴ ራብዒት ሆኖ በድምሩ በቀን ፀሐይ ከመውጣቷና ከገባች በኋላ ያለው የብርሃን መጠን ፶፪ ካልዒት ከ፴፩ ሣልሲት ይሆናል። ጳጒሜን ማለት ይህ ፀሐይ ከመውጣቷ በፊትና ከገባች በኋላ ያለው ብርሃን ነው።ይህንም የዘመን አቆጣጠርን የሚያጠኑ ሊቃውንት በአንድ ላይ እየሰበሰቡ ሲያሰሉት በዓመት ፭ቀን በ፬ኛው ዓመት አንዴ ደግሞ ፮ኛዋ የጳጉሜን ዕለት ይሰጣል።
ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም ኢትዮጵያን የመሰሉ ለምሳሌ እንደ ግብፅና ኤርትራን የመሳሰሉ ሀገራት ብቸኛ የባለ ፲፫ ወር ባለጸጋ መባላቸው ግን ዕለቷ በሌሎች አልኖር ብላ ሳይሆን ሌሎች እንዲሁ በዘፈቀደ ከሌላው ወር ጋር ደርበው ሲያከብሯት ኢትዮጵያና መሰል ሀገራት ግን ከላይ ከኬክሮስ እስከ ሳድሲት ባሉት ጥቃቅን የጊዜ መስፈሪያዎች ሰፍረን ቀምረን ስለምናውላት ነው። ሌሎች ግን እንዲሁ በዘፈቀደ ከወራቸው ጨምረው ያውሏታል ለምሳሌ ምዕራባውያንን ብንወስድ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፵፮ ዓ.ዓ ጁልየስ ቄሳር በቀመረው የጁሊያን አቆጣጠር ላይ ዐራቱን ወር ፴፩ ዕለት የቀሩት ፯ቱን ፴ አንዷን የካቲት ወይም እነሱ አሽባጥ የሚሏትን በሦስቱ ዓመት ፳፰ በ፬ኛው ዓመት ፳፱ አድርገው ያከብሯታል።
የአምስተኛዋ ጳጉሜን ተግባር
አምስተኛዋ ጳጉሜን “ዕለተ ምርያ ወይም ”የተመረጠች ቀን” አንድም ዕለት ኅሪት ዕለተ መድኃኒት ትባላለች (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት፣ ፲፱፻፵፰፣ ገጽ ፮፻፰) ዕለተ ምርያ ይህን ስያሜ ካገኘችበት ምክንያት አንዱ የጌታችን ልደት የምታሳውቅ በመሆኗ ነው። የጌታ ልደት ምን ጊዜም ቢሆን ይህች ቀን የዋለችበትን ዕለት አይለቅም። ይህም በመሆኑ በ፬ኛው ዓመት አንዴ የጌታ ልደት በ፳፰ ይውላል ወይስ በ፳፱ የሚለውንም ለማወቅ ይህችው ዕለት የዋለችበትን ዕለት ይዘን ብንቆጥር ታኅሣሥ ፳፰ የጌታ ልደት ሆኖ ስለምናገኘው ነው። ከዚህም የተነሣ አንዳንዴም ሱባዔ ልደት እየተባለች ትጠራለች።
በስድስተኛዋ ጳጉሜን ወይም በዘመነ ሉቃስ ሌሎች በዓላት ከዘመን መለወጫ ጀምሮ አንድ አንድ ቀን ወደፊት ሲገፉ ልደት ደግሞ ይባስ ብሎ አንድ ቀን ወደኋላ ተስቦ የሚከበርበት ምክንያት ለኢትዮጵያውያን የዘመን መነሻችን የጌታ ልደት ስለሆነ ነው። ለልደት ደግሞ ጥንቱ ፅንሰት ነው፤ የጌታ ፅንስ መጋቢት ፳፱ ቀን ነው። ከዚህ ጀምረን (፪፻፸፭) ቀን ፱ ወር ከ፭ ቀን የሚፈጸምበት በሦስት ዓመት በ፳፱ ሆኖ በ፬ኛው ዓመት ጳጉሜን ስድስት በምትሆንበት በዘመነ ዮሐንስ ከፅንሰቱ ጀምሮ ፱ ወር ከአምስት ቀን ለመጠበቅ ሁልጊዜ የጌታን ልደት ፳፰ ይከበራል፡፡
ይህንም ከድሜጥሮስ በኋላ የተነሡ ፫፻፲፰ ሊቃውንት አባቶቻችን ተስማምተውበት እስከ አሁን ሲያከብሩት መጥተዋል፡፡ እኛም ከእነርሱ ሃይማኖት ስለማንወጣ እስከ አሁንም እያከበርን ነው፤ ወደፊትም እናከብራለን። በሌሎች ሀገራት ዘንድ ግን የልደት በዓል እንደኛ በሦስቱ ዓመት ፳፱ በ፬ኛው አንዴ በ፳፰ እንደምናከብረው ከፍና ዝቅ የማይልበት ምክንያቱ ምንድን ነው ካልን ዕለተ ሠግርን(አዕዋዲትን)ማለት ፮ኛዋን ጳጒሜ እንደፈለጉ በ፬ኛው ዓመት ከአሽባጥ(የካቲት) ላይ ጨምረው ስለሚያውሏት ነው።(አቡሻክር ገጽ ፰፻፸) «ቀዳሚ በዓል ዘውእቱ ዕለተ ልደቱ ለክርስቶስ አመዕሥራ ወሐሙሱ ለታስዕ ወርኅ በኁልቆ ዕብራውያን ወበሐሳበ ግብጻውያን አመ ዕሥራ ወተስዑ ለወርኀ ታኅሣሥ ዘውእቱ ራብዓይ ወርኅ ግበሩ፤ የመጀመሪያው በዓል የክርስቶስ ልደት ነው፡፡ ይኸውም በዕብራውያን አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር በ፳፭ኛ ቀን በግብጻውያንና በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በታኅሣሥ ወር በ፳፱ኛው ቀን ታደርጋላችሁ ተብሎ ተወስኗል። (ዲድ፣ አንቀጽ ፳፱፣ ገጽ ፴፯)
ስድስተኛዋ ጳጕሜን
ስድስተኛዋ ጳጕሜን ሠግረ ዮሐንስ (ዮሐንስ ሳይውልባት የምታልፍ ዕለት) ትባላለች ይህችንም ዕለት ወንጌላውያን ተከፋፍለው ይመግቧታል እንጂ እንደ አምስተኛዋ ዕለት ለዐራቱም ወንጌላዊያን ሙሉ ሆና ስለማትደርስና ከሱባዔ ገብታ ስለማትቆጠር ነቢዩ ሄኖክም አልቆጠራትም።(ኩፋ ፯፥፴)
ጳጒሜን ጭማሪነቷ ለዘመን ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ሠራተኛውም ያለደመወዝ ጨምሮ የሚሠራት ዕለት ናት፤ በኢትዮጵያ በቀን ሠርቶ የዕለቱን ከሚያገኝ ሠራተኛ በቀር ደመወዝ የማይከፈልባት ዕለት ናት፤ ደመወዝም ብቻ ሳይሆን ቤት የሚከራዩ ሰዎችም በጭማሬ የሚኖሩባት ዕለት ናት እንጂ መስከረም ላይ የቤት ኪራይ ሲከፍሉ የጳጒሜን ጨምራችሁ ክፈሉ አይባሉም። ይህ ጳጒሜን ልዩ ያደርጋታል። ከዚህም በተጨማሪ በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊያን በጸበል ያሳልፏታል፤ “ስለምን ነው?” ቢሉ በዚህን ዕለት ውኃው ሁሉ የሚባረክበት ነው፤ ይህም ብቻ ሳይሆን እህልንም የወር ያክል እንደምታሳድግ ገበሬዎች ሳይቀር ይመሰክሩላታል። ርኅወተ ሰማይም የሚከበረው በዚሁ በጳጕሜን ዕለት ነው።
ኢትዮጵያውያን ጳጕሜን እንደሌሎች ሀገራት ከወራቸው ደርበው ቢያከብሯት ምን ችግር ይፈጥራል?
መጀመሪያ ሃይማኖታዊ ችግሮችን ነው። ኢትዮጵያ አሁን ኃያላን ነን የሚሉት ሀገራት ሳይኖሩ የራሷን የዘመን አቆጣጠር የራሷን ታሪክ ባህልና ሃይማኖት ይዛ የቆየች ሀገር ናት። ስንኳንስ ምዕራባውያን በቅርብ የመጡት ቀርቶ ለቀደምት እስራኤላውያን እንኳን እግዚአብሔር ማስተማሪያ ያደረጋት ኢትዮጵያ መሆኗን መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። እናንተ እስራኤላውያን ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ሰዎች አይደላችሁምን እንዲል። (አሞ.፱፥፯)
ስለሆነም በራሷ የዘመን አቆጣጠር መሠረት አጽዋማትን አውጥታ ከመጾም አልፋ በዓላትንም በየዕለቱ ታከብራለች። ከእነዚህ በዓላት መካከል ዕለተ ምጽአትንና ርኅወተ ሰማይን በጳጕሜን ወር ታከብራለች። ዕለተ ምጽአት በዋናነት በዓመት ሦስት ጊዜ ይታሰባል፤ የመጀመሪያው በዐቢይ ጾም እኩሌታ የደብረ ዘይት ሲሆን ፪ኛው ደግሞ በዚሁ ፲፫ኛ ወር ብለን በምናከብረው በጳጉሜን ወር ነው፡፡ ሌላው ሦስተኛው በኅዳር ወር መጨረሻ ቅድመ በዓለ ስብከት ነው።
እንግዲህ ሦስት ጊዜ ማሰባችን ጌታ ሦስት ጊዜ የሚመጣ ሆኖ ሳይሆን መታሰቢያ ነው፡፡ በጎላውና በዐዋጅ የሚከበርበትን መሠረት ስናደርግ በዓመት ሦስት ጊዜም ብቻ ተባለ እንጂ ሰው ሁልጊዜ ከኃጢአት ተከልክሎ ዕለተ ሞቱንና ዕለተ ምጽአትን ማክበር እንዳለበት ለሁሉም ኦርቶዶክሳውያን ግልጽ ነው። በዚህ ቀን ዕለተ ምጽአትን ስናስብ ክረምቱን በጨለማ መስለን አዲሱን ዓመት ደግሞ በቀን መስለን ከጨለማ ወደ ብርሃን ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዓመት ያሸጋገርከን ብለን ጳጕሜን መሸጋገሪያ አድርገን እናከብራታለን። ዕለተ ምጽአትን እንድናስብ ደግሞ ጌታ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬ እና ፳፭ አስተምሮናል ስለዚህ ጳጕሜን ከሌላው ወር ተደርባ ትዋል ካልን ዕለተ ምጽአትን እንዳናስብ ይሆናል ማለት ነው።
ሁለተኛው ርኅወተ ሰማይ (የሰማይ መከፈት) የሚከበረው በዚሁ ወር በጳጕሜን ፫ ነው። ርኅወተ ሰማይ (የሰማይ መከፈት) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮ ሳይሆን ያልታየ ምሥጢር የሚታይበት ስለሆነ ነው። በኖኅ ዘመን ሰማይ እንደተከፈተና የጥፋት ውኃ እንደዘነበ እናስታውሳለን፤ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታ ሲጠመቅ አሁንም ለምሕረት ሰማይ እንደተከፈተ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይነግረናል “ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ሶቤሃ ወፅአ እማይ ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ፤ ጌታ ተጠምቆ ያን ጊዜ ከውኃው ወጣ፤ እነሆ ሰማይ ተከፈተ” ይልና ይህን ተርጕሞ የሰማይን መከፈት ሲያትት “አሁን በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም፤ የተዘጋ ቤት በተከፈተ ጊዜ በውስጥ ያለ ዕቃ እንዲታይ ያልታወቀ ምሥጢር ተገለጸ ሲል ነው” ይላል፡፡ (ማቴ. ፫፥፲፮ ትርጓሜ) ይህም የሚሆነው ዕለቱ የመጀመሪያው በጳጕሜን ሦስት ቀን ነው። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን የመጀመሪያውን ርኅወተ ሰማይ የምታከብረው በዚሁ ወር ጳጉሜን ሦስት ቀን ነው።
በዚህ ቀን ጸሎት የሚያርግበት የበሽታ ፈውስ ለማግኘት ጸበል የሚጠጣበት ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከት የሚገኝበት ዕለት ነው ተብሎ ስለሚታመን ምእመናን ሰብሰብ ብለው ጸሎት የሚያደርሱበት ዕለት ስለሆነ ነው። ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር በሌላው ቀን ጸሎት አይቀበልም ማለት አይደለም።
ሦስተኛው በጨረቃ ዑደት ላይ የሚፈጠር ችግር ነው። ፀሐይም ጨረቃም የራሳቸው ዑደት እንዳላቸው ይታወቃል እንደ አጠቃላይ ፀሐይና ጨረቃ ዑደታቸውን በመስከረም አንድ ሲጀምሩ ጨረቃ በነሐሴ ፳፬ ፀሐይ ደግሞ በጳጉሜን ፭ የዓመት ጉዟቸውን ይጨርሳሉ ለይተን የዘንድሮውን ማለትም የ፳፻፲፰ ዓ.ም የጨረቃን ጉዞ ስናይ ደግሞ ጨረቃ የነሐሴ ወር ጉዞዋን ነሐሴ ፯ ቀን ትጨርሳለች የመስከረም ጨረቃ ነሐሴ ፰ ቀን ፳፻፲፰ዓ.ም ተወልዳለች የመስከረም ጨረቃ ፳፱ ቀን ስለሆነ ከነሐሴ ፳፪ እንይዛለን ጳጉሜን ፭ ሲደመር ፳፯ ይሆናል ይህን ፳፱ ለማድረግ ከመስከረም ፪ ስናመጣ የመስከረም ወር ጨረቃ መስከረም ፪ ያበቃና የጥቅምት ጨረቃ መስከረም ፫ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም ትወለዳለች። እንዲህ እያለ ዑደቱ የሚቀጥል ሲሆን የጳጉሜን ዕለት ከሌላው ጋር እንደርብ ብንል ግን የአንዱ ወር ጨረቃ ከአንዱ ወር ጋር የተደባለቀ ይሆንብናል።
እንዳጠቃለይ ሀገራችን ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን መቁጠርያ ቀመር ያላት፣ ፲፫ ወራት ፩ ዓመት ብላ በመቁጠር የ፫፻፷፭ ቀን በፀሐይ (solar calendar) ፫፻፶፬ የጨረቃ መቁጠርያ (lunar calendar) በ፲፪ ወራት ክፍፍል ከ፴ ቀናት ሲያልፍ ጳጉሜን ፲፫ኛ ወር አድርጋ በመጠቀም ልዩ ሆና ትታያለች።
ወርኀ ጳጉሜን በትውፊት እንደሚነገረው ፴ ቀናት ካሏቸው ወራት እኩል አዝርዕት የሚያድጉባት “የበረከት ወር” በመባል ትጠራለች፤ በዚህም የተነሣ ባለቅኔው “ይብል ጳጉሜን በቃለ ጳጉሜን መርህ፣ ሐፂር ቆምየ ወልቡናየ ነዊኅ፣ መምህር ጳጉሜን ቁመቴ አጭር ቢሆንም ልቤ ግን ረጅም ነው አለ” በማለት የወርኀ ጳጕሜን ትሩፋት ብዙ እንደሆነ አመሥጥረውታል። የዓመቱ ጸሎት የሚያርግበት መሆኑን ይታመናል፤ ይህንን በመረዳት ምእመናን ሱባዔ ይዙበታል፤ የፈቃድ ጾም ይጾሙበታል፤ ጸበል ይጸበሉበታል። የዳግም ምጽአት መታሰቢያ እንደመሆኑ በዚህ ቅዱስ ተግባር መጠንከር ይገባናል።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!