በዓለ ሢመቱ ወቅዳሴ ቤቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል
ከመምህር ተስፋሚካኤል ታደለ
በዓለ ሢመቱ ወቅዳሴ ቤቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት ቅዱሳን መላእክት የልዑል እግዚአብሔር የክብሩ መገለጫዎች፣ የፈቃዱ ፈጻሚዎች እና ለሰው ልጅ ድኅነት የሚላኩ አገልጋዮች ናቸው።
ከእነዚህ ቅዱሳን መላእክት መካከል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው። ቅዱስ ሩፋኤል የፈውስ፣ የደስታ፣ የጥበቃ እና የጸሎት አሳራጊ መልአክ መሆኑ ይታወቃል።
በየዓመቱ በወርኀ ጳጉሜን ፫ ቀን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት፣ በቅዳሴ፣ በወረብ እና በምስጋና ይከብራል። ይህ በዓል የሚከበርባቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ያሉ ሲሆን እነርሱም የመጀመሪያው በዓለ ሢመቱ (የሊቀ መላእክትነቱ ማዕረግ የተሰጠበት ቀን) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በእስክንድርያ አቅራቢያ የታነጸችው ቤተ ክርስቲያኑ የተቀደሰችበት (ቅዳሴ ቤቱ) በመሆኑ ነው።
«ሩፋኤል» የሚለው ስም የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን፣ የዋህ እና «እግዚአብሔር ፈዋሽ ነው» ማለት ነው። ይህ ስሙ እንደሚያስረዳው ቅዱስ ሩፋኤል በእግዚአብሔር ቸርነትና ይቅርታ ሰዎችን ከሕማመ ሥጋና ከሕማመ ነፍስ የሚፈውስ፣ ያዘኑትን የሚያጽናና እና ደስታን የሚያበሥር የፈውስ መልአክ ነው።
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያለ ማቋረጥ ፈጣሪውን ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው። በመጽሐፈ ጦቢት ላይ ቅዱስ ሩፋኤል ራሱን ሲገልጥ «የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ» (ጦቢት ፲፪፥፲፭) በማለት የሥልጣኑን ታላቅነት እና የምልጃ አገልግሎቱን ገልጧል።
ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአትና የደዌ ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው። በመጽሐፈ ሄኖክ ላይ «በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው» (ሄኖክ ፲፥፲፫) በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል።
ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ሆነ ቁስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል። ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው እና በምጥ ለተያዙ ሴቶች ታላቅ ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው። ሴት ልጅ ከፀነሰችበት ወቅት ጀምሮ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያትም። ሕፃኑ በማሕፀን እያለ ተሥዕሎተ መልክዕ (በሥላሴ አርአያና አምሳል የመልኩ ቅርጽ መሣል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለየውም። በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ሲማጸኑት ፈታሔ ማሕፀን ነውና ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል። (ሄኖክ ፮፥፫)
ቅዱስ ሩፋኤል በክፉዎች መናፍስት ላይ ታላቅ ሥልጣን የተሰጠው መልአክ ነው። አስማንድዮስ የተባለ እኩይ ጋኔን በራጉኤል ልጅ በሣራ ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሠቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል። (ጦቢት ፫፥፰-፲፯)
በመጽሐፈ ሄኖክ «ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው» ተብሎ እንደተጻፈ (ሄኖክ ፫፥፭-፯)፤ ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥንና መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው። (ሄኖክ ፲፥፬፣ ሄኖክ ፪፥፲፰)
በቅዱስ ሩፋኤል ተራዳኢነት ከተደረጉ ታላላቅ ተአምራት መካከል በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ ያደረገው ተአምር አንደኛውና ዋናው ነው። ይህ ታሪክም የቅዳሴ ቤቱ መታሰቢያ ምክንያት ሆኗል።
በመጽሐፈ ስንክሳር እና በድርሳነ ሩፋኤል እንደተጻፈው ያቺ ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ደሴት በታላቅ ዓሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ነበር።
በጳጉሜን ፫ ቀን ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተሰብስበው ሳለ የሰዎች ብዛት በከበደው ጊዜ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው። በዚህ ጊዜ ደሴቲቱና ቤተ ክርስቲያኗ ፈጽመው ተናወጡ። ምእመናኑም በታላቅ ፍርሃት ሆነው ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔር በከበረ መልአክ በቅዱስ ሩፋኤል ስም ጮኹ። ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል በታላቅ ክብር ተገልጦ ያንን ዓሣ አንበሪ በጦሩ ወግቶ «እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጥ ጸጥ ብለህ ቁም!» ባለው ጊዜ አንበሪው እንደ ድንጋይ ጸጥ ብሎ ቆሟል፤ ደሴቲቱም ከመስጠም ዳነች። በውስጧም ድንቆችና ተአምራቶች ተገልጠዋል፣ ለሕሙማንም ፈውስ ሆኗል።
ከዚህ ታላቅ የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ታሪክና ክብረ በዓል የምንማረው ታላቅ መንፈሳዊ ትምህርት አለ። ይኸውም በመከራና በፈተና ጊዜ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር በጸሎት መጮኽና በቅዱሳኑ አማላጅነት መታመን እንዳለብን ነው። ዓሣ አንበሪው የዚህን ዓለም ሁካታ የሰይጣን ፈተና ሲወክል፣ ቅዱስ ሩፋኤል በጦሩ ወግቶ ማቆሙ ደግሞ የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱሳን ጥበቃ ሕይወታችንን እንደሚያጸና ያሳያል።
ስለዚህ በወርኀ ጳጉሜን ፫ ቀን በዓለ ሢመቱንና ቅዳሴ ቤቱን ስናስብ በሃይማኖት ጸንተን፣ በበጎ ምግባር ተመላልሰን የክብሩ ተካፋዮች እንድንሆን ያስፈልጋል። የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ጥበቃ፣ አማላጅነትና ተራዳኢነት አይለየን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!