«በጊዜውም ባለጊዜውም ጽና» (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፪)
ከዲያቆን አብርሃም ባንቲሁን
የተወደዳችሁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከሁላችን ጋር ይሁን። በየዓመቱ ሐምሌ፲፱ ቀን በታላቅ መንፈሳዊ አከባበር የምናከብረው የሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ፣ የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣና የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓል አምላካችን እግዚአብሔር በሰላም አድርሶናልና፤ እንኳን አደረሳችሁ!
ይህ በዓል ከአካዳሚክ ትምህርታችሁ ለዕረፍት ወጥታችሁ ወደ ቤተሰቦቻችሁ አሊያም ለተለያዩ ተግባራት በተሰማራችሁበት በዚህ በክረምት ወቅት የሚከበር በመሆኑ፣ በግቢ ውስጥ የነበራችሁን መንፈሳዊ ሕይወት፣ ጸሎትና አንድነት ከግቢ ውጭ ባለው ዓለም ውስጥ በተግባር የምታሳዩበትና የእምነታችሁን ጽናት የምትመሰክሩበት አጋጣሚ ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ «ቃሉን ስበክ፤ በጊዜውም ባለጊዜውም ጽና» (፪ኛጢሞ. ፬፥፪) ብሎ ሲመክረው ብዙ ፈተና እንደሚገጥመው አውቆ ለሚመጣበት ፈተና እንዲዘጋጅ ነው።
“በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ” (ዕብ. ፲፩፥፴፯) ሐዋርያው ይህንን ያለው በሃይማኖታቸው መከራ የተቀበሉ ሰማዕታተ ብሉይ ከአቤል ጀምሮ ያሉትን ከዘረዘረ በኋላ ነው።
“አክሊለ ሰማዕታት፣ የሰማታት አክለል” አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሲመላለስ ዘመኑ ሁሉ በመከራ ነው ያሳለፈው፤ በእርሱ እንደደረሰ በተከታዮቹ ሁሉ እንደሚደርስ ደግሞ ሲነግረን “በእርጥብ እንጨት እንዲህ የሚያደርጉ ከሆኑ፥ በደረቀውስ እንዴት ይሆን?” (ሉቃስ ፳፫፥፴፩) አለ። በዚህም መሠረት ሐዋርያት ሁሉ በመከራ አለፉ፤ ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።” (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፩) እንዲል አምላክን መስሎ እኛም እርሱን እንድንመስል መከረን።
“ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፤ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው።” (መዝ. ፻፲፱፥፻፳፱) እንዲል ልበ አምላክ ዳዊት ጨክነው ሰውነታቸውን ለመከራ የሰጡ ብዙዎች ናቸው። እስከጌታችን ዳግም ምጽአት ድረስ ስትሰበክ የምትቆየው ወንጌለ መንግሥት የምትሰበከው በብዙ መከራ ነውና “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።” (ዕብ. ፲፫፥፯) እያለ ሐዋርያው በአገልግሎት እየጸናን በግብር መከተል እንዳለብን ይመክረናል።
በዚህ መሠረት የክርስቶስ ፈለግ የተከተሉ ወንጌልን በሕይወታቸው የተረጐሙት ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ተጠቃሾች ናቸው።
ሐምሌ ፲፱ ቀን ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ የተቀበሉበት ቀን ነው፡፡ ሕፃኑ ዕድሜው ሦስት ዓመት ሲሆነው እናቱ ከሮሜ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ይዛው ሸሸች፤ በዚያም የሸሸችውን መኮንን እለ አስክንድሮስን አገኘችው፡፡ ሰዎችም ነገር ሠሩባት፤ ወደ እርሱ አስቀረባትና ስለ አምልኮ ጠየቃት፡፡
ቅድስት ኢየሉጣም «መኮንን ሆይ! ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነው ሕፃን አለ፤ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ» አለችው፡፡
ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ንጉሡ ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየና «አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ! እንዴት ነህ? » አለው፡፡ ሕፃኑም መልሶ «አዎ፣ ለእኔ ደስታ ተጠብቆልኛል፤ ለአንተ ግን ኀዘን፣ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ነው» አለው፡፡ እግዚአብሔር ኃይልና ንግግርን ሰጥቶታልና በዚያ ያሉትን እስከሚያስደነግጣቸው ድረስ ንጉሡን፣ መኳንንቱንና ጣዖታቱን ረገማቸው፡፡
መኮንኑም በአፈረ ጊዜ በውስጡ ሰም፣ ጨው፣ ሙጫ፣ የዶሮ ማር፣ እርሳስ፣ ብረት፣ ቅንጭብና ቁልቋል ጨምረው ታላቅ የብረት ጋን እንዲያፈሉ አዘዘ። ፍላቱም በ፲፬ ክንድ ያህል ከፍታ ወደ ላይ ይዘል ነበር።
ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ በእስር ላይ ሳሉ ወደዚህ የፈላ ጋን ውስጥ እንዲጣሉ ተወሰዱ። ቅድስት ኢየሉጣ የፍላቱን ጩኸት በሰማች ጊዜ ብትሸበርም፣ ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተሞልቶ አጸናት፤ ወደ እግዚአብሔርም ስለ እናቱ ጽናት አሳስቦ ጸለየ። ጸሎቱም ተሰምቶ እናቱ ጥንካሬን አገኘች።
ወደ ፈላው ጋን ውስጥ በተጣሉ ጊዜም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የብረቱን ጋን እሳት አጠፋው፤ ቅዱሳኑንም ሳይቃጠሉ አዳናቸው።
መኮንኑም አሳቡ ስላልተሳካ ፲፬ የሾሉና የጋሉ ብረት ችንካሮች አምጥተው ሰባቱን በእናቱ አካል፣ ሰባቱን ደግሞ በሕፃኑ አካል ላይ እንዲቸነክሩ፣ የሕፃኑንም የራስ ቆዳ ገፈው እሳት ውስጥ እንዲጨምሩ አዘዘ። አሁንም መልአኩ መጥቶ መከራውን አራቀለት። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወርዶ አጽናናው፤ ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ታላቅ ቃል ኪዳን ሰጠው።
የተከበራችሁ የግቢ ጉባኤ ልጆች ከበዓሉ ልንወስዳቸው የሚገቡ ብዙ መንፈሳዊ ትምህርቶች አሉ፤ ጥቂቱን ለማንሣት ያህል የቅዱስ ቂርቆስ መንፈሳዊ ድፍረት፣ በነገሥታት ፊት ሳይፈራ በእምነት መቆም እንዲሁም ዓለማዊ ጫናዎችን በጸሎትና በእውቀት መመከት ነው።
የቅድስት ኢየሉጣ ጽናት፡ የሥጋ ፍርሃትን ማሸነፍ፣ መንፈሳዊ ሕይወትን ከዓለማዊ ጥቅም ማስቀደም እና ትውልድን በሃይማኖት ኮትኩቶ ማሳደግን እንዲሁም የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት፣ እግዚአብሔር ለሚታመኑበት ሁሉ ቅርብ አምላክ መሆኑንና መላእክቱን ልኮ እንደሚያድናቸው ማመን እንዳለብን የሚያስተምር ሕይወት ነው።
ታዲያ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በዚህ በክረምት ወቅት በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ የነበራችሁን መንፈሳዊ ንቁ ተሳትፎ በክረምት ወቅትም አጠናክራችሁ መቀጠል አለባችሁ፤ በጊዜውም ባለጊዜውም መጽናት ከእነዚህ ሰማዕታት ተምራችኋልና፤ የተወደዳችሁ ተማሪዎች!
በዚህ በክረምት ወቅት ከዓለማዊ ፈተናዎችና ከከንቱ የሥጋ ፍላጎቶች ተጠብቃችሁ መንፈሳዊ ማንነታችሁን የምታጠናክሩበት፣ ለእግዚአብሔርና ለቤተክርስቲያን ሕይወት ቅድሚያ የምትሰጡበት ጊዜ መሆን አለበት።
የሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ መንፈሳዊ ድፍረት፣ የቅድስት ኢየሉጣ ጽናትና የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት በየዕለት እርምጃችሁ አይለያችሁ። «የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር በቅዱስ ቂርቆስና በቅድስት ኢየሉጣ ጸሎት ይማረን፤ የተራዳኢው መልአክ የቅዱስ ገብርኤል ጥበቃና በረከት አይለየን! ለቅዱሳኑ የሰጠው አምላካዊ ቃል ኪዳንና በረከታቸው ከሁላችን ጋር ለዘላለሙ ይሁኑ።»
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፤ አሜን

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!