ሰሙነ ሕማማት ሠሉስ
ከመምህር ተፈሪ መንገሻ
በኢ.ኦ.ተ.ቤ/ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የሰሙነ ሕማማት ዕለታት የየራሳቸው ስያሜና ምሥጢር አላቸው። ከእነዚያ መካከል ዕለተ ሠሉስ የትምህርት ቀን የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል።
ይህንንም አስመልክቶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዕለቱ ጌታ ረጅም ትምህርት ያስተማረበትና ከአይሁድ፣ ከጸሓፍትና ከፈሪሳውያን ብዙ የተንኮል ጥያቄዎችን ተቀብሎ ለእነርሱም በጥበብ መልስ የሰጠበትን ድንቅ ትምህርት ሥርዓት ሠርታ ትዘክራለች/ታስታውሳለች። ይህች ዕለት የሰው ልጅ ውሱን በሆነው አዕምሮውና በተንኮል በተሞላው ልቡ ጥበብንና እውነትን (ክርስቶስን) ሊፈትን የሞከረበትና ጥበብ ክርስቶስ ግን ጥያቄአቸውን በጥያቄ የረታበት፣ ሐሰታቸውን የገለጠበት ዕለት ነው።
በሰኞ ዕለት ነጋዴዎችን ከቤተ መቅደሱ በማስወጣት ስላነጻ፣ ስለገሠጸ በማግሥቱ ማክሰኞ ዕለት ይህንን በማን ሥልጣን እንደሚያደርገውና ሌሎች ብዙ ጥያቄዎችን ጠይቀውታል። (ሉቃ. ፲፥፵፭)
በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ብዙ ጥልቅ ምሥጢራትን የያዘ ክፍል ነውና እነርሱን በዝርዝር ከፋፍለን እንደሚከተለው እንዳስሳቸዋለን።
ተንኮል በጥበብ ፊት (ሉቃ. ፳፥፩-፰)
በሰኞ ዕለት ጌታችን ቤተ መቅደሱን ከነጋዴዎች ማጽዳቱና የሃይማኖቱን ሥርዓት ወደ ንግድ የለወጡትን ማስወጣቱ (ሉቃ. ፲፱፥፵፭) በቤተ መቅደሱ ላይ የበላይነት አለን የሚሉት የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በእነርሱ ዘንድ “የጥቅም መነካት” ፈጥሮባቸው ነበር።
በነጋታው በዕለተ ሠሉስ ጌታችን በቤተ መቅደስ እያስተማረና ወንጌልን እየሰበከ ሳለ፣ እነዚህ መሪዎች ከሽማግሌዎች ሆነው በመምጣት ድንገተኛ “የሥልጣን ጥያቄ” አቀረቡ።
“ወይቤልዎ፥ ንግረነ በመባሕተ መኑ ትገብር ዘንተ? ወመኑ አብሐከ ትግበር ከመዝ? ንገረን ይህንን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማነው? አሉት” (ሉቃ. ፳፥፪)
ይህንንም ሲሉ የሥልጣኑን ምንጭ፣ “የማድረግ መብት” ወይም “ሕጋዊ ፈቃድ” ማለታቸው ነው። እነርሱ ጌታችንን የጠየቁት እንደ አምላክ ሳይሆን “እኛ ካልሾምንህ፣ እኛ ካልፈቀድንልህ ቤተ መቅደሱን የማጽዳት መብት ከየት አገኘህ?” የሚል ለአንድ ሰው የሚጠየቅ በዘመኑ ቋንቋ የቢሮክራሲ ጥያቄ ነው።
ክፋት ልባቸውን ስላሳወረው በዓይናቸው የሚመለከቷቸውን ተአምራት አይቶ ከማመን ይልቅ ከባለሥልጣን የፈቃድ ወረቀት ጠየቁት። ለስሕተታቸው እውነተኛ ማስረጃ ማቅረብ ስለማይችሉ ይህንን ስሕተታቸውን የገለጠባቸውን እውነት ከመቀበል ይልቅ መለኮታዊውን እውነት በሰዋዊ ሥርዓት ለመለካት ሞከሩ።
ዛሬም በሕይወታችን ውስጥ እውነትና ቅድስና ሲመጣ ቀድሞ የሚቃወመን የልባችን ክፋት ጥቅመኝነት ነው። ሀገራችንንና ዓለማችንን ብሎም ቤተ ክርስቲያናችንን እየፈተነ ያለው ከእውነት መንገድ ይልቅ በሐሰት የተገነባ ዝና፣ ስግብግብነትና ሆዳምነት ነው።
በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በኑሯችን የአንድን ሰው መንፈሳዊ ፍሬ ከመመልከት ይልቅ፣ “ከየት መጣ? ማን ፈቀደለት? የእኛ ወገን ነውን? በሚል ሥጋዊ ቅናት የእግዚአብሔርን ሥራ እንቃወማለን።
ጸሐፍት ይህ መንፈሳዊ ውድቀታቸው ሳያንስ እውነትን ለመሸፈን ያደረጉት ጥረት ይደንቃል። ይህ ጥያቄያቸው በተንኮል የተሞላና በሁለት አማራጮች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ጥያቄ ነበር።
➜ ሥልጣኔ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው ቢል፦ አንተ ራስህን አምላክ አድርገሀል ብለው ሊከስሱት ነው።
➜ ሥልጣኔ ከሰው ዘንድ ነው ቢል፦ “እንግዲህ ተራ ሰው ከሆንክ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድርጊት የማድረግ መብት የለህም” ብለው በሕዝብ ፊት ሊከሱትና ሊያስሩት ዐቅደው ነበር።
ጌታችን ግን የእነርሱን ተንኮል ተረድቶ መልሱን በጥያቄ መለሰላቸው።
➜ “ጥምቀቱ ለዮሐንስ እምአይቴኑ ይእቲ እምሰማይኒ ወሚመ እምሰብእኑ፣ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? አላቸው።” (ሉቃ. ፳፥፬)
ይህ የጌታ ጥያቄ ጠያቂዎችን በራሳቸው ጥያቄ ወጥመድ ውስጥ የሚከት ጥያቄ ነበር። ጌታ እነርሱ ሊያጠምዱበት ከዘረጉት ወጥመድ አልፎ እነርሱን በጥያቄ አጠመዳቸው። እነርሱ ባሰቡበት መንገድ አለመመለሱ ብቻ ሳይሆን እነርሱን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከታቸው የመልስ ጥያቄ ሆነባቸው። ስለ እርሱ ማንነት በራሳቸው አንደበት እንዲመልሱ የሚያደርግ ጥያቄ ነበር።
ጌታችን ዮሐንስ መጥምቅን ጠቅሶ የጠየቃቸው ለምንድነው? ቢሉ
➜ ዮሐንስ መጥምቅ ስለ ክርስቶስ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ.፩፥፳፱) ብሎ መስክሯልና ነው።
ስለዚህ እነርሱም “ከሰማይ ናት” ካልን፦ የዮሐንስን ምስክርነት መቀበልና በክርስቶስ ማመን ነበረባቸሁ ሊለን ነው። “ከሰው ናት” ካልን ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደነቢይ ስለሚያከብሩት ሕዝቡን በመፍራት በሁለት የአጣብቂኝ መልስ ውስጥ ገቡ።(ሉቃ. ፳፥፭-፮)
እግዚአብሔርን ብዙ ጊዜ “ለምን እንዲህ ሆነብኝ?” ብለን ስንጠይቅ፣ እርሱ ደግሞ “ቀድሞ የሰጠሁህን ጸጋ ምን አደረግከው?” ይለናል። (ማቴ.፳፭፥፲፭)
ጌታ እዚህ ጋር እያሳየን ያለው እውነትን ፍለጋ ወደ ውጭ ከመሄዳችን በፊት ወደ ውስጣችን እንድንመለከት ነው። ብዙ ጊዜ መልሱ እጃችን ላይ እያለ እኛ ግን እግዚአብሔርን “ሥልጣንህን አሳይ” እንለዋለን።
➜ በልባቸው ላይ ሐሰትን ያነገሡና እውነትን መቀበል የተሳናቸው ጸሐፍት ለጌታ ጥያቄ በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ እውነቱን እያወቁ እንዳላወቁ ሆነው “መልሰውም፦ ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት።” (ሉቃ. ፳፥፯)
➜ “አናውቅም” የሚለው መልሳቸው በታሪክ ውስጥ እጅግ አሳፋሪ ውሸት ነው። እውነቱን ስለማያውቁ ሳይሆን ማወቅ ስለማይፈልጉ ነውና። “ከሰማይ ብንል….ከሰው ብንል….” እያሉ የሚያሰሉት ስለ እውነት ሳይሆን ስለ ጥቅማቸውና ስለ ደኅንነታቸው ነበር።
ዛሬም በዘመናችን “አናውቅም” ባዮች በዝተዋል። በሀገራችን፣ በቤ/ክ አገልግሎታችንና አጠቃላይ በማኅበራዊ ሕይወታችን እውነት ሲገለጥና ግፍ ሲሠራ እያየን፣ ጥቅማችን እንዳይነካ “አላየሁም፣ አልሰማሁም፣ አናውቅም” እንላለን። “ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፣ ሰዎች ግን ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ” እንዲል ቅዱስ ዮሐንስ። (ዮሐ. ፫፥፲፱)
➜ “ኢየሱስም፦ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።” (ሉቃ. ፳፥፰)
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን የጌታ መልስ ሲተረጉም ጌታ መልስ የከለከላቸው ሊቀበሉት ዝግጁ ስላልሆኑና ለእሪያ ዕንቁ ስለማይጣል መሆኑን ይናገራል። (ማቴ. ፯፥፮)
ሰው በልቡ ክፋትን፣ ቂምንና ተንኮልን ሸምቆ የሚጸልየው ጸሎት መልሱ ዝምታ ነው። “በልቤስ በደልን አይቼ ብሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር።” (መዝሙር ፷፯፥፲፰) በማለት ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረ፡፡
ስለዚህ እኛም፡-
➜የእግዚአብሔርን ሥራ በራሳችን አእምሮ አንመዝን። “ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና” (፩ኛ ቆሮ.፩፥፳፭)
➜ ለእውነት ታማኝ እንሁን። እንደ ጸሐፍት በሰዎች ዘንድ የሚመጣብንን “ውግረት፣ ይሉኝታን፣ መገፋትና ሞትን ወዘተ ፈርተን እውነትን መካድ አይገባንም። እንደ ዳዊት “እስመ ለልየ አአምር ጌጋይየ ወኃጢአትየኒ ቅድሜየ ውእቱ በኵሉ ጊዜ፤ እኔ መተላለፌን (በደሌን) አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።” (መዝ.፶፩፥፫) ብለን እውነት ሐሰትን እንዲያሸንፍ በፊቱ ለንስሐ መቅረብና ማልቀስ አለብን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!