ቅዱስዮሐንስ
ከመምህር ተስፋማርያም ክንዴ
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን መካከል የነበረ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት ያበሠረ እና መንገዱን የቀየሰ ታላቅ ሐዋርያ፣ ካህን እና ነቢይ ነው።
መጽሐፍ ከእመቤታችን ጀምሮ ስለቅዱሳን ሲናገር የእገሌ ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚወዱ ደጎች ነበሩ እንደሚል ሁሉ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ወላጆችም ደግነት ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ በማለት ይመሰክራል።«በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ከአሮን ነገድ ነበረች። ወክልኤሆሙ ጻድቃን እሙንቱ በቅድመ እግዚአብሔር፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁለቱም ደጎች ነበሩ። ወንጹሓን እሙንቱ፣ ያለነውርና ያለ ነቀፋም የኖሩ ነበሩ” ይላል። (ሉቃ. ፩፥፭-፮)
ሰው እግዚአብሔር እስከሚመሰክርለት ድረስ ጻድቅ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ብለን በሐሳባችን ለምናወጣና ለምናወርድ ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “ዘቦቱ ትእዛዝየ ወየአቅቦ ውእቱ ዘያፈቅረኒ፣ ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው። ወለዘአፍቀረኒ ያፈቅሮ አቡየ፣ እኔን የወደደኝን አባቴ ይወደዋል፤ ወአነሂ አፈቅሮ፤ እኔም እወደዋለሁ፤ እራሴን እገልጽለታለሁ። እኔ በእርሱ እኖራለሁ፤ እሱም በእኔ ይኖራል” በማለት ይገልጻል። (ዮሐ. ፲፬፥፲፪)
በጽድቅ መንገድ የተጋዙት ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ጸሎታቸው እንዴት ፈጥኖ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚሰማ ሲነግረን ወንጌላዊው “ወይቤሎ መልአክ ኢትፍራህ ዘካርያስ እስመ ናሁ ተሰምዐ ጸሎትከ በቅድመ እግዚአብሔር ወብእሲትከኒ ኤልሳቤጥ ትወልድ ለከ ወልደ ወትሰምዮ ስሞ ዮሐንስ ወይከውነከ ትፍሥሕተ ወሐሤተ፣ ወብዙኀን ይትፌሥሑ በልደቱ፤ መልአክም ዘካርያስ ሆይ አትፍራ አለው፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቷልና፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ልጅ ትወልድልሀለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ፤ ፍጹም ደስታ ይሆንልሀል፤ ብዙዎች በልደቱ ይደሰታሉ” በማለት የመሰከረው ቅዱስ ገብርኤል ነው። (ሉቃ. ፩፥፲፫-፲፬)
የመልክአ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ደራሲ ደግሞ ስለ ክብሩ ሲናገር እንዲህ ይላል። “ሰላም ለፅንሰትከ እንበለ ኀጢአት ወግማኔ፣ ወለልደትከ ሰላም አመ ፴ሁ ለሰኔ፣ ዮሐንስ ዘኮንከ ደመና ሰማይ ኮናኔ፣ አዝንም መና አእምሮ ወኅብስተ ሕይወት መድኀኔ ኀበ ውስተ ልብየ ኀብሩ ወገብሩ ኩርጓኔ፤ ያለ ኃጢአትና ያለርኩሰት በቅድስና ሕግ ለተፈጸመ ፅንሰትህ እና በወርኀ ሰኔ በ፴ኛው ዕለት ለሚከበር ልደትህ ሰላምታ ይገባል።የሰማይ ደመናን ታዝዝ ዘንድ ሥልጣን የተሰጠህ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሆይ! በልቤ ውስጥ ተሰብስበው በአንድነት ወደተከማቹት ሕዋሳቶቼ የጥበብ እንጀራንና ሰማያዊ መናን አዝንምልኝ” በማለት ያወድሰዋል።
“አማን እብለክሙ ኢተነሥአ እምትውልደ አንስት ዘየዐቢ እምዮሐንስ መጥምቅ፤ ሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከዮሐንስ መጥምቅ የሚበልጥ አልተነሣም ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ” ብሎ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የመሰከረለት ራሱ ክርስቶስ ነው። (ማቴ. ፲፩፥፲፩)
ቅዱስ ዮሐንስ በእግዚአብሔር ዘንድ ደግ የሆነና ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ የመላበት፣ ከዓለም ምቾት የራቀ ብዙዎች ወጣቶችን እያሳተ ካለው ከዓለም ፍትወት፣ ከሱስና ከአልባሌ ነገሮች ራሱን ጠብቆ በንጽሕና ብቻውን በበረሃ በምናኔ (በትሕርምት) በማደግ በሕይወቱ ለወጣቶችም፣ በበረሃ ለሚኖሩት መናንያን አርአያ የሆነ በትምህርት “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንሰሓ ግቡ” እያለ ከክርስቶስ መንፈቅ ተቀድሞ የክርስቶስን መንገድ የጠረገ ሐዋርያ ነው።
ለመምህራንም እንዲሁ ቅዱስ ዮሐንስ ኃያሉን ንጉሥ ሄሮድስን ሳይፈራ “የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም “ (ማር. ፮፥፲፰) በማለት ስለ እውነት መስክሯል። ይህም አሁን ላሉ መምህራን መምህር ወመገሥጽ በመሆን አርአያ የሆነ ሰማዕት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ታላቅ ክብርና ተሰሚነት እያለው ስለ ክርስቶስ ሲናገር እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል። ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የባሕርዩ የምድር ነው የምድሩን ይናገራል።” (ዮሐ. ፫፥፴-፴፩)ብሏል።
ቅዱስ ዮሐንስን ሕዝቡ ሁሉ እንደ መሲሕ ሲያዩትና ሲያከብሩት እርሱ ግን ራሱን ዝቅ አድርጎ “የጫማውን ጠፍር ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ነኝ” በማለት የክርስቶስን አምላክነት መስክሯል። ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ፣ ካህን፣ ሐዋርያ ሌሎችም ጸጋዎች የበዙለት ቅዱስ ነው።
- ነቢይነቱ:- ከእግዚአብሔር ተልኮ የወደፊቱን የተናገረ ብቻ ሳይሆን፣ ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ተነሥቶ የዘመኑን ሕዝብ ንስሓ እንዲገቡ ያስጠነቀቀና “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት መሢሑን በአካል እያመለከተ ያሳየ በመሆኑ ነው። እርሱ ከነቢያት ሁሉ በላይ “የነቢያት ማኅተም” ተብሎ ይጠራል፤ ምክንያቱም የነቢያትን ትንቢት በተግባር ፈጽሟልና።
- ካህንነቱ:- ከአባቱ ከዘካርያስ ወገን (ከአሮን ቤተሰብ) የተገኘ በመሆኑ ከካህናት ወገን ነው።
- ሐዋርያነቱ: “ሐዋርያ” ማለት የተላከ ማለት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ከእግዚአብሔር ተልኮ የብርሃን ምስክር የሆነ ነው።(ዮሐ.፩፥፮)
የኢትዮጵያ ዐውደ ዓመት በቅዱስ ዮሐንስ ስም ይጠራል፤ በዚህ ስም ሊጠራ የቻለበት ምክንያት ደግሞ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ምትረተ ርእሱ መስከረም ሁለት ቀን ስለሚውል እርሱን ለማስታወስ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሏል። በሌላ በኩልም “ቅዱስ ዮሐንስ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስድስት ወር ቀድሞ ‘ንስሓ ግቡ’ እያለ የጌታን መምጣት ያበሠረ፣ የጨለማውን የብሉይ ኪዳንን ዘመን አሳልፎ ለሐዲሱ ኪዳን ድልድይ እንደሆነ፣ ይህም በዓል ክረምት ጨለማው አልፎ በጋውን አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት ስለሆነም ነው።
በሌሊቱ መጨረሻ ጎሕ ቀደደ እንደሚባለው ዮሐንስም ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ መጥምቅ በጨለማው ዘመነ ብሉይ መጨረሻ “ከእኔ በፊት የነበረው ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ አይገባኝም፤ እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን እርሱ በመጣ ጊዜ በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” በማለት ሰብኳል።(ዮሐ. ፩፥፲፭፣ ማቴ. ፫፥፪)
ይህም በዓል ርእሰ ዐውደ ዓመት እየተባለ ይጠራል። ርእሰ ዐውደ ዓመት የተባለበትም ምክንያት መስከረም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ወር ስለሆነ ይህም በዓል በመጀመሪያው ወር ከሁሉም ቀድሞ የሚውል በመሆኑና የአጽዋማትና በዓላት ሁሉ ርእስ ስለሆነ እሱን መሠረት አድርገው ሌሎች የዓመቱ በዓላትና አጽዋማት የሚወጡበት በመሆኑ ነው። በሌላም በኩል ይህ በዓል ዐውደ ዓመት መባሉ ፀሐይና ጨረቃ የዓመት ዑደታቸውን ጨርሰው በመስከረም ወር እንደገና ስለሚጀምሩ ነው።
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) ጥናት መሠረት መስከረም ፩ ቀን (ርእሰ ዐውደ ዓመት) «ወላዴ መጥቅዕ ወዐበቅቴ» ተብሎም ይጠራል። በዚህ ስም ሊጠራ የቻለበት ምክንያት በሒሳባዊ ስሌት ውስጥ ያሉት ሁለቱ መሠረታዊ የአጽዋማትና በዓላት ማውጫዎች (መጥቅዕ እና ዐበቅቴ) የሚገኙበትና አዲሱ ዑደት የሚጀምርበት ዕለት ስለሆነ ነው። ይህም ማለት በመስከረም ፩ ቀን የሚጀምረው የፀሐይ እና የጨረቃ የዘመን ዑደት ስሌት ለሚቀጥሉት በዓላትና አጽዋማት ማውጫ የሚሆኑትን መጥቅዕ (ጨረቃ ከፀሐይ የምትቀድምበትን ዕለት የሚያሳይ) እና ዐበቅቴ (የተረፈ ዘመን ወይም የጨረቃና የፀሐይ ቀናት ልዩነት) እንዲወለዱ (እንዲገኙ) ምክንያት ስለሆነ ነው።
በመሆኑም መስከረም ፩ (ቅዱስ ዮሐንስ) “ወላዴ መጥቅዕ ወዐበቅቴ የመጥቅዕንና ዐበቅቴን ወላጅ/አስገኚ» ተብሎ ይጠራል። በዓሉን አክብረን ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ለመሳተፍ ያብቃን። አምላከ ቅዱስ ዮሐንስ ዘመኑን የሰላም፣ የበረከት ዘመን እንዲያደርግልን መልካም ፈቃዱ ይሁንልን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!