ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

ከመምህር አበበ ፍቅሬ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ ያሉ የሳምንታቱ ዕለታት የራሳቸው ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ከእነዚህ ዕለታት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ዕለተ ዓርብን ቤተ ክርስቲያን በማለት ሰይመዋታል። ዓርብ የሚለው ዐረበ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ተካተተ የሚል ትርጕም አለው። ይህም የፍጥረት መካተቻ ቀን መሆኑን የሚያመልክት ነው።

ይህች ዕለት እግዚአብሔር ̎ሰውን በአርኣያችንና በአምሳያችን እንፍጠር ብሎ አዳምን የፈጠረባት ናት፤ (ዘፍ. ፩፥፳፮) በእግዚአብሔር አርኣያና አምሳል የተፈጠረው አዳም ይህንን አምሳለ እግዚአብሔርነቱን በበደሉ ምክንያት ሲያጣ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ በሐዲስ ተፈጥሮ ወደ ቀደመ ቦታው የመለሰባት ዕለት መሆኗን ሊያጠይቁ ዕለቲቱን ቤተ ክርስቲያን ብለው ሰይመዋታል።

በሊቃውንት ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ሲባል ሦስት ዓይነት ትርጕም ተሰጥቶት እናገኛለን፤ የመጀመሪያው የክርስቲያን ሰውነት ቤተ ክርስቲያን ይባላል፤ ሁለተኛው የክርስቲያን ኅብረት አንድነት ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ አምልኮ የሚፈጸምበት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ይሰኛሉ።

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን የሚለው ስያሜ ቤትና ክርስቲያን ከሚሉት የቃላት ጥምርታ የተገኘ ሲሆን፣ ቤተ አደረ፣ ክርስቲያን ከግሪክና ላቲን ቃል ተገኝቶ ክርስቶሳዊ የሚል ትርጕም ሲኖረው፣ አንድ ላይ የክርስቲያኖች ማደሪያ፣ መጸለያ የሚል ይሆናል።

በዘመነ ብሉይ በተለያዩ ስያሜያት ሲጠራ እናስተውላለን፤

ቤቴል ይባላል።

 ̎ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል (ዘፍ. ፳፰፥፳፪) ያዕቆብ ድንጋይ አቁሞ የሜሮን ምሳሌ የሆነውን ዘይት ያፈሰሰበት ቦታ ነው።

ቤቴል ማለት ቤተ እግዚአብሔር ማለት ነው። እንደሚታወቀው ትውልድ ከአምልኮተ እግዚአብሔር ለዓይን ጥቅሻ ያህል ፈቀቅ ባይልም የአምልኮ ቤተ መቅደስ ግን የተሠራው 1100 ቅ.ል.ክ (ቅድመ ልደተ ክርስቶስ) በንጉሥ ሰሎሞን ነው፤ ከዚያ በፊት የነበረው የመገናኛ ድንኳን ሲሆን ንጉሥ ዳዊት ለመሥራት ዕቅድ በያዘ ጊዜ እግዚአብሔር ̎…ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም (፩ኛነገ. ፰፥፲፱) ብሎ ̎የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው?̎ ብሎ እንደጠየቀ (ኢሳ.፷፮፥፩) ምንም እንኳ በቦታ የማይወሰን በሁሉ የመላ ቢሆንም በኵነት ያይደለ በረድኤት ሊያድርበት ለጠቢቡ ሰሎሞን እንዲሠራለት የፈቀደለት ይህ የእግዚአብሔር ቤት ይባላል።

̎ነሐውር ቤተ እግዚአብሔር በአሐዱ ልብ፤ በአንድ ልብ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ፤ (መዝ. ፶፬፥፲፬) ፤ ̎ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ቤተ እግዚአብሔር ነሐውር፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ (መዝ. ፻፳፩፥፩) በማለት እንደተናገረ ነቢዩ ዳዊት።

ቤተ ጸሎት ይባላል።

 ̎ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ።” (ኢሳ. ፶፮፥፯) ፣ (ማቴ. ፳፩፥፲፫)

አማኞች ጸሎት የሚጸልዩበት፣ መሥዋዕት የሚሠዉበት፣ በአጠቃላይ መንፈሳዊ ተግባራት በሙሉ የሚከውኑበትና ለእነዚህ ተግባራት መከወኛ የሚሆኑ ንዋያተ ቅድሳት የሚገኝባት፣ የሰው ልጅም የሚቀደስባት መካነ ዕረፍት (የዕረፍት ቦታ) ሆና የሥጋና የነፍስ ዕረፍት የምትሰጥ ስለሆነች አምላካችን በዚህች ቦታ መኖር እንደሚገባን ሲነግረን ̎በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?̎ ሲል መጠየቁን ልብ ይሏል።(ሉቃ. ፪፥፵፱)

በዕለተ ዓርብ አምላካችን ራሱ መሥዋዕት፣ ራሱ መሥዋዕት አቅራቢ፣ ራሱ መሥዋዕት ተቀባይ ሆኖ ድኅነተ ሥጋ እንጂ ድኅነተ ነፍስ በማያስገኘው በኦሪት መሥዋዕትና ክህነት ምትክ መሥዋዕቱ ከነሙሉ መሠዊያውና ሥርዓተ መሥዋዕት ቀይሮ ቤተ ክርስቲያን በትክክል የገነት (መንግሥተ ሰማይ) ምሳሌ መሆኗን ያረጋገጠባት ታላቅ ዕለት ናት።

የምእመናን ኅብረት(አንድነት)

የምእመናን ኅብረት ቤተ ክርስቲያን በመባል ትጠራለች። ይህም ኤክሌሲያ ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ሲሆን ኀሪት (የተመረጠች)፣ ጽውዕት (የተጠራች) ጉባኤ የሚል ትርጕም የያዘ መሆኑን ሊቃውንቱ ያብራራሉ፤ ሽማግሌዎች በጎ ሥራ የሚሠሩበትንም ጉባኤ ስሙ ኤክሌሲያ በማለት ግሪኮች እንደሚጠቀሙበት ይታወሳል፤ መመረጥና መጠራት የሚለው ሙሴ ሕዝበ እግዚአብሔርን እንዲያስተዳድሩ ሰባ ሊቃናት በኢትዮጵያዊው አማቹ ዮቶር ምክር ተነሥቶ የመረጣቸውን ተያይዞ እስከወዲያኛው የዘለቀ ሥርዓት ሆኖ ሥርዓት ሲሠሩ፣ ሕግ ሲያወጡ ሲያስፈጽሙ እስራኤልን ያስተዳድሩ የነበሩትን ሲያዘክር ነው።

ወጥ የሆነ ሕግ፣ ሥርዓት፣ ትውፊት፣ ቀኖና፣ እምነት ያለን በክርስቶስ ኢየሱስ ዳኝነት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የምንሰበሰብ ̎አንድ ልብ ያለን፣ ̎ራሳችን ክርስቶስ እኛ አካሉ የሆንበት፣ ምግባችን ሥጋ መለኮት፣ መጠጣችን ደመ መለኮት የሆነበት፣ ከአምስቱ የስሜት ሕዋሳት መጥቀን በስድስተኛው የስሜት ሕዋስ በመንፈስ የምንግባባበት፣ ̎በአንድ ልብ አስበን በአንድ አፍ ተናግረን አንድ ውሳኔ የምንወስንበት ጉባኤ የምእመናን ኅብረት ኤክሌሲያ ቤተ ክርስቲያን ናት፤

ብሉይ ኪዳን ለሐዲስ ኪዳን ጥላ፣ አምሳል፣ መርገፍ፣ መስታወት እንደመሆኑ፣ ኤክሌሲያም ለቤተ ክርስቲያን እንዲሁ ነው፤ ምክንያቱም ምድራውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ ምድራውያኑ ከሰማያውያን ጋር ኅብረት የፈጠሩበት መሆኑን በክርስቶስ ልደት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ፤ ምስጋና ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፣ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ…” (ሉቃ. ፪፥፲፬) አሉ ምድራውያንም ከመላእክቱ በጋራ ዘመሩ፤ በዚህም አንድነት ተወጠነ፤ በደብረ ታቦርም በብሔረ ሕያዋን ያለው ኤልያስ፣ በብሔረ ሙታን ያለው ሙሴና በምድር የሚገኙት ሦስቱ የምሥጢር ሐዋርያት የተባሉት ያዕቆብ፣ ዮሐንስና ጴጥሮስ ተገኝተው በአጸደ ነፍስና በአጸደ ሥጋ የሚገኙ የአዳም ልጆች ኅብረት እንደሆነች ታወቀች፤ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን ኲላዊት ትባላለች፤ በምድር፣ በሰማይ፣ በሀገር በአህጉር፣ በቋንቋ፣ በነገድ የማትከፈልና “የሁሉ ፤ Universal” በመሆኗ ነው።

ሰዎች በባሕርዩ ቅዱስ የሆነ አምላክን ለማምለክ በስሙ የተጠሩ፣ በስሙ ቅዱስ ተግባር እየፈጸሙ “ኲኑ ቅዱሳነ እስመ አነሂ ቅዱስ፤ እኔ ቅዱስ ነኛና ቅዱሳን ሁኑ” እንዲል ፍለጋውን በመከተል ቅድስና ገንዘብ የሚያደርጉባት መንገድ በመሆኗም “ቅድስት፤ Holy” ትባላለች።

“ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም።” (ሐዋ. ፬፥፴፪) እንዲል፣ እነ እገሌ የመሠረቷት የእነ እገሌ ቤተ ክርስቲያን የለችም፤ በአንድ በክርስቶስ ደም ተመሥርታለች እንጂ፣ ̎እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ (ዮሐ. ፲፭፥፩-፪)

̎አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። (፩ኛቆሮ. ፲፪፥፲፪-፲፫)

ይህ በጠቅላላ የገለጥነው ስለ ተጋዳይዋ ቤተ ክርስቲያን (Church Militant) ነው፤ ስለ ድል አድራጊዋ ቤተ ክርስቲያን (Triumphant church) ከተባለችው ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ስላለችው ስንናገር ደግሞ ከዚህ እጅግ የጠነከረ ይሆናል፤ ማለትም ምእመናን የተፈጠሩበት ተግባር ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ምስጋና ያለምንም የሐሳብ መከፈል በፍጹም ልብ ይጠቃለላሉና፤ ምክንያቱም ሌላ ምንም የሚያሳስባቸው ሥጋዊ አስተሳሰብ በዚያ አይኖርም።

ይህ የምእመናን አንድነት መተሳሰብና መደጋገፍ ያለበት ፍቅረ ቢጽ የሚገለጥበት እንደመሆኑ አምላክ የሚወደው እንደሆነ ልበ አምላክ ዳዊት ̎ናሁ አዳም ወናሁ ሠናይ ሶበ ይሄልው አኃው ኅቡረ፤ ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፣ እነሆም ያማረ ነው።” (መዝ. ፻፴፫፥፩) ብሎ ሲገልጠው፤ አምላካችንም ̎እንዘ ግቡአን በስምየ ክልኤተ ወሠለስተ አነ እሄሉ ማእከሌሆሙ ህየ፤ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ ፲፰፥፳) ብሎ የነቢዩን ቃል አጠነከረው፤ ጽኑእነቷንም ሲያስረዳ ̎ለቤተ ክርስቲያን ንገራት አለ። (ማቴ. ፲፰፥፲፯)

“እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤” (፩ኛ ጴጥሮስ ፪፥፱) ካሌዎካሌ የሚለውን የጽርዕ ቃል ፍቺው እዚህ ጋር ይገኛል፤ “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፦ በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” (፪ኛ ቆሮ. ፮፥፲፮) እያለ ደግሞ ምንም እንኳ ከጨለማ ለይቶ ወደ ሚደነቅ ብርሀን በብርሀኑ ቢጠራንም ያ ለይቶ ከጠራን ጨለማ ከተሰኘ ከጣዖት ጋር ኅብረት እንዳይኖረን ያስረዳናል።

የአማኝ ሰውነት

የሥላሴ ልጅነት ያገኘ ክርስቲያን ሰውነቱ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ይጠራል፤ ቤተ ክርስቲያን ማለት ማኀደረ እግዚአብሔር የሚል ትርጕም አለውና፤ ማደርያነቱም በድንግል ማርያም ሲያድር ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ በኵነት ሲሆን፤ በጥምቀት ልጆች በሆኑ በአማኒ ያን ያደረው ደግሞ በረድኤት ነው፤ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።” (ራእ. ፫፥፳) “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ።” (ዮሐ. ፮፥፶፮) እንዲል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰውነታችን ከኃጢአት ለይተን በቅድስና ለአምላካችን ስንሰጠው ሱታፌ አምላክ በመቀበል ከአምላካችን ጋር የምንሆንበት ነው።

በእግዚአብሔር አምሳልና አርኣያ የተፈጠረ፣ በበደል ምክንያት ቢተዳደፍ በማየ ገቦ፣ በጥምቀት ልጅነት አግኝቶ በቅብዐ ሜሮን ከብሮ በእግዚአብሔር ልጅ ሥጋና ደም ታድሶ ወደ ቀደመ ክብሩ የተመለሰው ይህ የሰው አካል የእግዚአብሔር ሕግጋትን ሲተላለፍ ደግሞ የእግዚአብሔር ማደሪያ ከመሆን ይፈርስና የርኵስ መንፈስ ማደርያ ይሆናል። (፩ኛ ቆሮ. ፫፥፲፮-፲፯፤ ፮፥፲፱-፳)

አሁን በተጨባጭ ያሉብን ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው

በግል ሕይወታችን

ዘመኑ ድኅረ ድኅረ ዘመናዊነት፤ (post post modernism) እንደመሆኑ መጠን ቶክኖሎጂው በየቀኑ የሚፈጥራቸው፤ ቁሶችና ሐሳቦች ተፈጥሮን የሚገዳደሩ፤ ስብእናን የሚጻረሩ፣ አምላክን የመያሳዝኑ፣ ትውልዱም ከባህል፣ ከሥርዓት፣ ከሞራል፣ ከሃይማኖትና ከመሳሰሉት ጠንካራ ዕሴቶች የሚነጥሉ ናቸው።

ማምለጫ መንገድ (መፍትሔ)

፩. ዘመኑን በሚገባ መዋጀት፡- “ዘመኑን እየዋጃችሁ፥ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ።” (ቆላ. ፬፥፭) ፤ እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። (ኤፌ. ፭፥፲፭) ይህህ ማለት ለሚመጡ የቴክኖሎጂ ግኝቶች ሁሉ እንደ እንግዳ ነገር ቆጥረነው ግር መሰኘት አያስፈልግም፤ የሚጠቅም ከሆነ ቶሎ መላመድ የማይጠቅም ከሆነ ማስወገድ ይገባል፤ ሌላው አጠቃቀሙን በተገቢው መንገድ ማድረግ፤ ይህ ሲባል አንድ ግኝት በጎ እንዲሁም ጎጂ ጎን ይኖረዋልና ነው። ይህ ካልሆነ ጎጂ ጎኑን ብቻ ዓይተን የምናስወግደው ከሆነ ከዘመኑ ጋር አብሮ መላመድ አይቻልምና፤ መርዙን አስወጥቶ ብልሀቱን መጠቀም ይገባል።

ከአሉባልታ ወሬ መታቀብ፡- እስከነ ብሂሉ ̎ወሬ የለውም ፍሬ አበባ የለውም ገለባ ነውና ያለአመክንዮ በግብታዊነት የሚናገሩ አሳች ሰዎችን መስማት ሳይሆን ትክክለኛ መረጃን መያዝ ይገባል።

፫. በዓለት ላይ መመሥረት፡- ይህም ዓለት የተሰኘው ቃለ እግዚአብሔርን በሚገባ መማር ከአሉባልታ ለይቶ ትክክለኛ አካሄድን ያመላክተናል፤ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው።” (መዝ. ፻፲፱፥፻፭) ስለሆነም በሆነው ባልሆነውም ነገር ሳንሸበር በርጋታ እንኖራለን፤ ̎ዐላዋቂዎችን ከጥበብ መራቅ ይገድላቸዋልና፥ ሰነፎችንም ቸልተኛ መሆን ያጠፋቸዋልና። የሚሰማኝ ግን በርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል። (ምሳሌ ፩፥፴፪-፴፫) እንዲህ ከሆነ በነገሮች መደናገጥ ሳይሆን ንስሓ መግባት፣ መቍረብ በጎ ምግባራትን መሥራትን እናዘውትራለን። ካልሆነ ደግሞ ወደነፈሰው እንነፍሳለን፤ ሽብርና ወከባ እየናደን በአሸዋ ላይ እንደተመሠረተ ቤት እንፈርሳለን። በተለይ የጌቢ ጉባኤ ተማሪዎች እናንተ ከዕድሜ አኳያ፤ ከትምህርቱ ጋር ተያይዞ ውስጣዊና ውጯዊ ፈተናዎች በላያችሁ ስለሚያንዣብቡ አጠንክራችሁ የግቢ ጉባኤ መርሐ ግብራትን መከታተልና በአገልግሎት መጽናት ይኖርባችኋል።

የምእመናን አንድነት

ነገደ እስራኤል (ሕዝብና አሕዛብ) ከሚለው የብሉይ የአምልኮ ሥርዓት በክርስቶስ ደም ተዋጅታ የተመሠረተችው ቅድስት፣ ኵላዊት፣ አሐቲ፣ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ምሁራን እንደሚገልጹት በተለያየ ዘመን በዓለም ላይ መከፋፈል እንደተፈጠረ እሙን ነው፤ ለዚህም ዋነኛ መንሥኤ የምንፍቅና ጉዳይ እንዳለ ሆኖ የሥልጣን በላይነት የማንጸባረቅ ጉዳይ መሆኑ ነው፤ ዛሬም የዘርና የፖለቲካ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እንደሚያውካት ተረድተን ልንታገልና ከሥጋ ማንነታችን ይልቅ ለሰማያዊ ዜግነታችንን ቅድሚያ ሰጥተን በክርስቶስ የሆነው ኅብረታችን ልንጠብቅ ያስፈልጋል።

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን

እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው ሁለቱን ጉዳዮች በአግባቡ ከጠበቅን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያናችን ጠብቀናትል ማለት ነው፤ የክርስቶስ አካል የሆነ አማኝ ከነጻ ኅብረታችን በዘረኝነት ካልተበከለ አምላካችን ̎ዝየ አኀድር፤ በዚህ አድራለሁ ይላል፤ ካልሆነ ግን ለግፈኞች አሳልፎ ይሰጣታል።

ስለዚህ በበጎ ምግባራት በመጸናት፣ ራሳችን በንስሐ በማንጻት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ልንኖር ይገባል።

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *