መርገመ በለስ

ከመምህር አበበ ፍቅሬ

̎ስንዱ እመቤት” የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሀገራዊ የዘመን አቆጣጠር፤ (calendar) ሰርታ ያስረከበች እንደመሆኗ መጠን የእያንዳንዱ የነገረ መለኮት አስተምህሮ፣ ሥርዓተ አምልኮ፤ (Liturgical worship) ፣ አጽዋማት፤ (fasts) ፤ ክብረ በዓላት እኒህን የመሳሰሉ ሁሉ የምታከናውነው ከታላቁ መጸሐፍ ቅዱስ መሠረት አድርጋ በዘመን ቀመር ነው። (ዘፍ. ፩፥፲፬)

ዓመትን፣ ወር፣ ሳምንት፣ ቀን፣ ሰዓት እያለ እስከ ሣድሲት መለኪያ በዘመን መስፈሪያ ውስጥ አካታ ቀመራትን ከጥንታት እንደ ̎ድርና ማግ” አሰናኝታ ወቅቶችን በሚገባ አሰናድታ ስትዋጅ እነሆ ሦስት ዐሥር ምእት ዓመታትን ዘልቃለች።

ኢትዮጵያዊው የዜማ ደራሲ ቅዱስ ያሬድ ዐቢይ ጾምን ከአስተምህሮ አንጻር በስምነት ሣመንታት መክፈሉ እሙን ነው። የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ሥግው ቃል ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረብንን የሞት ጥላ እንዲሁም የጌታችንን መከራ መስቀል አመጸኛው አዳምን ነፃ ለማውጣት እንደ አመጸኛ ተቆጥሮ የደረሰብን ስቃይ ሁሉ በዓይነ ኅሊናችን ስለን በመከራው ተባብረን በትንሣኤው አንድ እንድንሆን በሚል የዐቢይ ጾም ሳምንታት የመጨረሻዎቹ አምስቱ ቀናት ሰሙነ ሕማማት በሚል ጠርቷቸዋል። የእያንዳንዱ እለታት ከአስተምህሮ ጋር በተያያዘ የራሳቸው ስያሜ ያላቸው ሲሆን፤ የመጀመሪያው የሕማማት እለት ሰኞ ̎መርገመ በለስ፤ የበለስ መረገም” በሚል ተጠርቷል።

ስለበለስ መረገም

̎በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና፦ ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት፤ በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች።” (ማቴ. ፳፩፥፲፰-፲፱) እንደሚለን ቅዱስ ማቴዎስ አምላካችን በሕጻናቱ አንደበት እንደተመሰገነ ወደቢታንያ አቀንቶ ሰለነበረ ከቢታንያ ሲመለስ ተርቦ ወደበለስ እነደሄደና ፍሬ እንዳላገኘና እንደረገማት ነው የሚያስረዳን።

የአንድምታ ሊቃውንት በትርጓሜ ወንጌል እንዳስቀመጡት በለስ ለሚለው የተለያዩ ትርጉም ሰጥተው ይበይኑታል፤ በዚህም መሠረት

በለስ ቤተ እስራኤል ነው፤ ̎ሕዝበ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ አምላከ እስራኤል፤ የእስራኤል አምላክ” ተብሎ በስሙ የተጠሩት፣ በስማቸው የተሰየመው እንደውም ̎ወልድየ ዘበኲርየ፤ የበኲር ልጄ” ብሎ በቁልምጫ የሚጠራቸው፤ ̎መጽአ ኃበዚአሁ፤ የእርሱ ወደ ሆኑት ወደ ወገኖቹ መጣ።” (ዮሐ. ፩፥፲፩) ብሎ ዮሐንስ በወንጌሉ እንደ ነገረን ወዳጆቹ ተብለው የሚጠሩት ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን በጠላት እጅ ቢወድቁ ዐሥር ታላላቅ ተአምራትን አሳይቶ ያስለቀቃቸው እግር ለእግር ቢከታተላቸው በባሕር ያሰጠመላቸው፤ ከአለት ውሀ አፍልቆ ያጠጣቸው፤ ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ወደ ከነአን መርቶ ያወጣቸው፤ አሕዛብን አስለቅቆ ከነአንን በመሐላው መሰረት ያወረሳቸው፤ ሲያምጹ እንደልጅ አማሌቃውያንን አስነስቶ የቀጣቸው መልሰው ሲያለቅሱ ደግሞ በወዳጆቹ የታደጋቸው፤ አምላክ ሰው ሆኖ በመካከላቸው ተገልጦ “እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም።” (ማቴ. ፲፫፥፲፯) ፤ ̎አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው።” (ዮሐ. ፰፥፶፮) እያለ ቢነግራቸውም ̎ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት ̎ (ዮሐ. ፰፥፶፯) እንዲያውም “ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ።” (ዮሐ. ፰፥፶፱) እንዲል በሥጋ መገለጡን ሲያዩ ሰውነቱን እንጂ መለከታዊ አካሉን ማየት አልቻሉም፤ ብሉየ መዋእል ጌታን በዕድሜ ገድበውታል። ̎…እነርሱ ግን አልተቀበሉትም።” ዮሐ. ፩፥፲፩) እንዲል ካዱት።

“አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤” (ማቴ. ፫፥፱) “መልሰውም፦ አባታችንስ አብርሃም ነው አሉት። ኢየሱስም፦ የአብሃም ልጆች ብትሆኑ የአብርሃምን ሥራ ባደረጋችሁ ነበር።” (ዮሐ. ፰፥፴፱) እንዲል ቤተ እስራኤል ስም ብቻ ይዘው የቀሩ ምግባር የጎደላቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የዘገዩ ነበሩ።

ጌታችን ፍሬ ምግባርና ሀይማኖትን ፈልጎ በመጣ ጊዜ ቅጠል የአብረሀም ዘር መባልን ብቻ ሆነው ቀሩ። በመሆኑም ̎ለዘለዓለም ፍሬ አይገኝብሽ።” ብሎ ረገማት፤ በዚሁ ቃል መሠረት ምንም እንኳ እንደነ ቅዱስ ጳውሎስና እሱን የመሰሉ የወንጌል አርበኞች ቢገኙም ቤተ እስራኤል የብሉይ አማኝ ብቻ ሆና በመቅረት በክርስቶስ ኢየሱስ የሆነው የሐዲስ ኪዳን ሕግን ከመቀበል ገሸሽ ብላለች። እስካሁን የጌታ መምጣቱን ሳትቀበል ገና እንደሚመጣ ስትጠባበቅ በዘመናችን ትገኛለችና፤ ቤተ እስራኤል የሚጠበቅባትን የሀይማኖትና የምግባር ፍሬ ሳይገኝባት በመቅረቷ ተረገመች ወዲያው ደረቀች።

በለስ የተባለች ኦሪት ናት። መተርጕማኑ እንደሚተረጉሙት ኦሪት ̎ፈጻሜ ሕግ፤ የሕግ መፈጸሚያ ከመባል ውጭ ድኅነትን አላደረገባትም። ማለትም ይህንን አድርጉ ይህንን አታድርጉ ብቻ ትእዛዝን ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ ̎እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። (ማቴ. ፲፱፥፯-፰) እንደሚለው ሕግን ለመፈጸም የተሰጡ አሉና፤ እንዲሁም መሥዋዕትና ሥርዓተ ክህነቱ ጊዜያዊ ድኅነትን ያሰጡ ዘንድ ፍጹም ድኅነትን ማሰጠት የማይችሉ ሕግጋት ነበሩ። ስለዘህም ሻራቸው፤ ̎እምከመ ተሥዕረት መሥዋዕቶሙ ትሠዐር ክህነቶሙ፤ መሥዋዕታቸው ከተሻረች ክህነታችውም ትሻራለች እንዲል መሥዋዕቱ ከነሙሉ የመሠዊያ ሥርዓቱ ተሻረ፤ ምክንያቱም ዘለዓለማዊ የሆነ የነፍስ ድኅነት በሚያሰጠው በአማናዊ መሥዋዕት በኢየሱስ ክርስቶስ ተቀይሯልና ነው።

የክህነት አሰጣጡም ቢሆን ተቀይሯል፤ ቀደም ሲል ክህነት ከሌዊ ወገን ከሆነው ከአሮን ቤት ብቻ ነበር፤ በክህነቱም የሚሠዋው ደመ ነፍስ እንስሳ ሆኖ የሚፈውሰውም ሥጋን ብቻ ነበር፤ የሚታየውም ነቀፋ ነውረ ሥጋ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳን ክህነት ግን ሕዝብና አሕዛብ ብሎ በነገድ(ወገን) ሳይለይ በክርቶስ ያመነ ሁሉ የሚሰጥ ክህነቱም የዘለዓለም ኃጢአት ማስተስሪያ ነው፤ መስፈርቱም ነውረ ሥጋ ሳይሆን ነውረ ነፍስ የሆነው ኃጢአት ነው።

ከዚህም ባሻገር ̎ዓይን ቤዛ ዓይን/ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ የጥፋ” ተብለው የተሰጡት ዓየነት ሕጎችን “…ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።” (ዮሐ. ፰፥፯) “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።” (ዮሐ. ፰፥፲፩) ማንም ስለኃጢአቱ ንሰሐ እንዲገባ እንጂ እንዳይገደል አምላካችን አዟል።

በለስ የተባለው ኃጢአትን ነው። መተርጕማኑ ̎የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነ ኀጢአትም በዚህ ዓለም ሰፍና አገኛት።”፤ አንድም በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ይኮመጥጣል። ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ያሰኛል ኋላ ያሳዝናልና…ፍሬ አይገኝብሽ አላት በአንቺ በመጣ ፍዳ የሚያዝ አይኑር አላት። ኃጢአትም ፈጠና ጠፋች።”

በቀዳማዊ አዳም ምክንያት ሁላችንም ተላላፊዎች ተብለን በኃጢአት ባርነት ሥር ብንሆንም በዳግማዊ አዳም በኢየሱስ ክርስቶስ የተነሳ ሁላችንም ከበደል ከፍደ ነፃ ወጣን፤ በዚህም ማንም በአዳም መተላለፍ የሚጠየቅ እንደሌለና፤ ሁሉም ራሱ ወዶ ፈቅዶ በሚሠራት ኃጢአት የሚጠየቅ መሆኑን አስረዳን።

በባሕርዩ በደል የማይስማማው ንፁሐ ባሕርይ ክርስቶስ ሳይበድል በደለኛ ተብሏል፤ ከወንበዴዎች ጋራ ተሰቅሏል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከባርነት ቀንበርም አላቆናል። መተርጕማኑ እንዳስቀመጡትም ̎ኃጢአት ከሥሩ እንደተነቀለ ዛፍ ሆኗል፤ ከዚህ በኋላ ኃጢአት የሚሰራ ሰው ለተማረከ ወታደር የሚያገለግል ሰው ይመስላል።” 

 ዛሬም አምላካችን ከእያንዳንዳችን ፍሬ ሊፈልግ ይመጣል፤ ገበሬ የተከለው ችግኝ ኮትኵቶ፣ ውሀ አጠጥቶና አርሞ ካሳደገው በኋላ የድካሙን ፍሬ ከዛፉ እንደሚጠብቅ ሁሉ እስከ ሞት ድረስ የሚያደርስ ውድ ዋጋ የከፈለልን አምላካችን ከሁላችንም ፴፣ ፷ና ፻ የሃይማኖት ፍሬ የፈልግብናል

ከዚህ ውጪ ግን ፍሬ የማይገኝብን ከሆነ ̎አሁንም በወይኔ ላይ የማደርገውን እነግራችኋለሁ፤ አጥሩን እነቅላለሁ፥ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፥ ለመራገጫም ይሆናል። ባድማ አደርገዋለሁ፤ አይቈረጥም፥ አይኰተኰትም፤ ኵርንችትና እሾህ ይበቅልበታል፤ ዝናብንም እንዳያዘንቡበት ዳመናዎችን አዝዛለሁ።” (ኢሳ. ፭፥፭-፮) አንዲል ለመከራና ለዋይታ ተላልፈን መሰጠት ይኖራልና፤ ይህ እንዳይሆንብን ከወዲሁ አምላክ በልግስናው በሰጠን ዕድሜያችን ቃሉን ሰምተን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ልንሰራ ይገባናል። ማለትም

የሀይማኖት፣ የምግባር፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የመቻቻል ፍሬ ሊፈልግ ይመጣል፤ ለእኛ ብሎ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎችን አስበን እነዚህን ፍሬ አፍርተን ልንጠብቀው ይገባል።

ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *