የትንሣኤ ትሩፋቶች
ከመምህር ተፈሪ መንገሻ
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትና እምነት መሠረትና የሰው ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገረበት የድል አዋጅ ነው።
ከትንሣኤ እስከ ዕርገት ያሉት አርባ ቀናት እንዲሁም እስከ በዓለ ኀምሳ ያሉት ዐሥር ቀናት ቤተክርስቲያን የተመሠረተችባቸውና ሰማያዊው ሥርዓት ለሐዋርያት የተሰጠባቸው ልዩ ወቅቶች ናቸው። ፅንስ በማሕፀን እስከ አርባ ቀን ድረስ ተሥዕሎ መልክእ እንደሚሰጠው ክርስቶስም በሐዋርያት ልብ ቤተክርስቲያንን እየሣለላቸው ነበር።
ጌታችን በዚህ የክብር ወቅት በመካከላቸው እየተገኘ ለሐዋርያቱ የገለጠላቸው ምሥጢራት፣ የሰጣቸው ተስፋዎችና የመሠረታቸው ሥርዓቶች ዛሬ ለምንኖርባት ቤተክርስቲያን ሕይወትና እስትንፋስ ናቸው። እነዚህ ነጥቦች ትንሣኤው ለዓለም ያበረከተውን ፍሬና ጌታችን በነዚህ ዕለታት የፈጸማቸውን ዓበይት ተግባራት ናቸው።
እነርሱም፦
- ሞትን አሸንፎ ከሙታን መነሣት
ይህ የወርኀ ትንሣኤ መሠረት ነው። ጌታ በሦስተኛው ቀን ከመቃብር ተነሣ፣ ሞት የመጨረሻ አለመሆኑን አሳየ። ሞት በክርስቶስ ፊት ተሸነፈ፣ የሰው ተስፋ ከመቃብር በላይ እንዳለ ገለጠ። (ማቴ. ፳፰፥፩-፮፣ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፶፬-፶፯) - ለሴቶች የትንሣኤውን ዜና በመጀመሪያ ማስታወቅ
የሞት ምክንያት ቅድሚያ ሴቶች ቢሆኑ አሁን የትንሣኤውን ዜና ቀድሞ ለእነሱ ተነገረ። “ለማርያም መግደላዊት መጀመሪያ ታያት” (ማር. ፲፮፥፱) እንዲል።
እንዲሁም መልአኩ ለሴቶቹ “ተነሥቶአል” ብሎ አበሠረ፤ ጌታም በመንገድ ላይ ተገልጦ “ደስ ይበላችሁ” አላቸው። ይህም እግዚአብሔር የመድኃኒቱን ዜና ወደ ደካሞችና በልብ ኀዘን ለተጎዱ ሰዎች እንደሚያመጣ ያሳያል። ማቴ. ፳፰፥፭-፲
በዚህም ሴቶችን የትንሣኤው ቀዳሚ ምስክሮች በማድረግ ክብራቸውን አድሷል። - የሰላም አዋጅን ማወጅ
ደቀ መዛሙርቱ በአይሁድ ፍርሃት ደጆቻቸውን ቆልፈው ሳለ፣ ጌታ በመካከላቸው በመቆም ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ አላቸው” (ዮሐ. ፳፥፲፱)
የዚህም ምክንያት ከትንሣኤው በፊት የነበረውን የፍርሃትና የጭንቀት መንፈስ በሰማያዊ ሰላም ለመተካት ነው። - የመጻሕፍትን ምሥጢር መግለጥ
ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ለነበሩት ሁለት ደቀ መዛሙርት (ሉቃስና ቀለዮጳ) ስለ እርሱ የተጻፈውን ከመጻሕፍት እያነሣ ተርጉሞላቸዋል። “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጎመላቸው” እንዲል። (ሉቃ. ፳፬፥፳፯)
የዚህም ምክንያት ትንሣኤው ድንገተኛ ክስተት ሳይሆን፣ የነቢያት ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ለማስረዳት ነው። - ምሥጢረ ቁርባንን ማጽናት
በኤማሁስ መንገደኞች በቤት እንጀራውን ባርኮና ቆርሶ በመስጠት፣ በምሥጢረ ቁርባን በኩል የሚገኘውን የሱን መገኘት አስተምሯል።
“እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፣ ቆርሶም ሰጣቸው፤ ዓይናቸውም ተከፈተ አወቁትም” (ሉቃ. ፳፬፥፴-፴፩) እንዲል።
የዚህም ምክንያት በአካል ተለይቶ ካረገ በኋላ፣ በምሥጢረ ቁርባን አማካኝነት ከምእመናን ጋር ለዘላለም እንደሚኖር ለማሳየት ነው። - የጥርጣሬን ግድግዳ ማፍረስ
ለቶማስ ቁስሉን እንዲዳስስ በመፍቀድ፣ ትንሣኤው በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በአካል (In the Flesh) መሆኑን አረጋግጧል። “ከዚያም በኋላ ቶማስን፦ ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።” እንዲል። (ዮሐ. ፳፥፳፯)
የዚህም ምክንያት ትንሣኤውን ምትሐት ነው የሚሉ የሐሰት ትምህርቶች እንዲነሡ ያውቃልና ምክንያት ለማሳጣት ነው። - የክህነት ሥልጣንን መስጠት
ሐዋርያትን “እፍ” በማለት መንፈስ ቅዱስንና ኃጢአትን የመፍታትና የማሰር ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። “ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፦ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው። (ዮሐ. ፳፥፥፳፪)
በዚህም ጌታችን የቤተክርስቲያን አስተዳደራዊና መንፈሳዊ መሪነትን (Hierarchy) መሥርቷል - የተስፋና የንስሓ ሥርዓትን ማሳየት
ጌታን ክዶት ለነበረው ለጴጥሮስ ሦስት ጊዜ “ትወደኛለህን?” ብሎ በመጠየቅ ወደ ቀደመ ማዕረጉ መልሶታል። “በጎቼን አሰማራ… ግልገሎቼን ጠብቅ” (ዮሐ. ፳፩፥፲፭-፲፯) ብሎም ሐዋርያነቱን አጽንቶለታል።
አንድ ምእመን ኃጢአት ቢሠራ ተስፋ ቆርጦ እንዳይለይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ንስሓ የገባ ማንኛውም ኃጢአተኛ ወደ ክብሩ ሊመለስ እንደሚችል በተግባር ለማሳየት ይህንን አድርጓል። - መጽሐፈ ኪዳንንና የሥርዓተ አምልኮ ደንቦችን ማስተማር
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትውፊት፣ ጌታ በእነዚህ ቀናት ሐዋርያትን “መጽሐፈ ኪዳን” አስተምሯቸዋል።
“ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገር እየነገራቸው አርባ ቀን ታያቸው” (ሐዋ. ፩፥፫) እንዲል።
ምክንያቱም ሐዋርያት ዓለምን በሚያስተምሩበት ጊዜ እንዴት ማምለክና ምን መጸለይ እንዳለባቸው ግራ እኔዳይገባቸውና ወጥ የሆነ የሥርዓተ ቅዳሴና የሃይማኖት መመሪያ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን።” እንዳለው። ፩ኛ ቆሮ. ፲፬፥፵ - ዓለም አቀፍ የወንጌል ተልእኮ መስጠት
ቤተክርስቲያን ከአይሁድ ተሻግራ ለአሕዛብ ሁሉ እንድትደርስ ትእዛዝ ተሰጥቷታል።
“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” እንዲል። (ማቴ. ፳፰፥፲፱)
የዚህም ምክንያት የክርስትና ሃይማኖት/ቤተክርስቲያን ወሰን ገደብ የሌለባት ዓለም አቀፋዊት (Universal) መሆኑን ለማወጅ ነው። - ወደ ሰማይ ማረጉና ዳግም የመምጣቱን ተስፋ ማጽናት
በመጨረሻም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ባረገ ጊዜ፣ ዳግመኛ እንደሚመጣና እስከ ዓለም ፍጻሜ አብሯቸው እንደሚሆን ተስፋ ሰጥቷል። “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. ፳፰፥፳) እንዲል።
በዚህም ጌታ ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው በአሰቃቂ ስደትና መከራ ውስጥ ሲያልፉ ይህ ተስፋ እንዲያበረታቸው ነው። - በበዓለ ኀምሳ መንፈስ ቅዱስን መላክ
በዐሥረኛው ቀን (ከትንሣኤ በ፶ኛው ዕለት) ጌታችን በሰጠው ተስፋ መሠረት መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወርዷል። “በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ… እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።” እንዲል። (ሐዋ. ፪፥፩-፬)
ይህም የሆነበት ምክንያት
➜ ኃይልን ለመስጠት፦ ሐዋርያት ዓለምን ዞረው ወንጌልን እንዲያስተምሩ ከላይ የሚመጣ ሰማያዊ ኃይል ያስፈልጋቸው ስለነበር።
➜ ቤተክርስቲያንን ለመመሥረት፦ በዕለተ ጰንጤቆስጤ (በዓለ ኀምሳ) በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ሦስት ሺህ ሰዎች ተጠምቀው የቤተክርስቲያን ጉዞ በይፋ የተጀመረበት ዕለት ስለሆነ።
➜ ቋንቋን ለመቀደስ፦ የሰው ልጅ በባቢሎን ግንብ ምክንያት ተከፋፍሎ የነበረውን ቋንቋ (ዘፍ. ፲፩) በመንፈስ ቅዱስ አንድነት አማካኝነት ለወንጌል አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ ነው።
ማጠቃለያ
እነዚህ ሁሉ ከላይ የተመለከትናቸው ሁነቶች የጌታችን ትንሣኤን ተከትለው የመጡ የትንሣው ትፋቶች ናቸው።
የጌታችን ትንሣኤው ባይገለጥ
➡️ ሐዋርያት ለ፫ ዓመት ከ፫ ወር የተማሩት ትምህርት ተረት ሆኖ ይቀር ነበር። ➡️ደቀ መዛሙርቱ በቀቢጸ ተስፋ እንደተበተኑ ይቀሩ ነበር።
➡️የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱ አይረጋገጥም ነበር።
➡️ሞት አስፈሪነቱ እንደቀጠለ ይኖር ነበር።
➡️ደቀ መዛሙርቱ ወንጌልን ለዓለም የመስበክ ወኔ አይኖራቸውም ነበር።
➡️መጽሐፈ ኪዳን መማር አይኖርም ነበር።
➡️የአግብኦተ ግብር ተግባር አይስተዋለም ነበር።
➡️የዕርገት በዓልን አናይም ነበር።
➡️የጰራቅሊጦስ በዓልን አናከብርም ነበር።
እነዚህ በተጨባጭ ዛሬ ለእኛ ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የሚያስረዱን ነገር ቢኖር፣ በስንፍና፣ በቸልተኝነት፣ በግዴለሽነት፣ በሱስ፣ አጠቃላይ በኃጢአት ሞት ሞተን በተስፋ፣ ጊዜያችንን በአግባቡ ተጠቅመን ጠንክረን በመማር፣ በወንጌል እንዲሁም በንስሓ ትንሣኤያችን ካላረጋገጥን የሥጋ ተድላ ደስታ የነፍስ ድኅነትን ማግኘት አይታሰብም።
የጌታችን ትንሣኤና ተከታዮቹ አምሳ ቀናት የታሪክ ለውጥ ብቻ ሳይሆኑ፣ የሰው ልጅ ተስፋ የታደሰባቸውና የቤተክርስቲያን መሠረት የተጣለባቸው የድል ቀናት ናቸው። ትንሣኤው ሞትን ድል ማድረግ ብቻ ሳይሆን አዲስ ሕይወትን፣ አዲስ ተስፋንና አዲስ ሥርዓትን እንዲሁም ሙሉና ሕያው የሆነችውን የክርስቶስን አካል (ቤተክርስቲያንን) ለሰው ልጅ የሰጠበት ታላቅ ምሥጢር ነው።
ስብሐት ለእግዚአብሔር

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!