ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ጥቅሙና ጉዳቱ
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ጥቅሙና ጉዳቱ
ከመምህር ሓጋዚ አብርሃ
ባለንበት ዘመን ማኅበራዊ ሚዲያ በወጣቱ መንፈሳዊ ሕይወት፣ ሥነ ምግባር፣ ሥርዓተ ትምህርት እና ሥነ-ልቡናዊ ሕይወት ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ በራሱ መሣሪያ ነው፤ መሣሪያ ደግሞ እንደ አጠቃቀማችን ወይ ይገነባናል ወይም ያፈርሰናል። “ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል” እንዲሉ አበው አእምሮ ያለን አገናዛቢ፣ ልብም ያለን አሳቢ ፍጡር ነን። ከዚህ የተነሣ ይጠቅሙናል፣ ድካማችንን ይቀንሱልናል ብለን ያዘጋጀናቸው መሣሪያዎች እንዳሰብነው ሳይሆን አሉታዊ ተጽዕኗቸው ሲጨምር ከአጠቃቀማችን አንጻር ቆም ብሎ ማሰብ ያለብን እኛው የሰዎች ልጆች ነን። “ሰው ሠራሽ አስተውሎት” (AI) በተመለከተ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች አኳያ በትንታኔ ለማየት እንሞክራለን።
- ሰው ሠራሽ አስተውሎት ምንድ ነው?
ሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) በሰዎች የሚሠሩ፣ ማሰብና ማገናዘብ የሚችሉ ተደርገው የተዘጋጁ የኮምፒውተር ሥርዓቶች ወይም ፕሮግራሞች ማለት ነው።
በሌላ አገላለጽ፦ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሰጠውን የማሰብና የመማር ችግሮችን መፍታትና ውሳኔ መስጠት የሚያስችለውን አእምሯዊ ብቃት (Intelligence) የሰው ልጅ ደግሞ ማሽኖች (ኮምፒውተሮች) እንዲመስሉት አድርጎ የፈጠረው ጥበብ ነው።
ለምሳሌ፡- ChatGPT፣ የትርጉም ሥርዓቶች፣ የምክር አልጎሪዝሞች (recommendation algorithms) ፣ አውቶማቲክ የምርምር መሣሪያዎች፣የድምፅ ረዳቶች፣ ምስል አመንጪዎች (image generators) ፣ እና የትምህርት ሶፍትዌሮች ተጠቃሾች ናቸው።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ “ሰው ሠራሽ አስተውሎት” (AI) በትምህርት፣ በኮሙኒኬሽን፣ በምርምር እና በዕለት ዕለት የሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ካሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሣሪያዎች አንዱ ሆኗል። ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደ ቻትቦቶች (chatbots)፣ የምርምር ረዳቶች፣ የትርጉም መሣሪያዎች እና አውቶማቲክ የመማሪያ መድረኮችን የመሳሰሉ የ-AI ሥርዓቶችን በስፋት እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ምንም እንኳን AI ብዙ ጥቅሞችን ቢሰጥም፣ ያለ አግባብ ከተጠቀምንበት ወይም ከልክ በላይ በእሱ ላይ ከተደገፍን ሥነ-ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ጉዳቶችን ያስከትላል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ የግቢ ጉባኤያት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በሁለት አስፈላጊ ዘርፎች በተመሳሳይ ጊዜ የሕይወት ለውጥ እንዲያመጡና እንዲያድጉ ይጠበቃል።
- የትምህርት ጥራትና ብቃት ፡- በተሰማሩበት የትምህርት ዘርፍዕውቀትን፣ ጥበብን፣ ጥልቅ አስተሳሰብን እና ሙያዊ ብቃትን ማግኘትና ማሳደግ፤
- ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊ ሕይወት፡- በጾም፣ በጸሎት፣ በትምህርተ ሃይማኖት ዕውቀት፣ በትሕትና፣ በንስሓ እና በምሥጢራት ሱታፌ፣ በማስተዋልና በትዕግሥት፣ በቅድስና እና ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ኅብረት መሳተፍና ማደግ ናቸው።
የፈጠራ ቴክኖሎጂ በራሱ ክፉ አይደለም። ችግሩ ያለው የሰው ልጅ የአጠቃቀም መንገድ ላይ ነው። ልክ እንደማንኛውም የሰው ልጅ ፈጠራ ሁሉ፣ AI ለበጎ ነገር የሚውል መሣሪያ ወይም የጉዳት ምንጭ ሊሆን ይችላል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ፤ ሁሉ ግን አይጠቅምም”(፩ኛ ቆሮ. ፮፲፪) እንዳለው የግቢ ጉባኤያት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች AI-ን እንዴት በጥበብ፣ በተጠያቂነት እና ለመንፈሳዊ አገልግሎት መጠቀም እንደሚችሉ መረዳትና መገንዘብ ይገባል።
ቅዱስ መጽሐፍ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።” እንዳለ (ምሳሌ ፱፥፲) በኦርቶዶክሳዊ የሥነ-መለኮት ትምህርት መሠረት እውነተኛ ጥበብ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነው። ሰው ሠራሽ አስተውሎት መረጃ ሊያቀናብር ይችላል እንጂ መሠረታዊ አካዳሚያዊ ጥበብን፣ ተግባራዊ ልምምድን ወይም የሰው ልጅ ኃላፊነትን ሊተካ አይችልም።
- የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጥቅሞች
የግቢ ጉባኤያት ኦርቶዶክሳውዯን ተማሪዎች ሰው ሠራሸ አስተውሎትን በአግባቡ እና በኃላፊነት ስሜት ጥቅም ላይ ማዋል ከቻሉ በሚከተሉት ጉዳዮች በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ሀ. ለትምህርት
- መረጃን በቀላሉ ማግኘት፡-
ሰው ሠራሽ አስተውሎትተማሪዎች መጻሕፍት፣ የምርምር ጽሑፎች፣ ማብራሪያዎች፣ የቋንቋ ትርጉሞች እና ማጠቃለያዎች በፍጥነት እንዲያገኙ ይረዳል። ይህ የመማር ብቃትንና ፍጥነትን ሊያሻሽል ይችላል።
- የምርምር እገዛ
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሐሳቦችን በማደራጀት፣ ረቂቅ ማውጫዎችን በማዘጋጀት፣ ዋቢ መጻሕፍትን በማስገኘት፣ ሰዋሰውን በማስተካከል፣ ረጅም ጽሑፎችን በማጠቃለል፣ እና መረጃዎችን በመተንተን ተማሪዎችን ሊረዳ ይችላል። እንዲሁም ለድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች የሥነ-ጽሑፍ ክለሳ (literature review) ፣ የጽሑፍ ቅርጽ ማስተካከል ፣ የዋቢ ጽሑፎች አደረጃጀት (citation organization) ወ.ዘ.ተ ላይ ሊያግዝ ይችላል።
- የቋንቋ እና የተግባቦት ድጋፍ
በባዕድ ቋንቋዎች የሚቸገሩ ተማሪዎች ሰው ሠራሽ አገልግሎት ለትርጉም፣ ለሰዋስው እርማት፣ ቃላትን ለመማር እና ለአካዳሚክ ጽሑፍ ድጋፍ መጠቀም ይችላሉ።
- የጊዜ ቁጠባ
በተለምዶ ብዙ ሰዓታት የሚወስዱ ሥራዎች አንዳንድ ጊዜ በ-AI እገዛ በፍጥነት ሊጠናቀቁ ይችላሉ፤ ይህም ተማሪዎች ይበልጥ ጥልቅ በሆነ ጥናትና ትንተና ላይ እንዲያተኩሩ ዕድል ይሰጣል።
ለ. ከቤተክርስቲያን እና መንፈሳዊ ሕይወት ጋር የተያያዙ ጥቅሞች
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ሲውል ለቤተክርስቲያን አገልግሎት እና ለመንፈሳዊ ትምህርት ሊያግዝ ይችላል።
- መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለማግኘት
የክፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ለመፈለግ፣ የቀደሙት ሊቃውንትና የቅዱሳን አባቶችን ጽሑፎች ለማግኘት፣ የቤተክርስቲያንን ታሪክ ለመማር፣ ኦርቶዶክሳዊ ሥነ-መለኮትን ለማጥናት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
- ለሐዋርያዊ አገልግሎት (ለትምህርታዊ አገልግሎት)
የቤተክርስቲያን መምህራንና አገልጋዮች ሰው ሠራሽ አገልግሎትን ትምህርቶችን ለማዘጋጀት፣ የማስተማሪያ ቁሳቁሶችን ለማደራጀት፣ ሰነዶችን ለመተርጎም፣ እና የኢንተርኔት (ኦንላይን) ስብከተ-ወንጌልን ለመደገፍ በሚገባ ሊገለገሉበት ይችላሉ።
- በቤተክርስቲያን ፈተናዎች እና ችግሮች ላይ ምርምር ለማድረግ
ከላይ ካየናቸው ጥቅሞች ከፍ ባለ መንገድ ከተመለከትነው ደግሞ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የግቢ ጉባኤያት አገልጋዮች በተለይ ድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች ማኅበራዊ ፈተናዎችን ለመተንተን፣ የወጣቶችን ችግሮች ለመመርመር፣ የግቢ ጉባኤያት እና የሰንበት ትምህርት ቤቶችን የአገልግሎት አካሄድ ለማጥናትና ለማዘመን፣ ከአኀት እና ሌሎች ምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተያያዙ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የአገልግሎት መፍትሔዎችን ለመቅረጽ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።
- የሰው ሠራሽ አስተውሎት ጉዳት
ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችም ጥቅሞች ቢኖሩትም፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ከዋለ በቀላሉ የማንወጣቸው ከባድ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል።
ሀ. ትምህርታዊ ጉዳቶች
- ጥገኝነት እና ምሁራዊ ስንፍና
ሰው ሠራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ላይ ከሁሉ የላቀው አደጋ በእሱ ላይ ከመጠን በላይ መደገፍ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ በAI ላይ ሲደገፉ፦ በጥልቀት ማሰብ ያቆማሉ፤ ማንበብን ይተዋሉ፤ የማሰብ (የመተንተን) ችሎታቸውን ያጣሉ፤ እናም የፈጠራ ብቃታቸው ይዳከማል። መማር ደግሞ ጥረትን፣ ሥርዓትን (ዲስፕሊንን) እና ልፋትን ይጠይቃል። ኦርቶዶክሳዊ የቅዱሳን አባቶች ሕይወት እንደሚያስተምረን አእምሮአዊም ሆነ መንፈሳዊ ዕድገት የሚመጣው በሥራና በትዕግሥት ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከእናንተ ጋር ሳለን፦ ሊሠራ የማይወድ ማንም አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና።” (፪ኛ ተሰ. ፫፥፲) እንዳለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ማሰብን ሊያግዝ ይገባል እንጂ ሊተካው አይገባም።
- የምርምር ክሂሎት መዳከም
እውነተኛ ምርምር ጥያቄ መጠየቅን፣ ማጣራትን፣ ማነጻጸርን፣ መተንተንን፣ እና የራስን አዲስ ትንታኔ ማቅረብን ይጠይቃል። ተማሪዎች በ-AI የተፈጠረውን ጽሑፍ ዝም ብለው የሚገለብጡ ከሆነ ፡- የምርምር ዘዴን ማዳበር ያቅታቸዋል፤ የአካዳሚክ ታማኝነትን ያጣሉ። ከዚህ የተነሣ ራሳቸውን ችለው ሳይንሳዊ ሥራዎችን መሥራት የማይችሉ ይሆናሉ። በመጨረሻም እንዲህ ዓይነቶቹ ተማሪዎች ዲግሪ ሊይዙ ይችላሉ፤ ነገር ግን እውነተኛ ብቃት አይኖራቸውም።
- የሌሎችን ሥራ መስረቅ (Plagiarism) እና አካዳሚካዊ ታማኝነት ማጣት
በሰው ሠራሽ አስተውሎት-AI የተዘጋጀን ሥራ ያለ ምንም ግምገማ ወይም ምንጩን ሳይጠቅሱ በቀጥታ መቅዳት የስርቆት እና የሐሰተኝነት መገለጫ ነው። አካዳሚካዊ ታማኝነት እውነተኛነትንና ኃላፊነትን ይጠይቃል። የኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነትም ሐሰትን በጥብቅ ይከለክላል። በቅዱስ መጽሐፍ “ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ … እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።” (ኤፌ. ፬፥፳፭) እንዳለ አንድ ክርስቲያን ተማሪ ለምቾት ሲል እውነትን አሳልፎ መስጠት የለበትም።
- የተሳሳተ መረጃ እና ዕውቀት
ሰው ሠራሽ አስተውሎት አንዳንድ ጊዜ ትክክል ያልሆኑ መረጃዎችን፣ ተሳሳቱ ዋቢ መጻሕፍትን፣የተዛቡ ትርጓሜዎችን ወይም ወገንተኝነት ያለባቸውን ድምዳሜዎች ያመነጫል። እንዲሁም መንፈሳዊ ምሥጢራትን ወይም ታሪካዊ እውነታዎችን በትክክል ላይረዳ ይችላል። የነገረ መለኮት (Theology) ዕውቀትን ከሰብአዊ ፍልስፍና ጋር በመደባለቅ የተሳሳተ ድምዳሜ ሊሰጥ ይችላል።
ለ. ከቤተክርስቲያናዊ ሕይወት አኳያ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
ቶሎ ማስተዋልና መረዳት ካልተቻለ በAI ምክንያት በሚያጋጥሙ ፈተናዎችበመንፈሳዊ ሕይወት የሚደርሰው ጉዳት ከአካዳሚክ ጉዳት የከፋ ሊሆን ይችላል። ለዚዚህም የሚከተሉትን ማሳያዎች እንመልከት፡-
- የግል መንፈሳዊነት መዳከም
ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ክርስቲያናዊ ተጋድሎን፣ ሥርዓትን ፣ ትዕግሥትን፣ ትኩረትን፣ ጽናትንና ትጋትን እጅጉን ይፈልጋል። ለፈጣን የቴክኖሎጂ እገዛ ሁል ጊዜ መገዛት ትዕግሥትን፣ ጸጥታን፣ የተመስጦ ሕይወትን፣ ጥልቅ ሱባኤን ወዘተ. ሊያዳክም ይችላል።
- ከቤተክርስቲያን ኅብረት እና ከአባቶች ምክር መለየት
ከልክ ያለፈ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ጥገኛ መሆን ከቅድስት ቤተከርስቲያን ኅብረታዊና ሥርዓተ-አምልኮ ሕይወት፣ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ምክርና ኑዛዜ ከቤተክርስቲያን ትውፊት ወዘተ. ቀስ በቀስ ሊነጥለን እና ሊያርቀን ይችላል።
- ትዕቢት እና የዕውቀት ቅዠት
መረጃን በቀላሉ ማግኘት ምሁራዊ መታበይን ሊፈጥር ይችላል። ‘መረጃዎችን ወዲያውኑ ማግኘት ስለምችንል ሁሉንም ነገር አውቃለሁ’ ወደሚል ግልብ ሕይወት ሊመራን ይችላል። ነገር ግን ያገኘነው መረጃ እንጂ ጥበብ አይደለም። የቤተክርስቲያን አባቶች ከትዕቢት እንድንጠበቅ ደጋግመው ያስጠነቅቃሉ። ትዕቢት መንፈሳዊ ማስተዋልንና ጥበበ እግዚአብሔርን ሊያጨልም ይችላልና።
- ጸጥታ እና የውስጥ ትኩረት ማጣት
የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች አእምሮን ዘወትር ያነቃቁታል። ከመጠን በላይ በዲጂታል ነገሮች ላይ ጥገኛ መሆን የውስጥ ጸጥታን (እርጋታን)፣ ማሰላሰልን፣ ጸሎትን እና ለእግዚአብሔር የሚሰጠውን ትኩረት ያዳክማል።
- የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች AIን እንዴት እንጠቀም?
መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ” ይላል። (፩ኛ ተሰ. ፭፥፳፩) የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ቴክኖሎጂውን እንደ ጌታ ሳይሆን እንደ አገልጋይ ሊጠቀሙበት ይገባል።
- AIን እንደ ማሟያ መሣሪያ ብቻ መጠቀም
ተማሪዎች ለሚፈልጓቸው ጉዳዮች መጻሕፍትን በራሳቸው ማንበብ፣ የራሳቸውን ትንታኔ መጻፍ፣ በሂሳዊ መንገድ መመልከት እና AI-ን የመማር ሂደታቸውን ለመደገፍ ብቻ መጠቀም አለባቸው። በመሠረታዊነት ጥሩ ትምህርት ጥያቄን፣ ጥረትን፣ መተንተን እና ሥርዓትን ይፈልጋል።
- መረጃዎችን በጥንቃቄ ማረጋገጥ
ተማሪዎች ከ-AI የሚያገኟቸው ምላሾችን ከአካዳሚክ መጻሕፍት፣ ከምርምር መጽሔቶች (journals)፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከአባቶች ጽሑፎች፣ እና ከታመኑ ምሁራን ሥራዎች ጋር በማነጻጸርና በማመሳከር ጉዳዮችን በማስተዋል መጠቀም አስፈላጊ ነው።
- የቤተክርስቲያን ሥርዓትን መጠበቅ
የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ምን ጊዜም ቴክኖሎጂን ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ሥርዓት ሥር አድርገውና አስማምተው መጠቀም ላይ ቆራጥ መሆን ይጠበቅባቸዋል። በተለይ የጾም፣ የጸሎት፣ የንስሐና የምሥጢራት ሕይወትን፣ የቅዳሴና የሥርዓተ አምልኮ ሱታፌን፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ሕይወትን ወዘተ. የAI አገልግሎት ጊዜ እንዲተካባቸው በፍጹም መፍቀድ የለባቸውም።
- እውነተኛ ጥናትና ምርምር ማድረግ
የግቢ ጉባኤያት አመራር እና ተመራቂ ተማሪዎች በተለይ የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ (thesis) በሚጽፉበት ጊዜ በቀጥታ ከ-AI የመቅዳት ፈተና ይገጥማቸዋል። ይህ ትልቅ አካዳሚያዊና መንፈሳዊ ችግሮችን ይፈጥራል። ይልቁንም ተማሪዎች AI-ን በኃላፊነት ስሜት ሊጠቀሙበት ይገባል።
AI ለምናደርጋቸው ጥናቶችና ምርምሮች የጽሑፍ ቅርጽ (formatting)፣ ማውጫዎች፣ ማጠቃለያዎች፣ እና አደረጃጀትን በመስጠትና በመፍጠር ሊያግዝ ይችላል። ነገር ግን ክርክሮች (arguments)፣ ትንታኔዎች (analysis)፣ ትርጓሜዎች (interpretation)፣ እና ድምዳሜዎች (conclusions) ወ.ዘ.ተ ከተማሪ ከራሱ ምሁራዊ ጥረት መምጣት አለባቸው።
ይልቁንም ጠንካራ ምርምር እውነተኛ ችግሮችን እንደሚፈታ በማመን ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ ማድረግ፣ የመስክ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ የቤተክርስቲያንን ነባራዊ ሁኔታዎች መታዘብ፣ የአካባቢውን ችግሮች መተንተን፣ እና ከእውነተኛ የሚመለከታቸው አካላት/ማኅበረሰብ ጋር በመገናኘት የተፈተነና የታሸ የጥናትና ምርምር ውጤት ባለቤት መሆን መቼም ሊዘነጋ አይገባውም።
በቤተ ክርስቲንና ኦርቶዶክሳውን ሕይወት ታሳቢ ሊሆኑ የሚችሉ የጥናትና ምርምር መስኮች፦
- የወጣቶች መንፈሳዊ ተጋድሎ (ፈተናዎች)፣
- የቴክኖሎጂ ሱስ፣
- የቤተክርስቲያን ጥንታውያን መጻሕፍትንና የብራና ጽሑፎችን በዲጂታል መንገድ የመጠበቂያ (Archiving) ሥርዓት
- የግእዝ ቋንቋን ጠብቆ ማቆየት፣
- የዲጂታል ስብከተ-ወንጌል አገልግሎት
- ሥነ-ምግባራዊ የ-AI አጠቃቀም፣
- የአእምሮ ጤና እና መንፈሳዊነት፣
- ጥናትና ምርምር ለቤተክርስቲያን ያለው ፋይዳ
- የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሥርዓቶች የተወሰኑት ናቸው።
- አካዳሚክ ጥራትን ከመንፈሳዊ ሕይወት ጋር ማዋሐድ
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ “ለመንፈሳዊ ሕይወት የሚጠቅመንን ዕውቀት ከዓለማውያን መጻሕፍትም ቢሆን መቅሰም አለብን” እንዳለው፣ ትምህርት የሰውን ልጅ ወደ በጎነት እና ወደ እውነት ሊመራው ይገባል። ስለዚህ በግቢ ጉባኤያት የሚያልፉ ምሁራን እውነትን፣ ትሕትናን፣ ታማኝነትን፣ አገልጋይነትን … ገንዘብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ከእነዚህ መንፈሳዊ ዕሴቶች ውጭ የሆነ ዕውቀት የትም ሊያደርስ አይችልም። ያለ እግዚአብሔር የሚደረግ የሰው ልጅ እድገት አደገኛ እንደሆነ ቤተክርስቲያን ታስተምራለች። ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ከኃጢአት፣ ከሞት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ከትዕቢት ወይም ከመንፈሳዊ ባዶነት ሊያድነው አይችልም። የሰውን ልብ በበጎነት የሚለውጠው እና ወደ ፍጹም ድኅነት የሚያደርሰው እግዚአብሔር ብቻ ነው።
ቅዱስ መጽሐፍ “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል?” (ማር. ፰፥፴፮) እንዳለ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AIን) ስንጠቀም መንፈሳዊ ማንነታችንን በማያጠፋ እና ለአካዳሚክ ስኬታችን ድጋፍ በሚሰጥ ሚዛን ላይ መሆን አለበት።
በአጠቃላይሰው ሠራሸ አስተውሎት (AI) ለክርስቲያኖች በጎ ዕድልም ፈተናም ነው። ሙሉ በሙሉ በጎ ወይም ሙሉ በሙሉ ክፉ አይደለም። ጥቅሙ የሰው ልጅ በሚጠቀምበት መንገድ ላይ የሚወሰን ነው። የግቢ ጉባኤያት ወጣት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ቴክኖሎጂውን በጥንቃቄና በኃላፊነት ስሜት በመጠቀም፣ በአንድ እጃቸው የሳይንስ ዕውቀታቸውን፣ የምርምር ጽሑፎቻቸውን፣ በሌላ እጃቸው ደግሞ የቤተከርስቲያን አገልግሎትና መንፈሳዊ ሕይወትን ይዘው፣ ለቤተክርስቲያንና ለሀገር የሚተርፍ ብሩህ አእምሮና ንጹሕ ልብ ያላቸው ምሁራን ሆነው መውጣት የምችሉባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ በመረዳት ጊዜው እና ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!