መናፍቃን የሚስቱባቸውና የሚያስቱባቸው መንገዶች (አራተኛ ክፍል)

በዳዊት አብርሃም

ጥቅሱን ካጠቃላዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮት (Biblical Theology) አንጻር ለማየት አለመቻል

 ትክክለኛ ትምህርተ መለኮት ጥቅሶችን በዘፈቀደ መደርደር አይደለም፡፡ የተደረደሩት ጥቅሶች ከጥንት ከሐዋርያት ጀምሮ በመጣ አመክንዮ ተያይዘው ትርጉም የሚያስገኙበት ዘዴ አለ፡፡ ይህም ትውፊት ይባላል፡፡ ትውፊት የሌላቸው አብያተ ክርስቲያናት የሉም፡፡ ትውፊትን የሚያጥላሉት ፕሮቴስታንቶች እንኳ ከአውሮፓ የተሐድሶ አባቶች ከነማርቲን ሉተር የሚነሣ የአስትምህሮ ቅብብሎሽ አላቸው፡፡ ምንም አስተምህሯቸውን በጣም የሚለውጡ ክስተቶች እየተፈጠሩ ከነርሱ መካከል ወግ አጥባቂዎች የሆኑት እስኪደነግጡ ቢደርሱም መለዋወጥን የሚፈቅድ ሥርዓት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የራሳቸው ትውፊት ነው፡፡

ትውፊትን ወይም ቅብብሎሽን መቀበል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮትን ለማፅናት ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ነገረ መለኮት ደግሞ ትክክለኛና ጥሩ እንዲሆን ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በጥንቃቄ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ነገረ ድኅነት የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛና ማዕከላዊ ሐሳብ  ስለሆነ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እርስ በርሳቸው ሳይገጫጩ ተስማምተው የሚያስተምሩትን ነገረ መለኮት እያንዳንዱን ጥቅስ ከዚህ አጠቃላይ ምስል አንጻር በመቃኘት መተርጐም ተገቢ ነው፤ ይህን ፈለግ ካልተከተልን ግን መሳሳታችን አይቀሬ ይሆናል፡፡ በልዩ ልዩ የጥናት መስክኮች ‹‹The whole is greater than the sum of its constituents›› ማለትም ‹‹አጠቃላዩ ምስል፣ ምስሉን ከገነቡት ቅንጣቶች ድምር ይበልጣል›› የሚባለው ይህን እውነታ ይበልጥ ስለሚገልጠው እዚህ ጋር ማስታወሱ ይጠቅማል፡፡

ከጥቅሱ ንባብ ይልቅ የራስን ትርጓሜ አስበልጦ ማቅረብ

የተሐድሶ አራማጆች ነን የሚሉት ወገኖችና መሰል ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ጥሬ ቃሉ ላይ እንጂ ትርጓሜ ላይ መመሥረት አያስፈልግም በሚል አቋማቸው የሊቃውንትን የትርጓሜ አሳቦች ሙሉ በሙሉ ለማስወገድና ለማግለል ባያፍሩም ራሳቸው ግን ለቅዱሳት መጻሕፍት የመሰላቸውን ትርጕም ከመስጠት አልሰነፉም፡፡ እንዲያውም እነርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አስመስለው የሚያቀርቡት ኀይለ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ውስጥ ቃለ በቃል ቢፈለግ አይገኝም፡፡ ተቃዋሚዎች ቃሉን ወስደው በራሳቸው መንገድ የተረጎሙትን ነው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አስመስለው የሚጠቅሱት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መዳን በጸጋና በእምነት መሆኑ የመገለጡን ያህል መዳን በሥራ፣ በጥምቀት፣ በጸጋ መንፈስ ቅዱስ፣ በንስሐ፣ በሥጋ ወደሙና በሌሎች በርካታ ነገሮች መሆኑ ተገልጧል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ግን እነዚያን የማይፈልጓቸውን ጥቅሶች ችላ ብለው መዳን በእምነትና በጸጋ መሆኑን የሚገልጡ ንባባት ላይ ብቻ አተኮሩ፡፡ በዚህም አላበቁም፤ ለነዚያ ጥቅሶች የራሳቸውን ትርጕም በመስጠት የመዳን ብቸኛ መንገድ ይህ ነው ብለው ደመደሙ፡፡ መዳናችን የተፈጸመው በጌታ መሆኑ የታመነ ነው፡፡ ሆኖም ስለ ጌታ ማዳን የተነገሩትን ጠቅሶ መተርጐም እንዳለ ሆኖ “መዳን በጌታ ብቻ ነው” የሚል የግል ንግግር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ አስመስሎ ማቅረብ ውሸት ከመሆኑም በላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይልቅ የራስን ሐሳብ  ማስቀደም ነው፡፡

መናፍቃን ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ይልቅ የራሳቸውን ትርጕም የተከተሉበትን አንድ ምሳሌ እንመለከት፡፡ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ነው፤ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።” (ዮሐ.6፡53-56) በማለት የሥጋ ወደሙን አዳኝነት ግልጽ አድርጎ ማስተማሩ ተጽፏል፡፡ መናፍቃኑ ግን ይህን መቀበል ስላልፈለጉ “ሥጋውን መብላት ደሙን መጠጣት ማለት ቃሉን በእምነት መቀበል ማለት ነው” ብለው ይከራከራሉ፡፡ ይህ የእነርሱ ሐሳብ  ግን በመጽሐፍ ቅዱስ በጭራሽ አይገኝም፡፡

አንድን ጥቅስ ለተቃርኖ አስተያየት መጠቀም

ሌላው የስሕተት መንስኤ ከላይኛው ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ሆኖ የተለየ ጠባይ ያለው ነው፡፡ ይኸውም ለጥቅሱ ተገቢ የሆነውን ማብራሪያ ከመስጠት ይልቅ ጥቅሱን ያልሆነውን ወይም አሉታውን ሐሳብ በመግለጥ ለመተርጐም ሙከራ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የእግዚአብሔር ቃል የሕይወት ቃል መሆኑን የሚገልጡ ጥቅሶች ያነቡና መዳን በቃሉ ከሆነ ለመዳን ጥምቀት አያስፈልግም ማለት ነው ብለው ይደመድማሉ፡፡ መዳን በእምነት መሆኑን የሚገልጡ ጥቅሶችን ያነቡና ስለዚህ መልካም ሥራ አያስፈልግም ብለው በአሉታ ይተረጒማሉ፡፡ መዳን በጸጋ መሆኑን የሚገልጡ ጥቅሶችን ያነቡና ለመዳን ምንም ጥረት ከሰው አያስፈልግም ይላሉ፡፡ ሆኖም መዳን በቃሉ ስለሆነ ጥምቀት አያስፈልግም የሚል ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለመኖሩም በላይ በትርጕምም ቢሆን ይህን ዓይነቱን ትርጓሜ ስልት ትክክል ተገቢ አይደለም፡፡ መዳን በእምነት ነው ማለት መልካም ሥራ አያስፈልግም ማለት ነው የሚል መደምደሚያ ፍጹም ምክንያታዊ አይደለም፡፡ መዳን በጸጋው ነው ማለት ከሰው ምንም የሚጠበቅ ድርሻ የለም የሚል መደምደሚያ ሊያስከትል አይችልም፡፡

በጥቅሱ ውስጥ ያልነበረ ቃል መጨመር

ሰው የራሱን ሐሳብ  ትክክል ለማስመሰልና የሌሎችን ደግሞ ነቅፎ ለማስነቀፍ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ብዙ ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን ሊጠቀም ይችላል፡፡ የፕሮቴስታንቱ ዓለም የራሱን የመዳን ትምህርት ትክክለኛ ለማስመሰልና ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርት ለመቃወም ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ቃል ጨምሮ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስመሰል ነው፡፡ መዳን በእምነት እንዲሁም መዳን በጸጋ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፡፡ “መዳን በእምነት ብቻ” “መዳን በጸጋ ብቻ” የሚል ቃል ግን አልተጠቀሰም፡፡ “ብቻ” የምትለው ቃል ወሰንን ታመለክታለችና ቀላል ቃል አይደለችም፡፡ ይህችን ቃል የሚጠቀሙ ሰዎች ምናልባት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ ጣልቃ ገብታ ስትነገር ጉዳቷ አይስተዋልም በሚል ግምት ተነሣሥተው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም “ብቻ” የምትለው ቃል መኖር አለመኖር በትርጕም ውስጥ ትልቅ ልዩነት ይፈጥራል፡፡ በመሠረቱ የራሳቸው የፕሮቴስታንት ምሁራን “በእምነት ብቻ” “በጸጋ ብቻ” የሚል ቃል ወይም ነገረ መለኮት በትርጓሜ ሒደት የተፈጠረ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳችም ቦታ እንደማይገኝ ያምናሉ፡፡ በተቃራኒው ግን ይህን ሐሳብ  ትተው እውነታውን ሊከተሉ አይፈልጉም፡፡

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አምርሮ መጥላት

መጽሐፍ ቅዱስን በጠቅላላው አጥብቀው የተረዱ የሚመስሉና ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱስን አያነቡም በሚል ወቀሳ የሚያበዙ የፕሮቴስታንት ክፍሎች ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አስተካክለው ለመቀበል የሚቸገሩበት ጊዜ በታሪካቸው ውስጥ በተደጋጋሚ ተከሥቷል፡፡ እንቀበላቸዋለን ከሚሏቸው ስድሳ ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል እንኳ የሚጠሉትና የሚጠራጠሩት ክፍል አለ፡፡ ከዚህም ውስጥ ከነገረ ድኅነት ጋር በተያያዘ አንድ ምሳሌ እናቅርብ፡፡

ከፕሮቴስታንት መሪዎች መካከል ቀንደኛው ማርቲን ሉተር ሲሆን ይህም ሰው በተለይ “ለመዳን እምነት ብቻ በቂ ስለሆነ ሥራ አያስፈልግም” የሚለውን ትምህርት በማስፋፋት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህን ሐሳቡን የሚቃወሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለሐሳቡ እንቅፋት በመሆን ትምህርቱን ያሰናክሉበት ነበር፡፡ በተለይ የያዕቆብ መልእክት ለመዳን እምነት ብቻ በቂ እንዳልሆነና ሥራ መሥራት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ በስፋትና ግልጽ በሆነ ቋንቋ አበክሮ በመግለጡ ሉተር ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አምርሮ ጠላው፡፡ በተደጋጋሚም “የያዕቆብ መልእክት ምንም ፍሬ የማይገኝበት ገለባ ነው” ብሎ ከመናገርም አልፎ ይህንኑ ሐሳቡን በጽሑፍ አስፍሮታል፡፡ (ቄስ ኮሊን ማንሰል፣ ትምህርተ እግዚአብሔር፣ ገጽ 81) ሉተር የያዕቆብን መልእክት የመጥላቱና የመቃወሙ ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ የግል አሳቡን እንኳን ሊደግፍለት ቀርቶ እንዲያውም የሚቃወምበት ስለሆነ ነው፡፡ ይህ የሉተር ሐሳብ  የጠላት ወሬ ሳይሆን ራሳቸው ፕሮቴስታንቶቹ በየመጽሐፎቻቸው የመሰከሩት እውነት ነው፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *