ቶማስ

መምህር ተፈሪ መንገሻ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከትንሣኤ ጀምሮ ያሉትን ዕለታት ትርጉም ባለው ምሥጢር በመሰየም ከትንሣኤው ጋር እያገናኘች ልጆቿን በምሥጢር ሰረገላ ራስ ወደ ሆናት ክርስቶስ ታሳርጋቸዋለች።

ዕለተ ማክሰኞም “ቶማስ” ትባላለች።

ለምን ተሰየመ? ምሥጢሩና አሁን ላለው ዓለም የሚያንጸባርቀው ታላቅ እውነት ምንድነው? እንመለከተዋለን።

ቶማስ ማለት ፀሐይ ማለት ነው። ጌታችን ለመግደላዊት ማርያም ከተገለጠላት በኋላ ጌታ በተነሣባት ዕለት ምሽት ላይ ሐዋርያት አይሁድን በመፍራት ደጃቸውን ዘግተው በቤት ውስጥ ተቀምጠው ነበር። ጌታችንም መዝጊያን ሳይከፍትለት በመካከላቸው ተገኝቶ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።

በዚህም ጌታችን ደቀመዛሙርቱ መምህራቸው ይመራቸውና ሁሉን ጥለው የተከተሉት ጌታ በሮማውያን ጭፍሮች ተይዞ፣ ተሰቅሎ ሞቶ ባለበት ሰዓትና እኛንም ይገድሉናል በሚል ታላቅ ፍርሀት ውስጥ ባሉበት ሰዓት በርግጥም “ሰላም” ያስፈልጋቸው ነበር።

እንዲሁም ደጆች ተዘግተው ባሉበትና እያንዳንዷ ኮሽታ በሚያስደነግጣቸው ሰዓት በር ሳይከፈት በመካከላቸው ተገኝቶ መቆሙ ከምንም በላይ ያልጠበቁትና የሚያስደነግጣቸው ነውና በቅድሚያ ውስጣቸው ሊረጋጋ ያስፈልጋልና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። “ይህንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው።” ዮሐንስ ፳፥፲፱-፳።

ይህም የሥጋና የመለኮት ተዋሕዶ ከትንሣኤ በኋላም አንድ እንደሆነ ያሳያል። ግዙፉ ሥጋ የመለኮትን ረቂቅነት ረቂቁ መለኮት ደግሞ የሥጋን ግዙፍነት ገንዘብ ማድረጉን የሚገልጽ ድንቅ ምሥጢር ነው። እንዲሁም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬ ላይ እንደተገለጸው ለሐዋርያት በተገለጸላቸው ጊዜ “ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው” ስለሚል

አሁን በፊት ለፊታቸው የሚመለከቱት ሥጋ ከሦስት ቀን በፊት በመስቀል ላይ ያንን ሁሉ መከራ የተቀበለውና የሞተው መሆኑን ለመግለጽ ነበርና “እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ [ምትሀት] ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።”

አንድም እንደነ ቅዱስ ቄርሎስና ቅዱስ ኤፍሬም እንዲሁም አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንደተረጎሙት የጌታን በዝግ ቤት መግባቱንና ከኅቱም መቃብር መውጣቱን ከኅቱም ድንግልና መወለዱ ጋር በማገናኘት ሰውም አምላክም መሆኑን የገለጸበት መሆኑን ይናገራሉ።

በዚህም ጌታችን አምላክ እንደመሆኑ በዝግ ቤት ሲገባ ሰው እንደመሆኑ ደግሞ የተወጋውን እጆቹንና ጎኑን በማሳየት ያ አንዱ ሥግው ቃል ከትንሣኤ በፊትና በኋላም በተዋሕዶ የጸና መሆኑን ልብ ይሏል።

ነገር ግን ቶማስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል በዚያ ቤት አልነበረም። በኋላም ጌታን እንዳዩት በነገሩት ጊዜ ትንሣኤውን በቀላሉ ማመን አልፈለገም። “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው።” (ዮሐ. ፳፥፳፭) ቶማስ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት አየነው ስላሉት “ካላየሁ አላምንም” ብቻ ሳይሆን ከማየትም አልፎ “ካልነካሁ አላምንም” የሚል ጭምር ነበር።

የቶማስ ጥርጣሬ ከክህደት የመነጨ የልብ መደንደን አልነበረም፤ ይልቁንም ጌታችን ለዓለም ሁሉ የትንሣኤውን እውነት የሚያትምበት መሣሪያ እንጂ። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “የቶማስ አለማመን ከሌሎቹ ሐዋርያት ማመን ይልቅ እምነታችንን አጸናው” በማለት እንደተረጎመው፣ ቶማስ በኛ ቦታ ሆኖ ጠየቀ፤ በኛ ቦታ ሆኖ መረመረ፤ የእርሱ መጠራጠር እኛ እንድናምን አደረገ።

ከትንሣኤው በኋላ ያለው የክርስቶስ አካል ያ በመስቀል ላይ የዋለው፣ የተቸነከረውና የተወጋው ትክክለኛው ሥጋ መሆኑን (የተዋሕዶን ምሥጢር) ለማረጋገጥ ነበር።

ጌታችን ለሌሎች ተገልጦ ለቶማስ ለስምንት ቀናት ሳይገለጥለት ቆየ። ይህ ሁሉ ምክንያት ነበረው ሌሎች ሐዋርያት ጌታን ስላዩት ሲፈነድቁ ቶማስ ግን ይህንን በመሰለ ጥርጣሬ ውስጥ እያለ ወዲያው አለመገለጡ ውስጡ ላይ ይህንን እውነት የማየት ፍላጎቱ እንደ ማዕበል እንዲቀሰቀስ፣ የናፍቆት እሳቱም ይበልጥ እንዲፋፋም አደረገው።

እኛም በሕይወታችን ውስጥ የምንፈልገው ነገር ወዲያው ሳይሳካ ቀርቶ ሲዘገይ፣ ውስጣዊ ፍላጎታችን እንደ ማዕበል መናወጡ ለጸሎትና ለተጋድሎ ብርታትን የሚሰጥ መንፈሳዊ ጥማት እንዲኖረን ያደርጋል።

ይህም መዘግየት ልክ እንደ ቶማስ ስምንት ቀናት ሁሉ፣ እምነታችን ከመስማት አልፎ ወደ ጥልቅ እርግጠኝነት እንዲሸጋገር የሚረዳ ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስም ይህንኑ ሲያጸና “ነፍሴ እግዚአብሔርን ትጠማለች፤ በውኑ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አየዋለሁ?” (መዝሙር ፵፩፥፪) በማለት የመሻታችንን ፋና ይበልጥ ያበራዋል።

የጌታችንን የፍቅሩን ጥልቀትና የትሕትናውን ስፋት እስኪ በአንክሮ ተመልከቱ! የሰውን ልጅ ከተጠማበት የኃጢአት ድርቀት ሊያረካ በቀትር ፀሐይ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት ሲል በውኃ ጉድጓድ አጠገብ የጠበቀው ያ የነፍሳት ታላቅ እረኛ፤ አሁንም ለአንዲት ለምትጠራጠር ነፍስ ሲል በዝግ በር ውስጥ አልፎ ገባ። ዐሥሩ ደቀ መዛሙርት በቦታው ነበሩ፤ የጌታችን ዐይኖች ግን የፈለጉት አንዱን ቶማስን ብቻ ነበር። ቀጥታ ወደ እርሱ ሄደ፤ ቶማስንም አነጋገረው።

“ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው።” ዮሐንስ ፳፥፳፯

ቶማስ “የችንካሩን ምልክት ካላየሁ…” ብሎ የተናገረው ለብቻው ሆኖ አልነበረም፤ ሌሎች ሐዋርያት ሁሉ በተሰበሰቡበት እንጂ። ጥርጣሬው የዐደባባይ እንደነበረ ሁሉ፣ ፈውሱም የአደባባይ መሆን ነበረበት። ጌታችን ሌሎቹ ባሉበት ለቶማስ ብቻ የተናገረው፣ ቶማስ በወንድሞቹ ፊት ክብሩ እንዲመለስ፣ ጥያቄውም በሚታይና በሚዳሰስ መለኮታዊ ምላሽ ተዘግቶ፣ ያ “አላምንም” ያለበት አንደበት በዚያው ጉባኤ መካከል “ጌታዬና አምላኬ” ብሎ እንዲመሰክር ነው።

መላእክት በፊቱ የሚንቀጠቀጡለት፣ ኪሩቤልና ሱራፌል በመፍራት ፊታቸውን የሚሸፍኑለት ክቡር አምላክ፣ አፈርና ትቢያ የሆነው ፍጡር ጣቱን ወደ ጎኑ እንዲያገባ መፍቀዱ እንዴት ያለ ዕፁብ ድንቅ ምሥጢር ነው!

አንድ አፍቃሪ እናት ልጇን ለማሳመን እስከ ልጇ አስተሳሰብ ዝቅ እንደምትለው ሁሉ፤ ጌታም ቶማስ ወደ እምነት እንዲመጣ እስከሚያስፈልገው ጥግ ድረስ ራሱን ዝቅ አደረገ።

ብዙ ጊዜ እኛ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ ረጅም ደረጃዎችን መውጣት ያለብን ይመስለናል፤ ነገር ግን ጌታ ልክ ለቶማስ እንዳደረገው፣ አንተ ባለህበት የድካም፣ የጥርጣሬና የጭንቀት ደረጃ ድረስ ወርዶ ያገኝሃል። አንተ መጸለይ እንኳ በጠፋህ ጊዜ፣ እርሱ በዝምታህ ውስጥ ሆኖ ያናግርሃል፤ ምክንያቱም እርሱ አባት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ እናት የሚራራ፣ ድካምህን ተረድቶ ዝቅ የሚል አፍቃሪ ነውና።

ጌታችን ቶማስን ቁስሉን እንዲነካው የጋበዘው ትንሣኤው ምትሐት አለመሆኑን፣ ይልቁንም በመስቀል ላይ የተቸነከረው ያው የተወጋው ሥጋው ከሙታን መነሣቱን በተግባር ለማስረገጥ ነው። የቶማስ እጅ የጌታን ጎን ሲዳስስ፣ የዓለም ሁሉ ጥርጣሬ አብሮ ተዳሰሰ፤ ለትውልድ ሁሉ የሚሆን የማይነቃነቅ የትንሣኤ ማረጋገጫም ሆነ።

“በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን።” (ት.ኢሳ ፶፫፥፭) እንዲል የቶማስ የጥርጣሬው ሕመም ቁስሉን በመዳሰስ ተፈወሰ።

“ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።” ዮሐንስ ፳፥፳፰

በርግጥም ሌሎች ሰዎች ከሞት ሲነሡ ቶማስ ተመልክቷል። ነገር ግን ቶማስ ጌታችንን ባየ ጊዜ የሰጠው ምስክርነት ከሞት ስለመነሣቱ ብቻ አልነበረም ስለ ተነሣው አካል ምንነት ማለትም ስለ ጌትነቱና የባሕርይ አምላክነቱ መሰከረ እንጂ።

የተመለከተው ቁስል በሕንድ ለሚደርስበት ስቃይ የሚጸናበት፣ እስከሞት ደርሶ ትንሣኤውን የሚመሰክርበት ሆነ።

“ኢየሱስም፦ ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው።” ዮሐንስ ፳፥፳፱።

ጌታ ቶማስን “ስለ አየኸኝ አምነሃል” ሲለው፣ እምነቱ በማየትና በመዳሰስ ላይ መወሰኑን መገሠጹ ነው፤ ይህም ተግሣጽ ቶማስን ለማሳፈር ሳይሆን፣ እምነቱ ከሥጋዊ ዓይን እይታ ወጥቶ ወደ መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲሸጋገር ለማድረግ ነው።

ምክንያቱም እውነተኛ እምነት “ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ” (ዕብ. ፲፩፥፩) እንጂ በዓይን እይታ ላይ ብቻ የሚቆም አይደለምና።

ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን ምሥጢር ሲያደንቅ “እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ በነፍሳችሁ መዳን የማይነገርና ክብር የሞላበት ሐሴት ታደርጋላችሁ” (፩ጴጥ. ፩፥፰) ይላል።

የተወደዳችሁ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ሆይ ይህን አስተውሉ። ቶማስ በዓይኔ ካላየሁና በእጄ ካልዳሰስኩ አላምንም ማለቱ የአእምሮው ምርምር በእምነቱ ላይ ገዥ እንዲሆን አድርጎት ነበር። እናንተም በያላችሁበት የትምህርት ዘርፍ የምትቀስሙት ዕውቀት አእምሮአችሁን በትዕቢት አሳብጦ ከፈጣሪያችሁ እንዳያርቃችሁ ተጠንቀቁ።

“እግዚአብሔርን ይህን አሳየኝ ያንን አድርግልኝ፣ ከዛ አምንሀለሁ” ማለት የንግድ ሐሳብ እንጂ እውነተኛ እምነት አይደለም።

ጌታ ቶማስን “ያመንህ እንጂ ያላመንክ አትሁን” (ዮሐ. ፳፥፳፯) ብሎ የገሠጸው፣ እናንተም በአጉል ፍልስፍናና በእግዚአብሔር የለሽ ዕውቀት ታውራችሁ “የማይታየውን መለኮት” እንዳትክዱ ነው።

ቶማስ የጌታን ቁስል እንዲዳስስ የተጋበዘው፣ የእኛ የጥርጣሬና የኃጢአት ቁስል የሚድነው በእርሱ የፍቅር ቁስል ብቻ ስለሆነ ነው። “በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን” (ት.ኢሳ. ፶፫፥፭) ተብሎ እንደተጻፈ፣ ከዓለም ፍልስፍናና ሳይንስ ይልቅ ከክርስቶስ መስቀል ሥር እውነተኛውን ሰላም ፈልጉ።

እንደ ቶማስ መጠየቅ ቢኖርባችሁ እንኳ፣ ጥያቄያችሁ ወደ “ጌታዬና አምላኬ” ምስክርነት የሚያደርስ እንጂ ወደ ክሕደት የሚያወርድ እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ጌታችን ቶማስን በዝምታው ውስጥ እስከ ስምንት ቀን እንደጠበቀው ሁሉ፣ እናንተንም በፈተናችሁ ውስጥ በትዕግሥት ይጠብቃችኋል።

በሕይወት ጉዟችሁ ላይ በርካታ የተዘጉ በሮች ሊገጥሟችሁ ይችላሉ፤ የጭንቀት፣ የጥርጣሬ፣ ወይም የብቸኝነት በሮች። ነገር ግን አስታውሱ፤ ጌታችን በዝግ በር አልፎ ወደ ደቀ መዛሙርቱ እንደገባ ሁሉ፣ ዛሬም ወደ እናንተ ሕይወት ለመግባት በር አይከለክለውም።

​እንደ ቶማስ በሐሳብ ማዕበል ስትናወጡ፣ ዓለም በአጉል ፍልስፍናና በእግዚአብሔር የለሽ ዕውቀት ልባችሁን ስታደነዝዘው፣ ውስጣችሁ በተለያዩ ነገሮች ሲጨናነቅና ሰላምና ተስፋ ስታጡ እርሱ በትዕግሥት ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ይላችኋል። ቶማስ የጌታን ቁስል ነክቶ የራሱን የጥርጣሬ ቁስል እንደፈወሰ፣ እናንተም በትምህርታችሁም ሆነ በኑሮአችሁ የሚገጥማችሁን ስብራት ይዛችሁ ወደ እርሱ ቅረቡ። የዓለም ዲግሪና ዕውቀት አፈር ሆኖ ሲቀር፣ እናንተ ግን ሳታዩ በማመናችሁ ያገኛችሁት የብፅዕና አክሊል ለዘለዓለም ይኖራል።

የክርስቶስ ሰላም፣ ከምድራዊ ዕውቀት በላይ የሆነው መለኮታዊ ጥበብ፣ በልባችሁና በአእምሮአችሁ ይንገሥ።

ጌታችን በፈተናችሁ መካከል መጽናናትን፣ በጥርጣሬያችሁ መካከል እውነተኛ እምነትን፣ በድካማችሁም ውስጥ የእጆቹን ብርታት ይስጣችሁ።

ስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *