ደብረ ምጥማቅ
ከመምህር አዲሱ በዛብህ
”አብ በሰማይ ሆኖ ተመለከተ፣ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ አንድ ልጁንም ልኮ ከአንቺ ሰው ሆነ።”
[ቅዳሴ ዘእግዚእትነ ማርያም]
ደብረ ምጥማቅ ከሠላሳ ሦስቱ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት አንዱ ነው። ደብረ ምጥማቅ በግብፅ ሀገር በምኔተ ገምኑዲ አቅራቢያ የምትገኝ ቦታ ናት። እመቤታችን በስደት ሳለች ጌታ በዚህ ቦታ በስምሽ ዐቢይ ቤተ ክርስቲያን ይታነጻል፤ ስሙንም ደብረ ምጥማቅ ይሉታል ብሎ ነግሯት ነበር። ይኸውም አልቀረ፤ በዚሁ ቦታ በእመቤታችን ስም ቤተክርስቲያን ታንጾ ስሙ ደብረ ምጥማቅ ተብሏል።
በዚህም ዕለት እመቤታችን ከፀሐይ ሰባት እጅ አብርታ ከጉልላቱ ላይ በመንበረ ብርሃን ተቀምጣ፣ መላእክት ሊቃነ መላእክት ከበው ሲያመሰግኗት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት እጅ ሲነሷት ታይታለች። “እንዘ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ሐምሰ ዕለታተ” እንዳለ ደራሲው በልጇ የመለኮት ብርሃን አሸብርቃ መላእክት: ሊቃነ መላእክት: ኪሩቤል: ሱራፌል ከበዋት ነቢያት: ሐዋርያት: ሰማዕታት: ደናግላን: መነኮሳት ሄሮድስ ያስፈጃቸው ሕፃናት ይመጣሉ፤ ሱራፌልም ማዕጠንት ይዘው በእያንዳንዱ እያመሰገኑ ያጥኑ ነበር። ከሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ፣ ቀጥሎም ቅዱስ መርቆሬዎስ በጥቁር ፈረስ በየተራ እየመጡ ይሰግዱላታል።
ከፊቷ ብርሃን የተነሣ 5 ቀን ሌሊቱና ቀኑ አይታወቅም ነበር። በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን ወደ ላይ ሲወረውሩላት የፈቀደችውን ተቀብላ ትልክላቸዋለች። ከዚያም ለበረከት ይካፈሉታል። ከተሰበሰቡትም እስኪ እገሌን አስነሺልን እያሉ ሲለምኗት አስነሥታ በሕይወተ ሥጋ ታሳያቸው ነበር። እንዲህ እየሆኑ በፍጹም ደስታ ሰንብተዋል። እስከ አምስት ቀንም ምእመናኑንም አረማውያኑንም አንድ ወገን አድርጋ ስትባርክ ሰንብታለች። ከዚህም በኋላ ምእመናኑም አረማውያኑም በየዓመቱ እነዚህን አምስት ዕለታት በደብረ ምጥማቅ ተሰብስበው የሚያከብሩ ሆነዋል። የበዓሉ መታሰቢያ ከግንቦት 21 እስከ 25 ቀን ነው።
ግንቦት 21 በደብረ ምጥማቅ በገሃድ ተገልጻ ታላቅ ተአምር ያደረገችበት፡፡
ግንቦት 22ና 23 በደብረ ምጥማቅ ለተሰበሰቡ ምእመናን በግልጽ በመታየት ትነጋገራቸው የነበበት፡፡
ግንቦት 24 እመቤታችን ተወዳጅ ልጇን ይዛ ከአረጋዊ ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር በመሰደድ ግብፅ አገር የገባችበት ዕለት ነው፡፡
ግንቦት 25 ተወዳጅ ልጇ የደረቁ በትሮችን ተክሎ በተአምራት ያለመለመበት ዕለት ናቸው፡፡
በዚህ ዕለትም እናታችን፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ ለ5 ቀናት በግልጽ መታየቷ፣ የሞቱት መነሣታቸው፣ ብርሃን መሆኑ (ጨለማ መጥፋቱ)፣ የሰውን ልመና መቀበሏ …ወዘተ ይነገራል።
“ድንግል ሆይ! በሁሉ አንደበት መመስገን የተገባሽ ስለሆነ በሰማይ ካሉ መላእክትና በምድር ከሚኖሩ ደቂቀ አዳም ሁል ጊዜ ምስጋና ይቀርብልሻል።”
[ቅዳሴ ዘእግዚእትነ ማርያም]
“ሰላም ለእለ ርእዩኪ ከመ ዐይነ ወለት ኀበ እማ፣
መዋዕል ሐምስ እስከ ይትፌጸማ፣
ማርያም ንግሥት ዘደብረ ምጥማቅ ከተማ፣
ብፁዓት አዕይንት ዘነጸራኪ በግርማ፣
ወብፁዓት አእጋር ቅድሜኪ ዘቆማ።”
፤አምስት ቀናት እስኪፈጸሙ ልጅ ወደ እናቷ እንደምታይ ላዩሽ ለእነዚያ ሰላምታ ይገባል፤ የደብረ ምጥማቅ ከተማ ንግሥት ማርያም ሆይ! በግርማ ያዩሽ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው፤ ካጠገብሽ የቆሙ እግሮችም ብፁዓን ናቸው።
[ምንጭ፡ መዝገበ ታሪክ 2 ገጽ 87፣ መድብለ ታሪክ ገጽ 383]
✍️ እንግዲህ የልዑል እግዚአብሔር ልጆች ይህ ዕለት የመላእክትና የቅዱሳን ሁሉ ንግሥት፣ የሰው ልጅ ሁሉ የደኅንነት ምክንያት የሆነችው ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በግልጥ ተገልጣ ሕዝቡን ሁሉ በሰማያዊ ብርሃንና በደስታ የባረከችበት ዕለት ነው። ቅዱሳን አባቶቻችን ስለዚህ ታላቅ ምሥጢር በዕለቱ የሚያስተምሩንን ድንቅ መንፈሳዊ ትምህርት በጥቂቱ እንመልከት፦
፩. እውነተኛው የሰላምና የፍቅር ማእከል
በደብረ ምጥማቅ እመቤታችን ስትገለጥ ክርስቲያኑም፣ እስላሙም፣ አረማውያኑም በአንድነት ሆነው ለተከታታይ አምስት ቀናት በዐይናቸው አይተዋታል። አባቶች እንደሚያስተምሩን፤ ድንግል ማርያም የሰላም እናት ናት። እርሷ በተገለጠችበት ስፍራ ሁሉ ጥላቻ፣ መለያየትና ክፉ ነገር ይጠፋል፤ በምትኩም ፍቅር፣ አንድነትና መጽናናት ይሰፍናል። ዛሬም በቤታችንና በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን የእናትነቷ ጥበቃ ያስፈልገናል።
፪. ሰማይ ወደ ምድር የመጣበት ምሥጢር
በዚያች ዕለት ቅዱሳን መላእክት በማዕጠንት፣ ሰማዕታት በፈረሶቻቸው፣ ሕፃናትም በደስታ እየዘለሉ በፊቷ ሲሰግዱ ሕዝቡ ሁሉ “በሰማይ ያሉ” ይመስላቸው ነበር። አባቶች ይህንን ሲተረጉሙ፦ “ልቡን ንጹሕ ያደረገ ክርስቲያን፣ እመቤታችንን በሃይማኖትና በምግባር የሚያስባት ከሆነ፣ ሕይወቱና ቤቱ ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ ይሆናል” ይሉናል።
፫. የዕንባ አባሽነቷ ሕያው ምስክር
በበዓሉ ዕለት እናትና አባቱ የሞቱበት ወይም ዘመድ የናፈቀው ሰው ሁሉ “እመቤቴ ሆይ አሳዪኝ” ብሎ ሲለምናት ቀድሞ በነበሩበት መልኩ ታሳያቸው ነበር። ይህ የሚያሳየው እመቤታችን የክርስቲያኖችን ጩኸትና ዕንባ የምታብስ፣ የተከዘውን የምታጽናና፣ ለተጨነቁት ሁሉ ፈጥና ደራሽ መሆኗን ነው።
✍️ ይህ በዓል ለሁላችንም የሚያስተምረን ታላቅ ቁም ነገር አለ፦ እመቤታችንን መውደድ ማለት እንደ እርሷ በትሕትና መኖር፣ ልብን ከክፋትና ከሽንገላ ማጽዳት፣ ለሰዎች ሁሉ መልካም ማድረግ ነው። ዛሬ በፈተናና በጭንቀት ውስጥ ያላችሁ ወገኖቼ ሁሉ፣ የደብረ ምጥማቋ እናት ዕንባችሁን አብሳ በሰማያዊ ሰላሟ ትባርካችሁ።
✍️ ድንግል ማርያም ለእኛ ለኦርቶዶክሳውያን ፤
✍️ ድንግል ማርያምን እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የምናከብራት በምክንያት ነው። እርሷ የእግዚአብሔር እናት (ወላዲተ አምላክ ስለሆነች)፣ በድኅነት ታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ ስላላት፣ በእምነትና በትሕትና ምሳሌ ስለሆነች ነው።
- ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ
1) “ቡርክት ነሽ”
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለማርያም፦
“ጸጋ የተሞላብሽ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ ጌታ ካንቺ ጋር ነው።” (ሉቃስ ፩፥፳፰)
እንዲሁም ኤልሳቤጥ “ከሴቶች ሁሉ በላይ ቡርክት ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው።” (ሉቃስ ፩ ፥፵ ፪)
✍️ ይህ ማርያም በእግዚአብሔር ዘንድ ልዩ ጸጋ ያገኘች መሆኗን ያሳያል።
2) “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል”
✍️ ድንግል ማርያም እንዲህ አለች፦
“እነሆ፥ ከእንግዲህ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል።” (ሉቃስ ፩፥፵ ፰)
✍️ ስለዚህ ቅድስት ድንግል ማርያምን ማክበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ነው።
3) “የጌታዬ እናት”
✍️ ቅድስት ኤልሳቤጥም እንዲህ አለች፦
“የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ይህ ከወዴት ሆነልኝ?” (ሉቃስ ፩ ፥፵ ፫)
“ጌታ” የተባለው ክርስቶስ ነው፤ ስለዚህ ማርያም “የጌታ እናት” ተብላለች።
4) ቃል ሥጋ ሆነ
የእግዚአብሔር አብ ልጅ ከእርሷ ሥጋ ነሥቶ ሰው ሆነ፦
“ቃልም ሥጋ ሆነ፥ በእኛም አደረ።” (ዮሐ. ፩ ፥፲ ፬)
✍️ ስለዚህ ድንግል ማርያም ለአምላክ ሰው መሆን ምክንያት ሆነች።
5) ሁሉም ይታዘዙላታል
በቃና ዘገሊላ ተአምር፣ ክርስቶስ በእናቱ ምልጃ ውኃን ወደ ወይን ቀየረ።
እሷም “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለች፡፡ (ዮሐ. ፪ ፥ ፭)
✍️ ይህ የድንግል ማርያምን ምልጃ እና በአማኞች መካከል ያላትን ክብር ያሳያል። - ከሊቃውንት አበው ትምህርት
1) ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ ይላል፦
“ማርያም በእውነት ወላዲተ አምላክ ናት፤ ከእርሷ የተወለደው በሥጋ የተገለጠ እግዚአብሔር ነው።”
✍️ ይህ ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆኑን ያስረዳል።
2) ቅዱስ ቄርሎስ በኤፌሶን ጉባኤ ላይ፦
“ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብለን እንጠራታለን፤ ምክንያቱም ከእርሷ የተወለደው በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር ቃል ነው።”
3) በኤፌሶን ጉባኤ 431 ዓ.ም. ማርያም “Theotokos፣ ወላዲተ አምላክ” መሆኗን አጽንቶ አስተማረ። ይህ የቅድስት ማርያምን ክብር ብቻ ሳይሆን የክርስቶስን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክነትን የሚገልጽ ትምህርት ነው።
4) ቅዱስ ኤፍሬም፦
“ከአንቺ የተወለደው ቅዱስ ነው፤ አንቺም ከሴቶች ሁሉ በላይ የተከበርሽ ነሽ።” - የኦርቶዶክስ አጠቃላይ አስተምህሮ ፤ ድንግል ማርያምን የምናከብራት፦
- እግዚአብሔር ስለመረጣት
- የክርስቶስ እናት ስለሆነች
- በትሕትናና በታዛዥነት ምሳሌ ስለሆነች
- የሰማይና የምድር ንግሥት ስለሆነች
- የድኅነታችን ምክንያት ስለሆነች
ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ ለግብጻውያን ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደምትገለጥላቸው ሁሉ ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም በዘወትር የሕይወት ውጣ ውረዳችን ሁሉ ተገልጣ እንደምትረዳን እናምናለን። በተለይም በአብነት ትምህርት ቤት በቆሎ ተማሪነት ያሳለፈ ሁሉ “በእንተ ስማ ለማርያም” እያለ ያደገባት በመሆኑ የእሷ ፍቅር በልቡናው ጽላት ላይ ተጽፋ ትኖራለች።
ልክ እንደዚሁ ሁሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታችሁን የምትከታተሉ ውድ ተማሪዎች! ዘወትር በቃል ኪዳኗ ሥር ሆናችሁ የሚገጥሟችሁ የሕይወት ፈተናዎች ሁሉ ለድንግል ማርያም ነግራችሁ በአንዳች ሳትጨነቁ ሸክማችሁን ማራገፍ ይኖርባችኋል። እሷ “የበላኤ ሰብእ እመቤት” ከዓለም የኃጢአት ዝለት የምትታደግ አእምሮውን ለብዎውን የምታድል የእነቅዱስ ኤፍሬም፣ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ሕርያቆስ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ የቅርብ ወዳጅ የሆነች ለእነሱ ምሥጢርን የገለጸች ለእኛም ትገልጻለችና “ስለዚህ ድንግል ማርያምን አክብሯት ከሥዕሏም ፊት ስገዱ…”
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ። አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!