ማዘንና መጸለይ

በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

የሰው ልጅ በመጀመሪያ ሲፈጠር ዓለምን ከፈጣሪ በታች እየመራ፣ ፍጡራን ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ነበር፡፡ አዳም በተፈጠረ ጊዜም ጣርና ሐዘን፣ መከራና ስቃይ አልነበረበትም፤ ይልቁንም በድሎትና በደስታ ይኖር ነበር እንጂ፡፡ ይሁን እንጂ አድርግ የተባለውን ብቻ ማድረግ ሲኖርበት አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ የሞት ሞት አገኘው፡፡ አዳምና ሔዋን ስቃይና እንግልት፣ ፈተና፣ ሐዘንና መከራ ደረሰባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው የሰው ልጅ ኑሮው በችግርና በድሎት፣ በስደትና በመረጋጋት፣ በሐዘንና በደስታ፣ በማሸነፍና በመሸነፍ፣ በመርታትና በመረታት መካከል ሆነ፡፡ የሰው ልጅ ሕይወትም መውደቅና መነሣት፣ ማግኘትና ማጣት፣ መከፋትና መደሰት፣ ማዘንና መረጋጋት ልማዱ ሆነ፡፡

ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ጠቢቡ ሰሎሞን፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ደስታ አለው፤ የሚከፋበትም ጊዜ አለው፡፡ የራሱ የሆነ ችግር አለው፤ ደስተኛ የሚሆንበትም ወቅት አለው፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ ሰዎች ማዘን ባለባቸው ሰዓት ከማዘን ይልቅ ማዘን በሌለባቸው ሰዓት ሲያዝኑ ይስተዋላሉ፡፡ ይህም የምኞት ፈረስ ከመጋለብ የሚመጣ ነው፡፡ በሥጋዊ ሕይወቱ መንፈሳዊ ኑሮን የሚኖር ሰው ጎመን በልቶ ፈጣሪውን ያመሰግናል፤ ምኞትን ብቻ የጸነሰ ግን ሥጋ እየበላ፣ ወይን እየጠጣ መርካት ይሳነዋል፡፡ እግዚአብሔርን ለሕይወቱ መሠረት ያደረገ ሰው ጎዳና ላይ ማደሩ ደስታውን አይነፍገውም፤ እግዚአብሔርን የረሳ ሰው ደግሞ ባማረ ቪላ ቤት እየኖረ ፎቅ ካልሠራሁ ብሎ ፈጣሪውን ያማርረዋል፡፡

በመንፈሳዊ ኑሮ ያለ ሰው የነፍሱ እርካታ እንጂ የሥጋው ጉስቁልና አያስጨነቀውም፤ በተቃራኒው የቆመ ሰው ግን እየበላ ያለቅሳል፤ እየለበሰ ይበርደዋል፤ በቤተ መንግሥት መኖር ቢችል እንኳን ጎዳና ላይ የወደቀ ያህል ይሰማዋል፡፡ በዚህም ከመጨነቁና ከማዘኑ የተነሣ ፈጣሪውን ያማርራል፤ ያላየሁትን ልይ ያልጨበጥኩትን ልጨብጥ ይላል፡፡ ለመጨበጥ እጁን ሲዘረጋ ያሻውን ባያገኝ ሰው መሆኑን ይጠላል፡፡

በመሆኑም እግዚአብሔርን ረዳት ሳናደርግ በምኖረው ሕይወት ማዘንና ማልቀስ ክርስቲያናዊ አይሆንም፤ ይልቁንም በተፈቀደልን ነገር ማዘንና ላዘንበት ነገርም መፍትሔ ይመጣ ዘንድ መጸለይ እንጂ፡፡ ለመሆኑ የሰው ልጅ ማዘንና ማልቀስ ያለበት መቼ ነው? ቢባል፤

  1. እግዚአብሔር ትእዛዝ ተላልፎ ኃጢአት ሲሠራ

አዳምና ሔዋን በገነት ሲኖሩ ደስተኞች ነበሩ፤ ነገር ግን በሰይጣን አታላይነት ትእዛዙን ሲተላለፉ በደረሰባቸው ከክብር መዋረድ የተነሣ አዝነዋል፤ አልቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማዘናቸውን የተመለከተና እስከመጨረሻው ወድቀው ይቀሩ ዘንድ ያልፈቀደ እግዚአብሔር በገባላቸው ቃል መሠረት መጸጸታቸውን አይቶ አዳናቸው፡፡ ከሞት ወደ ሕይወትም ተመለሱ፡፡

የሰው ልጅ ማዘን ያለበት በዚህ ሰዓት ነው፡፡ በሕይወት እንቅስቃሴው ሁልጊዜም ቢሆን ኃጢአት ሊሠራ ይችላል፡፡ ኃጢአት ሳይሠራ የሚኖር ማንም የለም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍም ይህንን ያረጋግጥልናል፡፡ አንድስ እንኳ ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለም፤ ምክንያቱም ውሎና አዳራችን እንዲሁም ኑሯችን ኃጢአት በከከባት፣ የምድራዊ ተድላ ደስታ ወጀብ በሚያናውጣት ዓለም ነውና የምንኖረው፡፡

በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው ኃጢአት ሲሠራ ቶሎ ብሎ በሠራው ኃጢአት በመጸጸትና በማዘን ወደ ንስሓ መቅረብ አለበት፡፡ ኃጢአት ሠርተን የምናዝነው ሐዘን ወደ ንስሓ በር ለመግባት ትልቅ በር ከፋች ስለሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ለእኛ ብሎ የሞተውንና በመቃብር አድሮ የተነሣውን የፍቅር አምላክ  ረስተን በሥጋዊ ነገር ተታለናልና ሐዘን ይገባናል፤ ከሰማያዊ መንግሥት ይልቅ ምድራዊ ፈተና አሸንፎናልና ሐዘን ይገባናል፡፡ በዚህ ጊዜ አልቅሶ ማረኝ ማለትና የቆሸሸን ሕይወት በንስሓ ሳሙና መታጠብ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

  1. ወዳጆቻችን በሞት በተለዩን ጊዜ

በእኛ ሀገር ባህልም ሆነ በሌሎች በርካታ ሀገራት የሰው ልጅ በሥጋ ሲሞት አልቅሶና አዝኖ መሸኘት የተለመደ ነው፡፡ ማዘኑና ማልቀሱም ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በሕይወት አብሮን የነበረ ሰው፣ በክፉው በደጉ ሁኔታዎችን አብሮ ያሳለፈ ሰው በድንገት በሞት ከመካከላችን ሲለይ ማዘኑና ማልቀሱ ተገቢም፣ ክርስቲያናዊም ነው፡፡ ነገር ግን ሐዘንና ልቅሶን ከአቅም በላይ እንድናበዛ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አታስተምርም፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ሰው ሲሞት የሚለቀሰው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም በመጀመሪያ የሟቹ ነፍስና ሥጋ ሲለያዩ፣ ሁለተኛ አስከሬኑ ከኖረበት ቤት ወጥቶ ወደ መካነ መቃብር ሲጓዝ፣ ሦስተኛ ደግሞ የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ሲፈጸም ነው፡፡

በእነዚህ በሦስቱ ሰዓት ማንኛውም ክርስቲያን ለሟች ወገኖቹ እንዲያዝንና እንዲያለቅስ ተፈቅዷል፡፡ ከዚህ ውጭ ባለው ግን እግዚአብሔር አምላክ የሟቹን ነፍስ በክብር እንዲያሳርፋት መጸለይና ማሰብ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከናወነው ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረስ ማድረግ እንጂ ፊትን በመንጨትና አመድ በመነስነስ እንድናዝን አልተፈቀደም፡፡

  1. 3. ሰዎች ከእግዚአብሔር መንገድ ባፈነገጡ ጊዜ

ክርስቲያን በክርስትና ሕይወት ሲኖር መኖር ያለበት ለራሱ ብቻ አይደለም፤ የሚያስበውም ለራሱ ጥቅምና ጉዳት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ክርስትና ከራስ አልፎ ለሌላውም መኖር ነው፤ ክርስትና ለሚያውቁትም ለማያውቁትም መጸለይ ነው፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለው ብሂል ክርስቲያናዊ ለሆነ ማኅበራዊ ኑሮ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም አባቶቻችን በእነርሱ መከራ ለሌሎች ሠርዶ እያበቀሉ እንጂ በዘመናቸው የነበረውን ሰርዶ ብቻ ተጠቅመው አላለፉምና፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ ታላቅ አብነት ይሆነናል፡፡

አምላክ ሲሆን ሰው ሆኖ፣ ከአዳም የልጅ ልጅ ተወልዶ፣ ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ሥራ እየፈጸመ ያደገው፣ በመጨረሻም መከራ መስቀሉን ተቀብሎ ደሙን ያፈሰሰው፣ ሥጋውን የቆረሰው ለራሱ ብሎ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሰው ልጅ ከተራቆተበት ድኅነት ይመለስ ዘንድ በማይመረመር ፍቅሩ ነው እንጂ፡፡

በመሆኑም የሌሎች ከእግዚአብሔር መንገድ ማፈንገጥና መውጣት ሊያሳዝነን ይገባል፤ ልንጸልይላቸው፣ ልናለቅስላቸው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ከድኅነት ወደ ሞት፣ ከሰላም ወደ መከራ፣ ከተድላ ወደ  ጉስቁልና አምርተዋልና፡፡ የሰው ልጅ ዘላለማዊ ሞት ሲሞት ከማዘን በላይ ሌላ ሐዘን የለም፤ ሰዎች በነፍሳቸው ሲጎዱ አይቶ ከማልቀስ በላይ ሌላ ልቅሶ የለም፡፡ በመሆኑም የምናውቃቸው ሰዎች ከክርስትና ሕይወት ባፈነገጡ ቍጥር መምከርና ከምክሩም  አፈንግጠው ወደ ተሳሳተ መንገድ ሲያመሩ ልናዝንላቸው፣ ልንጸልይላቸው ይጋባናል፡፡

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *