አዳም

ከመምህር ተስፋ ሚካኤል ታደለ

በቤተክርስቲያን ትውፊት ሐሙስ “የአዳም ሐሙስ” ተብላ የምትታወቀው አዳም የተፈጠረባት ዕለት ስለሆነች ሳይሆን፣ ከገነት ተባርሮ መከራ ሲቀበል እግዚአብሔር የመመለስ ተስፋውን የሰጠበት ዕለት በመሆኗ ነው። (መጽሐፈ አክሲማሮስ ፣ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ሳዊሮስ ስለ ድኅነተ አዳም በተናገረበት)

አዳም በስድስተኛው ቀን (ዓርብ) ተፈጥሮ በዕለተ ዓርብ ቢበድልም፣ እግዚአብሔር ግን በመከራው ውስጥ ተስፋ እንዲሆነው “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእትቤዘወከ፤ አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ” የሚለውን ቃል ኪዳን በሐሙስ ዕለት አረጋገጠለት። ይህ ዕለት ከአዳም ውድቀት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የድኅነት ብርሃን የታየበት፣ ከፈጣሪው ጋር ዳግም ለመገናኘት ቀጠሮ የተያዘበት ታላቅ የቃል ኪዳን ቀን ነው። (መጽሐፈ አክሲማሮስ ፣ በሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ሳዊሮስ ስለ ድኅነተ አዳም በተናገረበት)

ዕለተ ሐሙስ የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን (፭ ሺህ ፭ መቶ ዘመን) መጀመሪያ ተደርጋ ትቆጠራለች፤ እግዚአብሔር ለአዳም የገባለት ቃል “አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም አድንኃለሁ ” የሚል ነበር፤ ይህ ቀጠሮ አዳም በስደት ባለበት ወቅት በየሳምንቱ ሐሙስ ሲመጣ ያንን የተስፋ ቃል እንዲያስብና እንዲጸና ረድቶታል።

በሐዲስ ኪዳን አስተምህሮ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን የፈጸመው በጸሎተ ሐሙስ (በምሥጢር ሐሙስ) ነው። አዳም በዕለተ ዓርብ በበላው ዕፅ ምክንያት ያጣውን የጸጋ ምግብ፣ ጌታችን በሐሙስ ምሽት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመስጠት ካሳ አድርጎለታልና፤ አዳም ሐሙስን በጉጉት ሲጠብቅ እንደነበረ ሁሉ፣ ጌታችንም በዚሁ ዕለት ዝቅ ብሎ እግር በማጠብ የአዳምን ትዕቢት በትሕትና ደመሰሰ። ስለዚህ “የአዳም ሐሙስ” ስንል አዳም ተስፋውን የተቀበለበትንና ክርስቶስ ያንን ተስፋ የፈጸመበትን ምሥጢር በአንድነት የምናስብበት ታላቅ ቀን ማለት ነው። (መጽሐፈ አክሲማሮስ፣ በሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ሳዊሮስ ስለ ድኅነተ አዳም በተናገረበት ምዕ ፪፥፫)

 የአዳም አፈጣጠርና የክብር አክሊል

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ሰማይንና ምድርን፣ በውስጣቸውም ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ አዘጋጅቷል፤ ሊቃውንት ይህንን ሲያብራሩ “ንጉሥ ሳይመጣ አዳራሽ፣ ጌታ ሳይመጣ ግብር አይዘጋጅም” በማለት የሰው ልጅ የፍጥረት ሁሉ ዘውድና ማጠቃለያ መሆኑን ያስረዳሉ።  አዳም የተፈጠረው በስድስተኛው ቀን በዕለተ ዓርብ በሦስት ሰዓት (በሦስተኛው ሰዓት) ሲሆን፣ አፈጣጠሩም ከሌሎች ፍጥረታት የተለየ ነበር። ሌሎች ፍጥረታት በቃለ መለኮት “ይሁኑ” ተብለው ሲፈጠሩ፣ አዳም ግን በሥላሴ ዘንድ “ሰውን በአምሳላችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” ተብሎ፣ በእግዚአብሔር እጅ ተበጃጅቶ የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነው።

አዳም የተፈጠረው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ (ከውኃ፣ ከእሳት፣ ከነፋስና ከምድር) ነው። እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከምድር አፈር አበጀው፤ ከዚያም “የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት” (ዘፍ ፪፡፯) በዚህም ምክንያት ሰው ከእንስሳት ተለይቶ የሚያስብ፣ የሚረዳ፣ የሚናገርና በምድር ላይ የእግዚአብሔር ወኪል ሆኖ እንዲኖር ተደረገ። አዳም በአፈጣጠሩ የሥጋና የመንፈስ ውሕደት በመሆኑ፣ ምድራዊውን ዓለም ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ሆኖ ተሾመ። (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ምዕራፍ ፷፯)

አዳም በገነት ሲሾም የለበሰው የክብር አክሊልና ልብስ ምድራዊ ሳይሆን መለኮታዊ ብርሃን ነበር፤ በወቅቱ ንጉሥ፣ ካህንና ነቢይ ሆኖ ተሹሞ ነበር፤ ፍጥረታት ሁሉ (አራዊትና አዕዋፍ) ስም እንዲያወጣላቸው ወደ እርሱ መጡ፤ ይህም የእውቀቱና የሥልጣኑ ታላቅነት ማሳያ ነው። መላእክትም እንደ ታላቅ ወንድም ያከብሩት፣ እንደ ሞግዚትም ይንከባከቡት ነበር፤ በገነት ውስጥ ካሉት ዛፎች ሁሉ እንዲመገብ ተፈቅዶለት፤ በደስታና በሰላም እንዲኖር ተደረገ። ይህ የክብር ዘመን አዳም ከፈጣሪው ጋር ፊት ለፊት የሚነጋገርበትና ምንም ዓይነት መከራና ድካም የማያውቅበት የመንፈሳዊነት ጫፍ ነበር።

የአዳም ልዩ የክብር አክሊል “በእግዚአብሔር አምሳል” መፈጠሩ ነው። ይህ አምሳል ማለት ሥጋዊ መልክ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር የሰጠው ነፃ ፈቃድ ተጠቅሞ የሚያገኘው በነፍስ በኩል የሚሆንለት ቅድስና ነው ̎ኩኑ ቅዱሳነ እስመ አነሂ ቅዱስ፤ እኔ ቅዱስ ነኛና ቅዱሳን ሁኑ እንዲል፤ ጥበብና ገዥነት ለሰው ልጅ በጸጋ መሰጠቱን ደግሞ በአርኣያ እግዚአብሔር መፈጠሩን ያመለክታል። አዳም በገነት በነበረበት ሰባት ዓመታት፣ ከእግዚአብሔር ጋር በነበረው ኅብረት ምክንያት የሰውነቱ ብርሃን ከፀሐይ ይልቅ ያበራ ነበር፤ ከፍጥረት ሁሉ የላቀና የምድር ሁሉ ጌታ ነበር።

 ፪. ሕገ ገነትና ውድቀት

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ፈጥሮ በገነት ካኖረው በኋላ፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ፍቅርና ታማኝነትን ይገልጥ ዘንድ የሥነ-ምግባር ሕግን ሰጠው፤ ይኸውም “በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” የሚል ነበር (ዘፍ ፪፥፲፮) ።  ይህቺም ዕፅ በባሕርይዋ ክፉ ሆና ሳይሆን፣ አዳም ፍጡር መሆኑንና ከእርሱ በላይ ፈጣሪ መኖሩን እንዲያውቅ፣ እንዲሁም የታዘዘው በመታዘዝ የሚገኘውን በረከት እንዲረዳ የተሰጠች የፈተና መድረክ ነበረች፤ ይህ ሕግ አዳም ያለውን ነፃ ፈቃድ (Free Will) ተጠቅሞ ለፈጣሪው ያለውን ፍቅር በተግባር የሚያሳይበት መሣሪያ ነበር።

የሰው ልጅ ገነት ውስጥ በታላቅ ክብርና ሰላም መኖሩን የተመለከተው የጽልመት ገዥ ሰይጣን፣ በክፋትና በቅናት ተሞላ። “እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ” የሚለውን የሐሰት ተስፋ በመያዝ በእባብ ተመስሎ ወደ ሔዋን ቀረበ። ሰይጣን የተጠቀመበት ስልት እግዚአብሔር የሰጠውን ትእዛዝ እንዲጠራጠሩ ማድረግ ነበርና “በእውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዟልን?” በማለት ጥያቄ በማቅረብ፣ በመቀጠልም “ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ አትሞቱም” በማለት የትዕቢትና የጥርጣሬ ዘርን ዘራባቸው።

የአዳምና የሔዋን ውድቀት መነሻው የመብል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ “ያለ ፈጣሪ ረዳትነት ራሳችንን ችለን እንደ አምላክ እንሆናለን” የሚል የትዕቢት አስተሳሰብ ነው። ሔዋን የዛፏ ፍሬ ለመብላት ያማረ፣ ለዓይንም የሚስብ መሆኑን ባየች ጊዜ ትእዛዙን በመተላለፍ በላች፤ ለአዳምም ሰጠችው። በዚህም ወቅት የባሕርይ ሞት በላያቸው ላይ ሰለጠነ፤ ሊቃውንት እንደሚገልጹት፣ በዚያች ቅጽበት የለበሱት የብርሃን ልብስ ተገፈፈ፤ ራቁትነታቸውን ሆኑ፤ ይህም ከእግዚአብሔር ጸጋ መለየታቸውን የሚያሳይ መንፈሳዊ ዕራቁትነት ነበር፤ ፍርሃትና ጭንቀትም በልባቸው ውስጥ ተከሰተ፤ ከፈጣሪም ድምፅ መሸሸግ ጀመሩ።

ውድቀቱ በአዳምና በሔዋን ላይ ብቻ ሳይሆን በፍጥረት ሁሉ ላይ ተጽዕኖ አሳደረ፤ እግዚአብሔርም በአዳም ምክንያት ምድር የተረገመች እንድትሆን፣ ለአዳም በወዙ እንዲበላ፣ ሔዋንም እንደዚሁ በምጥና በጭንቅ እንድትወልድ ፈረደባቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” የሚለው ሥጋዊ ሞትና ከገነት ተለይቶ ወደ መከራ ምድር መሰደድ ትልቁ ቅጣት ነበር። ሆኖም በዚህ ውድቀት ውስጥ እንኳን የእግዚአብሔር ምሕረት አልተለየም፤ አዳም ከገነት ሲወጣ “አድንኃለሁ ” የሚል የተስፋ ቃል ተሰጥቶታል። ይህ ውድቀት ለሰው ልጅ መዳን ምክንያት ለሚሆነው ለዳግማዊ አዳም (ለክርስቶስ) ቤዛነት መሠረት ሆኗል።

፫. ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ የመመለስ ተስፋ

አዳምና ሔዋን ከገነት ሲባረሩ፣ እግዚአብሔር አምላክ ያለ ተስፋ በትኖ አልተዋቸውም፤ አዳም በሠራው በደል ምክንያት በደረሰበት መከራ ተጸጽቶና አዝኖ ባለበት ወቅት፣ እግዚአብሔር “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ” የሚል ታላቅና የማይታጠፍ የምሕረት ቃል ገባለት፤ ይህ አምስት ቀን ተኩል (፭ ሺህ ፭ መቶ ዘመን) የተባለው ቀጠሮ፣ ለሰው ልጅ የድኅነት ጉዞ መሠረት ሲሆን፤ አዳም ከገነት ሲወጣ በትውልድ መካከል ሲያልፍ ለነበረው ጨለማ እንደ ብርሃን ሆኖ ያገለገለ የተስፋ ስንቅ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ “በእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነው” (፪ ጴጥ ፫፥፰) እንዲል፤ አምስቱ ቀናት አምስት ሺህ ዓመታትን ሲወክሉ፣ ግማሹ ቀን ደግሞ አምስት መቶ ዓመታትን ያመለክታል። አዳም በስድስተኛው ቀን (በዕለተ ዓርብ) በስድስት ሰዓት እንደበደለ ሁሉ፣ ጌታችንም በዓርብ ቀን በስድስት ሰዓት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ አዳምን ነፃ አውጥቶታል።

አዳም ይህንን ቃል ኪዳን አምኖ በመቀበል፣ በመከራ ምድር በኖረባቸው ዓመታት ሁሉ ዓይኑ ወደ ፈጣሪው ተተክሎ ነበር። አዳም በሲኦል ውስጥ ሆኖ እንኳ ይህንን ተስፋ ይጠባበቅ ነበር።  “አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም አድንኃለሁ” የሚለው ቃል፣ አዳም በሞት ጥላ ውስጥ ሆኖ ለሚጠብቃቸው ልጆቹ ሁሉ ያስተላለፈው የነፃነት ዜና ነው፤ ይህ ተስፋ “የአዳም ሐሙስ” ተብሎ ከሚታሰበው ምሥጢር ጋር የተያያዘ ነው፤ ይኸውም የሰው ልጅ ከመከራ ወደ ደስታ፣ ከስደት(ከግዞት) ወደ ነፃነት ከሲኦል ወደ ገነት የሚመለስበት የተስፋ ቀጠሮ የተቀጠረበት ቀን መሆኑ ነው።

እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ለመፈጸም በዘመነ ሥጋዌ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ አዳም የጠፋበትን መንገድ ሁሉ ተከትሎ ፈለገው፤ በዕለተ ዓርብም ወደ ሲኦል ወርዶ የአዳምን ነፍስ ሲጠራው፣ አዳም ለ፭ ሺህ ፭ መቶ ዓመታት የጠበቀው ያ በዕለተ ዓርብ የተነገረው ተስፋ ቃል እንደተፈጸመ አስተዋለ፤ ይህም ተስፋ ለአዳም ብቻ ሳይሆን፣ ለሁላችንም የሰው ልጆች የእግዚአብሔር ቃል እንደማይታጠፍና የታመነ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፤ በመሆኑም ዕለተ ሐሙስን ስናስብ፣ አዳም “ወደ ርስቴ ገነት እመለሳለሁ” ብሎ የጠበቀው ያ የተስፋ ብርሃን እውን ሆኖሎት ፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ መንገዱ የተከፈተበት የምሥጢር ዕለትነቷን እናከብራለን። (መጽሐፈ አክሲማሮስ ፣ በሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ሳዊሮስ ስለ ድኅነተ አዳም በተናገረበት)

 ፬. የአዳም ኑዛዜና ለልጆቹ ያስተላለፈው “መዝገብ (ንብረት)”

አዳም በዚህ ምድር ላይ የ፱፻፴ (ዘጠኝ መቶ ሠላሳ) ዓመታት ዕድሜውን ካሳለፈ በኋላ፣ የዕረፍቱ ሰዓት መቃረቡን አወቀ። በዚያን ጊዜ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን በአንድነት ጠርቶ እንዲሰበሰቡ አደረገ።  ይህ ጉባኤ ተራ የቤተሰብ ጉባኤ ሳይሆን፣ ለሰው ልጅ ትውልድ ሁሉ የሚተርፍ መንፈሳዊ ኑዛዜ የተላለፈበት ታላቅ ጉባኤ ነበር፤ አዳም በፊታቸው ቆሞ፣ ዓይኖቹ በዕንባ ተሞልተው፣ ስለ ገነት ክብር፣ ስለ ውድቀቱ መራራነትና እግዚአብሔር ስለገባለት የተስፋ ቃል በዝርዝር ነገራቸው።

አዳም ከገነት ሲወጣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ይዟቸው የወጣ ሦስት ታላላቅ ንብረቶች ነበሩ፤ እነርሱም ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ ናቸው፤ እነዚህን ውድ ነገሮች ለልጁ ለሴት (Seth) በአደራ ሲሰጠው፣ እንደ ተራ ንብረት ሳይሆን “መዝገብ” አድርጎ ነበር፤ አዳም በኑዛዜው ላይ እንዲህ አላቸው፦ “እነዚህን ንብረቶች ጠብቁ፤ በመጨረሻው ዘመን ዳግማዊ አዳም (ክርስቶስ) ከድንግል ተወልዶ ሲመጣ ለአምላክነቱ፣ ለክህነቱና ለሞቱ ምልክት ይሆኑ ዘንድ ስጡት።” ይህ መዝገብ ከሴት ወደ ኖኅ፣ ከኖኅ ወደ መልከ ጼዴቅ ሲተላለፍ ቆይቶ፣ በመጨረሻም በሰብአ ሰገል አማካኝነት በቤተልሔም ለተወለደው ለክርስቶስ ቀርቧል። ( THE BOOK OF ADAM AND EVE፤ መጽሐፈ አዳም ወሔዋን፣ አንደኛ መጽሐፍ (Book I) ምዕ. ፴፩ )፣ ሁለተኛ መጽሐፍ (Book II) ምዕ. ፰)

አዳም ለልጆቹ ያስተላለፈው መዝገብ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን፣ ሥነ-ምግባራዊም ነበር። ልጆቹ ከቃየን ልጆች (ከክፉዎች) መንገድ እንዲለዩ፣ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁና እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲኖሩ አጥብቆ አዝዟቸዋል፤ ይህ ኑዛዜ አዳም ምንም እንኳ በሥጋ ቢሞትም፣ በተስፋውና በእምነቱ ግን ለልጆቹ ሕያው መሪ ሆኖ መቆየቱን ያሳያል።

አዳም ኑዛዜውን ከፈጸመ በኋላ በዕለተ ዓርብ በዘጠኝ ሰዓት ዐረፈ።  ሊቃውንት አዳም ያረፈበት ሰዓት ጌታችን በመስቀል ላይ ነፍሱን አሳልፎ ለሰው ልጅ ድኅነትን የሰጠበት ሰዓት ጋር አንድ ነው፤ አዳም ሲያርፍ ልጆቹ በመዝገቡና በተስፋው ቃል እየተጽናኑ፣ ፭ ሺህ ፭ መቶ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ያንን የወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ አደራ ሳይለወጥ እንዲቆይ አድርገዋል፤ ይህ የአዳም ኑዛዜ የሰው ልጅ ታሪክ ከመቃብር በላይ በሆነ ተስፋ የታሰረ መሆኑን የሚያሳይ ታላቅ ምስክርነት ነው።

የክርስቶስ ወደ ሲኦል መውረድና አዳምን መጥራት

አዳምና ልጆቹ ለ፭ ሺህ ፭ መቶ ዘመናት በሲኦል ጨለማ ውስጥ ሆነው፣ እግዚአብሔር የገባላቸውን የተስፋ ቃል ይጠባበቁ ነበር፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ካፈሰሰ በኋላ፣ ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ወደ ሲኦል ወረደች፤ ይህ መውረድ በሽንፈት ሳይሆን በድል አድራጊነት ነበር፤ ይኸውም በሲኦል ለነበሩት ነፍሳት ሁሉ የነፃነት አዋጅ የታወጀበትና የሞት ደጆች የተሰበሩበት ታላቅ ምሥጢር ነው፤ ጌታችን ወደ ሲኦል ሲወርድ በብርሃኑ ጨለማውን በትኖታል፤ በዚያም የነበሩት የአዳም ልጆች ሁሉ የጌታን ድምፅ ለመስማት በጉጉት ተጠባበቁ፤ ሐሴትም አደረጉ።

ጌታችን ወደ ሲኦል በወረደ ጊዜ መጀመሪያ የጠራው አባታችን አዳምን ነበር፤ አዳም በበደለ ጊዜ እግዚአብሔር በገነት “አዳም ሆይ ወዴት ነህ?” ብሎ የጠራው ጥሪ፣ በሲኦል ውስጥ “አዳም ሆይ ና ውጣ!” በሚል የመዳን ጥሪ ተተካ፤ ጌታችን አዳምን የጠራው በስሙ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንና የልጅ ልጆቹን ሁሉ ከዲያብሎስ ቀንበር ነፃ ለማውጣት ያለውን ለመዳን የሰጠው የተስፋ ቃል እውን መሆኑን የማመላከት ጉዳይ ነው፤ ይህ ጥሪ ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረው የተስፋ ቃል ፍጻሜ ማግኘቱን አበሠረ።

አዳም የጌታን ድምፅ በሰማ ጊዜ መንፈሱ ታላቅ ደስታና ሐሴት ተሞላ፤ ጌታችን ለአዳም የሰጠው ሰላምታ በሲኦል የነበረውን ሐዘንና መከራ ወደ ሰርግና ደስታ ቀየረው። 

ጌታችን ለአዳም “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ዛሬ ከእኔ ጋር ደስ ይበልህ” ሲለው፤ አዳምም አምላኩንና መድኃኒቱን ሲመለከት በፊቱ ተደፍቶ ሰገደ፤ “ጌታዬና አምላኬ ሆይ! ከዚህ ጨለማ ስላወጣኸኝ አመሰግንሃለሁ” በማለት የምስጋና መሥዋዕት አቀረበ፤ ይህ በጌታና በአዳም መካከል የተደረገው የሰላምታ ልውውጥ፣ የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር ዳግም የታረቀበትና የቀደመው ፍቅር የተመለሰበት ታላቅ ምሥጢር ነው።

ጌታችን አዳምን ከጠራው በኋላ፣ እርሱንም ሆነ በሲኦል ተስፋ አድርገው ይጠባበቁ የነበሩትን ቅዱሳን አባቶችና ነቢያትን ሁሉ ይዞ ወደ ገነት ወጣ። አዳም በአንድ ወቅት በኃጢአቱ ምክንያት የተዘጋችበትን ገነት፣ አሁን በክርስቶስ ቤዛነት ተከፍታ አገኛት። ይህ የክርስቶስ ወደ ሲኦል መውረድና አዳምን መጥራት፣ ሞት ድል የተነሳበትና የሰይጣን ግዛት የፈረሰበት ክስተት ነው።

እኛስ ከዚህ ምን እንማር?

የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አዳም የተፈጠረበት መንገድ (በእግዚአብሔር እጅ መሠራቱና የሕይወት እስትንፋስ እፍ መባሉ) የሰው ልጅ ምን ያህል ክቡር መሆኑን ያሳያል። ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ የተለያዩ ̎የአሮጊት ተረት የሚመስሉ̎ ፍልስፍናዎችና ዓለማዊ አመለካከቶች አስተሳሰባችሁን እና አመለካከታችሁን እንዳይበርዘው (፩ ጢሞ. ፬፥፯) ፤ “የእግዚአብሔር አምሳል” እና የፍጥረት ዘውድ መሆናችሁን አስባችሁ ሙት የሆነውን የነዳርዊን የቅዠት አስተሰሰብ ውድቅ አድርጋችሁ ይህ አርኣያና አምሳለ እግዚአብሔርነታችሁን አጠንክራችሁ መያዝ ይኖርባችኋል፤ ይህ ክብር በሥነ-ምግባርና በቅድስና ሊጠበቅ የሚገባው ትልቅ የአደራ ስጦታ ነው፤ ባላጋራችን ሰይጣን በምቀኝነት ቢቀማን መድኃኔዓለም አባታችን እስከ ሞት የሚያደርስ ዋጋ ከፍሎ የመለሰልን ውድ ስጦታችን ነው፤ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ሥልጣኔ የሚባለውን ጭንብል አድርጎ ዛሬም አምላካችን በመሥዋዕትነት የመለሰልንን ልጅነታችንን ሊቀማን ቋምጦ ይገኛልና “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።” ስለሆነም ልናውቅበት ይገባናል (ኤፌ. ፮፥፲፪)

በገነት ውስጥ የተቀመጠችው አንዲት ዛፍ ለአዳም የነፃነቱና የታማኝነቱ መለኪያ ነበረች፤ በተመሳሳይ መልኩ፣ በግቢ ቆይታ ውስጥ የሚገጥሟችሁ ልዩ ልዩ ፈተናዎች የእናንተን መንፈሳዊ ጥንካሬን የሚፈትኑ ናቸው። አዳም በትዕቢትና በጥርጣሬ እንደወደቀው ሳይሆን፣ ተማሪዎች ̎የዓይን አምሮት የሥጋ ምኞት̎ ሳይበግራችሁ የቤተክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ጋሻ መከታ አድርጋችሁ፣ ̎የእግዚአብሔር ዕቃ ጦር አንስታችሁ̎ ለአምላካችን ያላችሁን ፍቅር በታማኝነት በተግባር ልትገልጡ ይገባል። (ኤፌ. ፮፥፲፫)

አዳም ከገነት ቢወጣም፣ንስሓ መግባቱና ለ፭ ሺህ ፭ መቶ ዘመን በተስፋ መጠባበቁ በትንሽ ነገር ተስፋ ለምንቆርጠው ለእኛ ትልቅ ትምህርት ነው፤ የሰው ልጅ ደካማ ነውና በሐሳብም ሆነ በተግባር ሊወድቅ ይችላል፤ ዋናው ቁም ነገር ግን በውድቀት ውስጥ አለመቅረት ነው። “አድንኃለሁ” የሚለው መለኮታዊ ቃል ኪዳን ዛሬም በንስሓ ለሚመለሱ ሁሉ ክፍት ነው፤ ስለሆነም ተማሪዎች በሕይወታችሁ ስሕተት ብትሰሩ እንኳ እንደ አዳም ወደ ፈጣሪያችን በመጮህና የእርሱ ወደር የሌለው ምሕረት ተስፋ በማድረግ መነሳት እንዳለባችሁ ነው የሚያስገነዝበው።

አዳም ለልጆቹ ያስተላለፈው “የመዝገብ አደራ” (ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ) ለዘመናት ተጠብቆ ለክርስቶስ መቅረቡ፣ በትውልድ መካከል ያለውን መንፈሳዊ ሰንሰለት ያሳያል፤ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸውና ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን ሃይማኖታዊ ዕሴትና ሥነ-ምግባር ሳይበረዝ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት አለባቸው፤ ሃይማኖታችን ወደእኛ የደረሰችውም በትውፊት ነውና፣ የግቢ ጉባኤ አገልግሎት ለቀጣይ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ጠንክሮ በመሥራት ኃላፊነትን የሚሸከም ትውልድ ማፍራት ላይ መሥራትና ለኃላፊነት ብቁና ዝግጁ እንዲሆን ለተተኪው ሊወጡት የሚችሉትን ተግባር መስጠት ያስፈልጋል፤ በዕውቀት ብቻ ሳይሆን ለአደራ ያላቸው ታማኝነትም ሊታወቅ ይገባል።

ጌታችን ወደ ሲኦል ወርዶ አዳምን “ዛሬ ከእኔ ጋር ደስ ይበልህ” ብሎ መጥራቱ የመጨረሻው የፍቅር ጥግ ነው፤ እንደዚሁ ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው እርስ በርስ በሚኖራቸው መስተጋብር የክርስቶስን ትሕትና ሊላበሱ ይገባል፤ ይኸውም የወደቁትን በማንሳት፣ የተቸገሩትን በመርዳትና በይቅርታ በመኖር የአዳም ልጆች መሆናቸውን ሊያስመሰክሩ ይገባል። ድኅነት የተገኘው በትሕትና እንደሆነ ሁሉ፣ ስኬትም የሚገኘው በትሕትና መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። 

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *