የጥያቄ ቀን

ከኄራኒ ጠና

ጥያቄ ቀን

 ለፍጥረተ ዓለም ሶስተኛ ቀን የሆነችው ማክሰኞ በህማማት ሳምንት የጥያቄ/ የትምህርት ቀን ተሰኝታ፤ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀድሞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ማቅረባቸው እንዲሁም እርሱ መልስ በመስጠት ማስተማሩ ይዘከርባታል።

  • ጥያቄ

 ዕለቱን የጥያቄ ቀን ያሰኘው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሰኑይ ያደረገውን አንጽሆተ ቤተ መቅደስ ተከትሎ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይህንን ገበያ መፍታት፤ ተአምራትን ማድረግ ፤ ከምድራውያን ነገስታት ከሌዋውያን ካህናት ያይደለ ትምህርት ማስተማርን በምን ስልጣን ታደርገለህ? ይህንንስ ስልጣን ማን ሰጠህ? ሲሉ መጠየቃቸው ነው። (ማቴ ፳፩፥ ፳፫ – ፳፯)

ጸሐፍት እና ፈሪሳውያን ክርስቶስ ይህንን በማን ስልጣን አንደሚያደርግ ጠፍቷቸው አልነበረም ለጥያቄ የመጡት፤ ይልቁንም እርሱን ለመፈታተን እና ከቃሉም ስሕተትን ለማግኘት ነበር። ልቡና እና ኩላሊትን የሚመረምር ሁሉን አዋቂ አምላክ ግን የልባቸውን ጠማማ መሻት ቀድሞው አውቆ ነበርና ጥያቄያቸውን በሌላ ጥያቄ መለሰላቸው።

“ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች ከሰማይን ወይስ ከሰው አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ፦ ከሰማይ ብንል፦ እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም ይለናል ከሰው ግን ብንል ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። ለኢየሱስም መልሰው፦ አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ፦ እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችኹም አላቸው።” 

እነርሱ በሰው ዘንድ መከበሩን የቃሉ ትምህርትን መወደዱን አይተው ለማወቅ በቅንነት በመጠየቅ ፋንታ በቅናት ምን ብንለው እናሳጣዋለን ወጥመዳችን ውስጥ እናስገባዋለን ብለው አውጥተው አውርደው ጥያቄዎቻቸውን ይዘው መጡ ስለዚህም እንደ አመጣጣቸው መለሰላቸው።

እኛስ ዛሬ ምን ዓይነት ጥያቄ ይዘን ነው ወደ አምላካችን ብሎም ወደመምህራኖቻችን የምንቀርበው? በልባችን ክፉ ምኞትን ይዘን በንግግራችን ዋሽተንበት እንዳይሆን እንጠንቀቅ (ገላ ፮፥፯) በንፁሕ እና በተሰበረ ልብ ነው አምላካችን ፊት መቅረብ ያለብን እንጂ እንደ ጸሐፍት እና እንደ ፈሪሳውያን ነገር ጐንጕነን ሊሆን አይገባም፤ ስንጠይቅ አውቀን ለመራቀቅም አይሁን ይልቁንም በሕይወት ለመኖር እንጠይቅ፤ አዋቂ ነው/ናት ለመባል ለትዕቢትም አይሁን/ ለመረዳት እንጂ፤ የሰውን ስህተት ለማጕላትና ለመሰናክል አይሁን፤ እንዳጠቃላይ ከእርሿቸው መጠበቅ እንዳለብን አምላክ ነግሮናልና ልጠነቀቅ ይገባናል።

  •  ምሳሌዎች

 ክርስቶስ ጥያቄያቸውን በዚህ መንገድ ካስተናገደ በኋላ በምሳሌ ያስተምራቸው ጀመር ሁለት ምሳሌዎችንም ነገራቸው።

 ምሳሌ አንድ: – ፪ ልጆች የነበሩት አንድ ሰው ነበረ፤ ወደ አንደኛው ልጁም ሄዶ ልጄ ሆይ በወይን አትክልቴ ሥራ አለው፤ እርሱም ሊሠራ አልወደደም፤ ኋላ ተመልሶ ግን ተጸጸተ ሠራም፤ አባትየው ወደ ሌላኛው ልጁ አቀና እንዲህም አለው፤ ሌላኛውም ልጅ እሺ አለ አልሰራም ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው ማን ነው? አላቸው። እነርሱም የፊተኛው አሉት።

 በዚህ ምሳሌ አባት የተሰኘው እግዚአብሔር ሲሆን፤ የመጀመሪያው ልጅ ደግሞ በንስሐ የተመለሱ ቀራጮችን ይወክላል፤ ሁለተኛው ልጅ ደግሞ ጸሐፍትና ፈሪሳውያንን ይወክላል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይህንን ሲያብራራ እግዚአብሔር ከንግግራችን ይልቅ ሥራችንን እንደሚፈልግ ይነግረናል፤ ንግግራቸውን ካቀኑ መልካሙን ቃል ከሚናገሩ ነገር ግን በግብራቸው ከሚበድሉ፤ ክርስቶስም ራሱ “ስለዚህ ያዘዟችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ” (ማቴ ፳፫፥፫) ካላቸው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ቀድመው በቀደመ ሕይወታቸው ያላመኑ እንዲሁም የበደሉ ነገር ግን በንስሐ የተመለሱ ቀራጮች መንግሥቱን ይወርሳሉ አለ። እኛ አሁንም ከዚህ ምሳሌ እኒህን እንማራለን: –

  1.  የአንደበት ብቻ ሳይሆን የተግባርም ክርስቲያን ልንሆን እንደሚገባ

ውጫዊ በሆነው ሰው በሚያየው በመድረክና በማህበራዊ ሚዲያ ስለ እምነታችን መመስከር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በሚያየው ሰው በማያየው የግል ሕይወታችንም መልካሙን ምግባር ልንሠራ ይገባናል። ይህም ያለንን እውቀት፣ ገንዘብ የመሳሰሉትን ለተቸገሩ በመመጽወት ፤ በፍጹም ትሕትና እና ፍቅር ከሁሉ ጋር በመኖር…. ሊገለጽ ይችላል።

  •  አሁን አንዳልረፈደ

ልክ እንደቀራጮች ለእግዚአብሔር እምቢ ያልንባቸው ከሕጉም ያፈነገጥንባቸው ጊዜያት ቢኖሩም የምሕረት አባት የሆነው አምላካችን በንስሐ ሊቀበልን ከመንጋውም ሊቀላቅለን የታመነ ነውና፤ ኑ ዛሬ ነገ ሳንል በንስሐ ወደ አምላካችን እንመለስ።

 ምሳሌ 2: –

‹‹ባለቤት ሰው ወይንን ተከለ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጭመቂያም አስቈፈረለት፤ ግንብም ሠራለት፤ ለገባሮችም ሰጥቶአቸው ሄደ፡፡ የሚያፈራበት ወራት በደረሰ ጊዜም፥ ከወይኑ ፍሬ ያመጡለት ዘንድ አገልጋዮችን ወደ ገባሮቹ ላከ፡፡ ገባሮቹም አገልጋዮቹን ይዘው፥ አንዱን በበትር ደበደቡት፤ አንዱንም ገደሉት፤ ሌላውንም በድንጋይ መቱት፡፡ ከዚያም በኋላ ከቀደሙት የሚበዙ ሌሎች አገልጋዮችን ላከ፤ እነርሱንም እንዲሁ አደረጉባቸው፡፡ በኋላም ልጄንስ ይፈሩት ይሆናል ብሎ ልጁን ላከ፡፡ ገባሮቹም ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው፡- እነሆ፥ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ ተባባሉ፡፡ ይዘውም ከወይኑ ቦታ ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት፡፡›› (ማቴ ፳፩ ፥፴፫-፴፱)

በዚህም የምሳሌ ትምህርት የመሬቱ ባለቤት እግዚአብሔር አብ ሲሆን፤ ግንብ፣ ቅጥር እና መጭመቂያ የተሰኙት ደግሞ መቅደሱ፣ የኦሪት ሕግና መሰዊያው ነበሩ፤ ገበሬዎች ደግሞ የአይሁድ ካህናትና አባቶች ናቸው፤ ሰራተኞቹ የተባሉት በየዘመናቱ የተላኩ ነብያት ሲሆኑ፤ የተወደደው ልጅም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ጌታችን በዚህ ምሳሌ የተናገረው በአጭሩ ከብሉይ ወደ ሐዲስ ኪዳን የተደረገውን ሽግግር ነው። እግዚአብሔር የወይን አትክልት ስፍራ ለተባለችው ለእስራኤል እና ለተመረጠው ሕዝቧ በየዘመኑ ነብያትን ልኮ እንዳስተማራቸው፤ እነርሱም በነብያቱ መከራን እንዳጸኑባቸውና እንደገደሏቸው ይህንንም እየተመለከተ ስለ ምሕረቱ ብዛት በድጋሚ ነብያቱን እንደላከ መልሰውም ያንኑ እንዳደረጉባቸው ከዚያም በመጨረሻው የሚወደውን አንዱን ልጁ የተባለው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደላከ በእርሱም እንዳላመኑበት ይልቁንም  በእንጨት መስቀል እንደሰቀሉት ያሳየናል።

ይህም በውጤቱ የወይኑ ስፍራ በክርስቶስ ካላመኑት አይሁዳውያን ተወስዶ ለአዲሶቹ ገበሬዎች በክርስቶስ ላመኑት ለአሕዛብ መሰጠቱን እና ሐዋርያዊ የሆነች ቤተክርስቲያን መመሥረቷን ያሳየናል።

 ከዚህም ምሳሌ እኛ የሚከተሉትን ልንማር ይገባናል: –

  1.  በቤተ ክርስቲያን ያለን ስልጣን ለብቻው ለድኅነታችን ዋስትና እንደማይሆን፤

በምሳሌው ገበሬ የተሰኙት የአይሁድ መንፈሳዊ መሪዎች ካህናት የነበራቸው ስልጣን አላዳናቸውም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእነርሱ የጠበቀውን መልካሙን የምግባር ፍሬ አላፈሩምና። አሁንም እኛ ምንም እንኳ በመድረክ ብንዘምር ስነ-መለኮት አዋቂ ነን ብንል መልካሙን ፍሬ ትሕትናን፣ ፍቅርን ፣ መታዘዝን ገንዘብ ካላደረግን እኒህ ለእኛ ምንም ጥቅም እንደማይሰጡን ነው።

  •  ክርስቶስን መካድ የክሕደት ሁሉ መጨረሻው እንደሆነ

 አይሁድ ልጁ ወራሹ መጣ እርሱን ብንገድል ውርሱን እንወስዳለን ብለው እንዳሉትም አደረጉ፤ ያን ጊዜም ሁሉን ነገር አጡ። እኛም ዛሬ በስሕተት ትምህርት ተወስደን ክርስቶስን እንደ አምላክነቱ ባንቀበለው እንደ አይሁድ ሁሉን እናጣለን። በአገልግሎታችንም ሆነ ከሁሉም ነገር በፊት የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት እና ጌትነቱን በፍጹም ልብ ልናምን ይገባናል። የሐዲስ ኪዳኗ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያንም በዚህ እውነት ላይ ተመስረታለችና። (ማቴ ፲፮ ፥ ፲፰)

  •  የአሁኑ ገበሬዎች እኛ ነን!

 የወይን ቦታው አሁን ለሌላ ፍሬውን ለሚያፈሩ ገበሬዎች ተሰጥቷል፤ ሌሎቹ ገበሬ የተሰኘችው የሐዲሷ ቤተ ክርስቲያን ኅብረት ናት፤ ያህ ማለት እኔ፣ አንተ፣ አንቺ ሁላችንም የቤተክርስቲያን አባላት ማለት ነን። ታዲያ እኛ እውነት ፍሬ እያፈራን ነውን? እኛ የወይን ፍሬው ባለ አደራዎች እንጂ ባለቤቶች አይደለም፤ እናም ባለቤቱ መጥቶ በሰጠኋችሁ ሃይማኖት ሕግ እና ሥርዓት ምን መልካም ፍሬ አፈራችሁ? ቢለን የምንመልሰው አዘጋጀተናልን? ለዚህም ነው በየቀኑ ራሳችንን ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚሆን ምን ፍሬን እያፈራን እንደሆነ ልንጠይቅና በማስተዋልም ልንኖር የሚገባል።

  •  ትምህርት

 በዕለተ ሠሉስ ከላይ ከተነጋገርነው ከጸሐፍት፣ ከፈሪሳውያን እና የጌታችን መልስ ባሻገር ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ያስተማረው ረጅም ትምህርትም ታስቦ ይውላል። (ሉቃ ፳፩፥፪-፴፮)

በዚህም ጌታችን በመጀመሪያ የመበለቲቱ ሁለት ሳንቲም መባእ አመስግኗል፤ በዚያ ብዙ ወርቅ እና ሌላ ውድ የሆነ መባን የሚያገቡ ብዙዎች እያሉ ለምን የእርሷን ሁለት ሳንቲም መባእ አመሰገነ? ቢሉ ሌሎቹ ትርፍና ኪሳራቸውን አስልተው ሲሰጡ እርሷ ግን ያላትን ያለስስት ሰጥታለችና። የአቤልን መሥዋዕት የወደደ ያው እግዚአብሔር አሁንም ከስጦታው ብዛት ይልቅ የልቧን ንጽሕናና ከጎዶሎዋ ላይ ሳትሰስት መስጠቷን አደነቀ።

ጌታችን ዛሬም ቢሆን ያንኑ ስጦታ ይወዳል፤ ያለን ሁሉ ከእርሱ ነውና ለእርሱ ክብር ልናውለውም ይገባል አምላካችን እኮ አይደለም ብርና ንብረት ሕይወትም የሚሰጠው ነው ይህንንም እንኳ ብናደርግ እርሱ ካደረገልን ጥቂቱን እንኳን አንመልስም።

ከዚህም በተጨማሪ በዚህች እለት አምላካችን ስለ ዳግም ምጽአቱ እና ከእርሱ በፊት ስለሚፈጠሩት ነገሮች ከቤተ መቅደሱ መፍረስ ጋር አያይዞ በሰፊው አስተምሯል። ይህንንም ብቻ ተናግሮ ዝም አላለም፤ ምን ልናደርግ እንደሚገባንም ‹‹ራሳችሁን ጠብቁ፤ በመብልና በመጠጥ፥ በመቀማጠልና የዓለምን ኑሮ በማሰብ ልባችሁን አታደንድኑ፤ ያቺ ቀንም በድንገት ትደርስባችኋለች፡፡ በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ እንደተዘረጋች ወጥመድ ትደርሳለችና፡፡ እንግዲህ ከዚህ ከሚመጣው ሁሉ በጸሎታችሁ ማምለጥ እንድትችሉ፥ በሰው ልጅ ፊትም እንድትቆሙ ሁልጊዜ ትጉ፡፡›› (ሉቃ ፳፩፥፴፬-፴፮) ሲል ነግሮናል። እኛም በዳግም ምጽዓቱ የምናምን ይህንን በማሰብ ማስታዋል እንኑር!

በአጠቃላይ በዚች የሰሙነ ሕማማት ማክሰኞ የአይሁድን ጥያቄ እና የጌታችንን ትምህርት አስበን እንውላለን። ከሁሉ በላይ በዕለቱ የሚነገረውን የእግዚአብሔር ቃል እንደ ሕይወታችን ስንቅ ልንወስደው ይገባናል። ካስተማሩት ብዙ እንደሚጠብቁበት ጌታችንም በአንድም በሌላ ካስተማረን ከኛ ፴(ሠላሳ)፣ ፷(ስልሣ) እና ፻(መቶ) ያማረ ፍሬን ይጠብቃልና የተማርነውን በኑሮ እናትርፍበት! ልክ በቅዳሴ እንደምንታዘዘው ‘አልዕሉ አልባቢክሙ/ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ’ ተብለን በምድር ብንኖርም ልቡናችንን ወደላይ ወደ ሰማይ ከፍ አድርገን ከምድራዊ ፍላጎት በላይ በሆነው በእግዚአብሔር ሐሳብ ሕይወታችንን እንምራ።

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር ለዓለም ዓለም አሜን።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *