ጠንካራ ማንነት

…በዳዊት አብርሃም…

በዓለም ስትኖር ብዙ ሓላፊነቶችን ለመወጣት አለብህ። በዓለም መኖር ዓለማዊ መሆን አይደለም። ከኀጢአት ርቆ ዓላማን በማሳካት ምድራዊና መንፈሳዊ ሕይወትን አስተባብሮ መኖር ነው እንጂ። አንድ ሰው ጠንካራ ማንነትን ገንብቷል የሚባለው ምድራዊውንና ሰማያዊውን ዓለም አስታርቆ መኖር ሲችል ነው። በመሆኑም ጠንካራ ማንነትን ለመገንባት የሚከተሉትን አድርግ።

  1. መልካሙን ሥራ በርትተህ ሥራ

አንድ ክርስቲያን ለሥራ ያለው አመለካከት የተለየ ነው፡፡ ማለትም እንደ ሌላው ሰው ሥራ ደሞዝ ማግኛ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ትምህርት መማርም ቢሆን ጥሩ ማርክ ማግኛ ብቻ ነው ብሎ ካሰበ አመለካከቱ የተበላሸ ነው፡፡ ሆኖም ሥራም ሆነ ትምህርት ለቁሳዊ ጥቅም ከሚኖረው ፋይዳ በላይ በፍጹም ታማኝነት ተሠርቶ በረከት የሚገኝበት መንፈሳዊ ግዴታ ነው፡፡ በዚህ መልክ ሲታሰብ ክፍያው ከምድራዊነት የሚሻገር በረከት ማግኛ ነው፡፡ ፈጣሪያችን የሥራ አምላክ መሆኑ ሥነ ፍጥረትን ዐቅዶ በመሥራቱ ይታወቃል፡ ፡ ከቀዳሚት ሰንበት ዕረፍት በኋላም የመፍጠር ሥራው ቢያበቃም የመግቦት (የማስተዳደር) እንዲሁም የማዳን ሥራው ቀጥሏል፡፡ “ኢየሱስ ግን አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው” (ዮሐ.5፥17) እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ከሁሉ አስቀድሞ የሰጠው ነገር ሥራን ነው፡፡ “እግዚብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በኤደን ገነት አኖረው፡፡” ዘፍ.2፥15 ይህም በመሆኑ ሰው አስደሳችና ስኬታማ ሕይወት ሊኖረው የሚችለው በመዝናናትና በጨዋታ ሳይሆን በሥራ ነው፡፡

  1. ሕዋሳትህንና ልቡናህን ጠብቅ

“ማንም ሲፈተን በእግዚብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡፡” ያዕ.1፥14 “እንግዲህ ለእግዚብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል፡፡” ያዕ.4፥7 “በመጠን ኑሩ ንቁም ባለጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፡፡” 1ኛ ጴጥ.5፥8

እነዚህ ጥቅሶች የፈተና ምንጮች የሆኑ ነገሮችን ይገልጻሉ፡፡ የመጀመሪያው ጥቅስ የገዛ ራስን ድካም ያነሳል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ዲያብሎስን ይጠቁማል፡፡ መፍትሄውንም ከሁለተኛው ጥቅስ ጋር ሆኖ ሲገልጽ በመጠን መኖር፣ መንቃትና ዲያብሎስን መቃወም እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር መቅረብ መሆኑን ይገልጻል፡፡

  1. ተስፋ አትቁረጥ

“ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት፡፡ እንግዲህ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ፡፡” ገላ.6፥9 ተደጋጋሚ ሽንፈትና ውድቀት (አለመሳካት) ተስፋችንን ሊጎዱ አይገባም፡፡ ሁሌም እንደ አዲስ ልንሠራና ልንታገል ይገባናል፡፡

  1. ግብህ ላይ አተኩር

ሥራህ መከናወን ያለበት በጭፍን አይደለም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ “ዝም ብዬ ነፋስን እንደሚጎስም ሰው አልሠራም” ይላል፡፡ አንተም ከመንቀሳቀስህ በፊት በግልጽ የሚታይ ግብ ከፊትህ ልታስቀምጥ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም “ከእናንተ መካከል ግንብ መሥራት የሚፈልግ ቢኖር አስቀድሞ ግን ድምድማቱን ለመጨረስ የሚያስፈልገውን ኪሳራውን የማያሰላ ማነው”/ ሉቃ 14፡28/ እንደተባለው ግብን መወሰንና የታቀደ ሥራን መሥራት እንደሚያስፈልግ አትዘንጋ፡፡

  1. ምርጫና ውሳኔህ ከዓላማህ አኳያ ብቻ ይሁን

አንድ ውሳኔ ለመወሰን ምርጫዎች ቢበዙብህና አሳብህን መቁረጥ ቢቸግርህ የመቁረጫ መስፈርትህ ሊሆን የሚገባህ ቀደም ብለህ ያስቀመጥከው ግብህ ነው፡፡ ከግብህ የሚያቋርጥ ጓደኛ አያስፈልግህም፣ ግብህን የማይደግፍ ቦታ አትሂድ፡፡ እንዲሁም ግብህን ከሚያጣጥሉ ሰዎች ራቅ፡፡

  1. ባለፈው ውድቀት አትቆዝም

የሠራኸው ኀጢአት ቢኖር በንስሐ ተመለስ እንጂ በጸጸት አትድከም፡፡ መውደቅ መነሣት የማይቀር ሰው የመሆን ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ ወደ ቀደመ መልካም ሥራህ ተመለስ እንጂ በጥፋት ጭልጥ ብለህ አትቅር፡፡ “እንግዲህ ከወዴት እንደወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውን ሥራህን አድርግ፡፡” ራዕ.2፥57 እንዳለ።     ስለመጪው ዘመን አዎንታዊ አመለካከት አዳብር። ሁሌም ሥራህን አስመልክቶ ክፋትም ይሁን ልማት ያለፈውን መርሳት ያስፈልጋል፡፡ ጥፋት ሊያስቆዝምህ አይገባም፡፡ ልማትም ሊያመጻድቅህ አያስፈልግም፡፡ ወደፊት ነገሮች አይስተካከሉም የሚል ቀቢጸ ተስፋ እጅግ አደገኛ አዝማሚያ ስለሆነ ቶሎ ተቆጣጣረው፡፡ ይልቁንም የሕይወት መርሕ ሊሆንልህ የሚገባው እንደ ሐዋርያው “እኔ ገና እንዳልያዝሁ እቆጥራለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴም ወዳለው እዘረጋለሁ፡፡” የሚለው ነው፡፡ (ፊሊጵ.3፥13-14)