ጾም

መ/ር በትረ ማርያም አበባው

፩. ጾም ምንድን ነው?

ጾም ማለት ለተወሰነ ሰዓት ከምግብ መከልከል፣ ለተወሰኑ ቀናት ከጥሉላት መከልከል፣ ለዘለዓለሙ ደግሞ ከኃጢኣት መከልከል ማለት ነው። ስለ ጾም ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ በሰፊው ይናገራል። “ጾምሰ ተከልዖተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ እንዘ ይትኤዘዝ ለዘሐገጎ፤ የጾምን ሕግ ለሠራው ጌታ እየታዘዙ ለተወሰኑ ሰዓታት ለተወሰኑ ቀናት ከምግብ መከልከል ነው።”

ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ዓይን ይጹም እዝንኒ ይጹም እምሰሚአ ኅሡም” ብሏል። ይህም ማለት ጆሮ ክፉ ከመስማት ዓይን ክፉ ከማየት ይከልከል ማለት ነው። አጠቃላይ ሕዋሳቶቻችን ክፋትን ከማድረግ ይከልከሉ ማለት ነው። ይህ ዓይነት ጾም እስከ እለተ ሞታችን ድረስ የምንጾመው ጾም ነው። ጾም በብሉይ እና በሐዲስ የነበረ ሕግ ነው “ጾምን ቀድሱ” ብሏል  (ኢዮ. ፩፥፲፬)፡፡

“ጉልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ” (መዝ. ፻፱፥፳፬) እንደ ተባለው በጾም ወቅት ከጥሉላት ምግቦች ማለትም ከሥጋ፣ ከወተት፣ ከቅቤ እና ከመሳሰሉ ምግቦች መከልከል ይገባል። ፍትሐ ነገሥቱም አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፭ “ወኢይትበላዕ ቦሙ ሥጋ እንስሳ ወኢ ዘውእቱ እምእንስሳት፤ የእንስሳት ሥጋ አይበላ ከእንስሳት የሚገኙ ቅቤ ወተትም አይበላ” ይላል። ነቢይት ሐና “በጾምና በጸሎት ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር” ተብላለች። ይህ ጾሟ፣ ጸሎቷ ደግሞ የእስራኤልን መድኃኒት ጌታን ለማየት አብቅቷታል። (ሉቃ. ፪፣፴፯)

ቅዱስ ጳውሎስም ጾምን “በመትጋትና በመጾም፣ በንጽሕናና በዕውቀት፣ በምክርና በመታገሥ፣ በቸርነትና በመንፈስ ቅዱስ አድልዎ በሌለበት ፍቅር፣ በእውነት ቃል በእግዚአብሔር ኃይል ለቀኝና ለግራ በሚሆን የጽድቅ የጦር እቃ” ብሎታል። (፪ኛ ቆሮ. ፮፥፭-፰)

፪. ጾም ለምን ይጠቅማል?

ሀ. እግዚአብሔርን በረድኤት ለመፈለግ፡- ይህም ማለት በሥጋም በነፍስም ይረዳን ዘንድ እንጾማለን። (፪ኛ ዜና.መዋ. ፳፥፫)፡፡ “ኢዮሳፍጥም ፈራ እግዚአብሔርንም ሊፈልግ ፊቱን አቀና በይሁዳም ሁሉ ጾም ዐወጀ” ይላል። እግዚአብሔርን በረድኤት ለመፈለግ ኢዮሳፍጥ ያደረገው ጾምን ማወጅ ነበረ። “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ። ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታናሹ ማቅ ለበሱ፡፡” የነነዌ ሰዎች በበደላቸው ምክንያት ሀገራቸው ልትጠፋ ነበር። ነገር ግን ጾም አውጀው ሁሉም ሰው ከጾመ በኋላ ሀገሪቱ ከጥፋት ድናለች። (ኢዮ. ፪፣፲፪)

“አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” ይላል እግዚአብሔር። ይህም ኃጢኣታችንን በደላችንን አምነን በጾም በልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ብንመለስ ከጥፋት እንደምንድን ማሳያ ነው።

ለ. የቀናውን መንገድ ለማግኘት፡- “በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅሁ” ይላል (ዕዝ. ፰፥፳፩)  ቁጥር ፳፫ ላይ ደግሞ የጾምን ውጤት እንዲህ ብሎ ያስቀምጠዋል “ስለዚህም ነገር ጾምን ወደ እግዚአብሔርም ለመንን። እርሱም ተለመነን” ይላል። ዕዝራ ጾምን ያወጀበትን ምክንያት ተናግሯል ለእኛ ለልጆቻችን እና ለንብረታችን የቀናውን መንገድ ፈጣሪ ይሰጠን ዘንድ ነው በማለት።

ሐ. ለፈውሰ ሥጋ ወነፍስ፡- ጾም ከአጋንንት እስራት ነጸ ለመውጣት ለሥጋዊ ፈውስ እና ኃጢኣትን ለማስተስረይ ይጠቅማል። ጌታም ደቀ መዛሙርቱ ሊፈውሱት ያልቻሉትን በሽታ በምን እንደሚፈወስ ሲነግራቸው “ይህ ወገን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም” ብሏቸዋል።(ማር.፱፥፳፱)

ቅዱስ ያሬድም በድጓው ይህንኑ የሚያጠናክር ቃል ተናግሯል “ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ ወታጸመም ኲሎ ዘሥጋ ፍትወታ፤ ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች የሥጋን ፍትወትም ታጠፋለች” ብሏል። የነፍስ ቁስል የተባለ ኃጢኣት ነው። ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች ማለት ኃጢኣትን ታስተሰርያለች ማለት ነው።

ሠለስቱ ምእትም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፬ “ለሥርየተ አበሳ ኃጢኣቱ ሊሠረይለት፤ ወብዝኀ እሴት፤ ዋጋው ሊበዛለት፣ ከመ ያድክም ኃይለ ፍትወት፤ የፈቲውን ጾር ያደክም ዘንድ፣ ወትትአዘዝ ለነፍስ ነባቢት፤ ሥጋ ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ለክርስቲያን ሁሉ ጾም የታዘዘ ነው እንዲል፡፡

፫. ተቀባይነት የሌለው ጾም፡- ጾም ከጸሎት እና ከፍቅር ጋር እንዲሁም ከሌሎች መልካም ሥራዎች ጋር ካልሆነ ተቀባይነት የለውም። ይህንንም እግዚአብሔር እንዲህ ይለናል “ስለምን ጾምን አንተም አልተመለከትኽንም” ይላሉ። እነሆ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ። ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ ለጠብና ለክርክር ትጾማላችሁ። እኔ ይህንን ጾም የመረጥሁ አይደለም። ይህ ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠ አይደለም” ተብሏል (ኢሳ.፶፰፥፫-፭)

ሰውን እየበደልን እኛ ብንጾም ጾማችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ሰው ጿሚ ነህ ይበለኝ ብለን በሌሎች ሰዎች ለመወደስ የምንጾመው ጾምም ተቀባይነት የለውም። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህን ታጠብ። በስውር የሚያይ አባትህ በግልጥ ይከፍልሃል” ብሎ ተናግሯል።(ማቴ.፮፥፲፯-፲፰)

በእርግጥ ይህ ቃል የተነገረው ከአዋጅ ጾም ውጭ ለምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው እንጂ የአዋጅ ጾምስ በአዋጅ የሚጾም በሁሉ የሚታወቅ ስለሆነ ከንቱ ውዳሴ የለበትም። በስውር ጹም የተባለ ከአዋጅ አጽዋማት ውጭ ከንስሓ አባታችን ቀኖና ተቀብለን በምንጾመው እና እኛው በፈቃዳችን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ለማግኘት ብለን በምንጾመው ጾም ጊዜ ማንም የትሩፋት ጾም እንደምንጾም ሊያውቅ አይገባም።

፬. የአዋጅ አጽዋማት

በብሉይ ኪዳንም በተለየ የሚጾሙ ቀናት ነበሩ። ይህንንም “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሴትም በዓላት ይሆናል”(ዘካ. ፰፥፲፱) ከዚህ የምንረዳው በተጠቀሱት ወራት የሚጾም ጾም እንደነበረ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ሁሉም ክርስቲያን ሊጾማቸው የሚገቡ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡-

ሀ. ጾመ ኢየሱስ፡- ይህ ጾም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ የጾመውን አስበን የምንጾመው ጾም ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ   እንደተጠመቀ ልዋል ልደር ሳይል ከጥር ፲፩ ጀምሮ እስከ የካቲት ፳፩ ድረስ በቆሮንቶስ ገዳም ገብቶ ጾሟል (ማቴ.፬፥፩) የዚህ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል። እስከ ፲፪ ሰዓት ይጾማል። ሁለተኛው ሣምትን ቅድስት፣ ሦስተኛው ሣምንት ምኲራብ፣ አራተኛው ሣምንት መጻጉዕ፣ አምስተኛው ሣምንት ደብረ ዘይት፣ ስድስተኛው ሣምንት ገብር ኄር፣ ሰባተኛው ሣምንት ኒቆዲሞስ፣ ስምንተኛው ሣምንት ሆሣዕና ይባላል። ከቅድስት ጀምሮ እስከ ኒቆዲሞስ አርብ እስከ ፲፩ ሰዓት ይጾማል። ከሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ያለው ሰሙነ ሕማማት ይባላል። እስከ ምሽቱ ፩ ሰዓት ይጾማል። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፭።

ለ. ጾመ ድኅነት፡- ይኸውም ከበዓለ ሃምሳ ውጭ እና ጥምቀትና ልደት ረቡዕ እና አርብ ካልዋለ በሌላው ጊዜ መጾም ነው። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፮። ረቡዕ እና አርብ የሚጾሙትም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ነው።

 ሐ. የነነዌ ጾም፡- ይህም ለጊዜው የነነዌ ሰዎች ከጥፋት ድነውበታል። (ትንቢተ ዮናስን ይመልከቱ)። እኛም መቅሰፍት እንዳይደርስብን እንደ ነነዌ ሰዎች እንጾመዋለን። (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፯)፡፡

 መ. የገሃድ ጾም፡- ይህም የልደት እና የጥምቀት ዋዜማ በሚውለው ዕለት የሚጾም ነው። ጥምቀት ጌታ አንድነቱን ሦስትነቱ የገለጠበት ሲሆን ልደት ደግሞ የማይታየው በሥጋ የተገለጠበት የታየበት ስለሆነ ገሃድ ማለት መገለጫ ማለት ነው። (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፯)፡፡

ሠ. የነቢያት ጾም፡- ይኸውም በአራቱም ዘመናት ከኅዳር ፲፭ ጀምሮ እስከ ልደት ያለው ነው። ነቢያት ጌታ ይወርዳል ይወለዳል እያሉ የጾሙት ጾም ነው። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፰)፡፡

ረ. የሐዋርያት ጾም፡- ይህ ደግሞ ከጰራቅሊጦስ ጀምሮ እስከ ሐምሌ ፭ የሚጾመው ጾም ነው። ሐዋርያት በዕጣ ተከፋፍለው ወደየሀገረ ስብከታቸው ከመሄዳቸው በፊት አገልግሎታቸው የሠመረ ይሆን ዘንድ የጾሙት ጾም ነው(ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፷፱)፡፡

ሰ. ጾመ ማርያም፡- ከነሐሴ ፩ ጀምሮ እስከ ነሐሴ ፲፮ ያለው ነው። ሐዋርያት ሥጋ ማርያምን ለማግኘት ሱባኤ የገቡበትና ጌታም ከአጸደ ገነት አምጥቶ ሰጥቷቸው ገንዘው ከቀበሯት በኋላ ነሐሴ ፲፮ ተነስታ አርጋለች። የዚያ መታሰቢያ ነው። ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት የሚባሉት እነዚህ ናቸው። ከዐቢይ ጾም ውጭ ያሉት ሌሎች አጽዋማት እስከ ፱ ሰዓት ነው የሚጾመው። በጾም ወቅት እሑድ ቅዳሜ ከጥሉላት ብቻ ተከልክለን እንውላለን እንጂ እንደሌለው እስከዚህ ሰዓት ጹም የሚል የላቸውም። ቀዳም ስዑር ብቻ ይጾምባታል። በሌላው ግን የለም። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፭ ቁጥር ፭፻፸፪ ፡፡ “ወኢይጹሙ በዕለተ እሑድ ወበሰንበት ዘእንበለ ጥሉላት” እንዲል።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *